ከፍተኛ የታሊባን ባለሥልጣን ቢሯቸው ውስጥ በቦምብ ተገደሉ

ሞሐማድ ዳዉድ ሙዛሚል

የፎቶው ባለመብት, TALIBAN

የምስሉ መግለጫ, በፍንዳታው የተገደሉት የግዛት አስተዳዳሪ ሞሐማድ ዳዉድ ሙዛሚል

በአፍጋኒስታን ሰሜናዊ ክፍል የምትገኘው የባልካህ ግዛት አስተዳዳሪ የሆኑት የታሊባን ሹመኛ ቢሯቸው ውስጥ በተፈጸመባቸው ቦምብ ጥቃት ተገደሉ።

ሞሐማድ ዳዉድ ሙዛሚል የተባሉት የግዛት አስተዳዳሪ ታሊባን ከአንድ ዓመት በፊት ወደ አፍጋኒስታን የመሪነት ሥልጣን ከተመለሰ በኋላ የተገደሉ ከፍተኛ የቡድኑ አመራር ናቸው።

ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሱ ቢሆንም፣ በአይኤስ ታጣቂዎች የሚሰነዘሩ ናቸው በተባሉ ጥቃቶች ታዋቂ የታሊባን ደጋፊዎች እና ሌሎችም ተገድለዋል።

የግዛቱ ፖሊስ እንዳለው በአስተዳዳሪው ላይ የተፈጸመው ጥቃት ምክንያት ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም። በተጨማሪም ለጥቃቱ ኃላፊነት የወሰደ አካል የለም።

ነገር ግን የታሊባን ቃል አቀባይ የሆኑት ዛቢሁላህ ሙጃሂድ በትዊተር ላይ እንዳሉት ባለሥልጣኑ “በእስልምና ጠላቶች ቦምብ ጥቃት መስዋዕት” መሆናቸውን በመግለጽ፣ ስለጥቃቱ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን አመልክተዋል።

ሙዛሚል ቀደም ሲል የአገሪቱ ምሥራቃዊ ግዛት የሆነችው የናንጋርሃር አስተዳዳሪ በነበሩበት ጊዜ ከአይኤስ ታጣቂዎች ጋር ሲካሄድ የነበረውን ውጊያ ሲመሩ ነበር። አሁን ወደ ተገደሉበት ግዛት አስተዳዳሪነት የተዘዋወሩት ባለፈው ጥቅምት ወር ነበር።

በአስተዳዳሪው ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው ሁለተኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው ጽህፈት ቤታቸው ውስጥ በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ጠዋት ሦስት ሰዓት አካባቢ መሆኑን ፖሊስ ገልጿል።

በጥቃቱ ከአስተዳዳሪው በተጨማሪ ቢያንስ አንድ ሌላ ግለሰብ ሲገደል፣ ሌሎች በርካቶች ደግሞ የመቁሰል ጉዳት እንደደረሰባቸው የፖሊስ ቃል አቀባይ አሳውቋል።

በጥቃቱ የቆሰለ አንድ ግለሰብ “ፍንዳታው በተከሰተበት ጊዜ መሬት ላይ ወደቅኩ” ሲል ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግሯል። በፍንዳታው ጓደኛው አንድ እጁን እንዳጣ ማየቱን ጨምሮ ገልጿል።

ፍንዳታው የደረሰው የግዛቲቱ አስተዳዳሪ ቢሯቸው እንደገቡ ወዲያውኑ እንደነበር ይኸው የዐይን እማኝ ተናግሯል።

ፍንዳታው እንዴት እንደተከሰተ የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች ግን የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ነው እያሉ ነው።

ከጥቃቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የግዛቲቱ ዋና ከተማ ማዛሪሸሪፍ ውስጥ ስምንት “አማጺያን እና አጋቾች” መግደላቸውን የታሊባን ባለሥልጣናት ገልጸው ነበር። ነገር ግን የግዛቲቱ ባለሥልጣናት የተገደሉት የየትኛው አማጺ ቡድን አባላት መሆናቸውን በግልጽ አላመለከቱም።

ታሊባኖች ከ20 ዓመታት በፊት ከአፍጋኒስታን የመሪነት ሥልጣን ተባረው የቆዩ ሲሆን፣ ከሁለት ዓመት በፊት በአሜሪካ የሚመራው ኃይል ከአገሪቱ ለቆ ሲወጣ የታሊባን ኃይሎች መልሰው ወደ ሥልጣን ወጥተዋል።

ባለፉት ወራት ተከታታይ የቦምብ ጥቃቶች በአገሪቱ ውስጥ የተፈጸሙ ሲሆን፣ በአብዛኛውም መስጂዶችን እና አናሳ ማኅበረሰቦችን ኢላማ ያደረጉ ናቸው።

እነዚህ ጥቃቶች በአካባቢው የእስላማዊው መንግሥት ቡድን (አይኤስ) አጋር የሆነው አይኤስ-ኬ ተብሎ በሚታወቀው ታጣቂ ቡድን የተፈጸሙ ናቸው ብለው በርካቶች ይናገራሉ። በእርግጥም ቡድኑ ታሊባንን አጥብቆ የሚጠላ ተቀናቃኙ ነው።