የዩኬ መረጃ ሾልኮ ከወጣ በኋላ አፍጋኒስታኖች ለቤተሰቦቻቸው ደኅንነት እንደሚሰጉ ገለጹ

የታሊባን ታጣቂዎች በመኪና ላይ ሆነው ደስታቸውን ሲገልፁ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የታሊባን መንግሥት እ.አ.አ ሐምሌ 2021 በአሜሪካ የሚመራው የምዕራባዊያን ጦር ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ ሥልጣን ይዟል

በዩኬ ባለሥልጣናት በስህተት ስማቸው ይፋ የሆኑ አፍጋኒስታናዊያን ቤተሰቦች በታሊባን አስተዳደር የአፀፋ እርምጃ ይወሰድበናል በሚል ስጋት እንዳደረባቸው ተናገሩ።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በሺህዎች የሚቆጠሩ የአፍጋን ዜጎችን በሚስጥር ወደ ዩኬ የማዘዋውር መረጃ አፈትሎኮ መውጣቱ ይፋ ሆኗል።

ይህ መረጃ የልዩ ኃይል እና የዩኬ የስለላ ድርጅት ኤምአይ6 አባላትን ጨምሮ ከ100 በላይ የእንግሊዝ መኮንኖች እና በሺህዎች የሚቆጠሩ አፍጋናዊያንን ለደህንነት ስጋት የጣለ ነው ተብሏል።

አፈትልኮ የወጣው መረጃ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እስከ ትናንት ሐሙስ ድረስ በሚስጥር ተይዞ የቆየ ሲሆን፤ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ እግዱን ማንሳታቸውን ተከትሎ መገናኛ ብዙኃን ዝርዝሩን እንዲያወጡ ተፈቅዶላቸዋል።

ማክሰኞ ዕለት የዩኬ መንግሥት አፈትልኮ የወጣውን መረጃ ያመነ ሲሆን፤ በ20 ዓመታት የእንግሊዝ ቆይታ ከጦሩ ጋር የሰሩ 19 ሺህ የሚሆኑ አፍጋናውያን ወደ ዩኬ ለመዘዋወር ያቀረቡት ማመልከቻ ይፋ ሆኗል።

የታሊባን መንግሥት እ.አ.አ በ2021 ሥልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ወደ ዩኬ ለመዛወር ጥያቄ ካቀረቡ በሺህዎች የሚቆጠሩ አፍጋኒስታናውያን ውስጥ አማቱ እንደሚገኙ ራሂም (ስሙ የተቀየረ) ተናግሯል።

አምና እና ካቻምን ታሊባን አማቱን ለማግኘት ጥረታቸውን ማጠናከራቸውን የሚናገረው ራሂም አሁን ይህ ለምን እንደሆነ መረዳቱን ይገልፃል።

ታሊባን እስኪሳካለት ድረስ የጊዜ ጉዳይ ነው በሚልም ስጋት አድሮበታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዩኬ መንግሥት የካቲት 2022 መረጃው አፈትልኮ ከወጣ በኋላ በታሊባን ስልታዊ ወይም የበቀል ግድያ ስለመፈፀሙ አነስተኛ ማስረጃ ነው ያለው ይላል።

ነገር ግን ቢቢሲ ያነጋገራቸው አፍጋናዊያን መረጃው አፈትሎኮ በመውጣቱ ድንጋጤ እንደተሰማቸው እና ቤተሰቦቻቸው ላይ የአፃፋ እርምጃ ይወሰዳል በሚል ፍርሃት ላይ ሲሆኑ፤ አፈትልኮ የወጣውን መረጃም "የእንግሊዝ መንግሥት ትልቁ ስህተት" ብለውታል።

በዩኬ የሚኖረው ራሂም ስለ ታሊባን ሂሳብ ማወራረድ ጠንቅቆ ያውቃል።

ታሊባን ስልጣን ከመያዙ ከሁለት ዓመት በፊት ሁለት የአክስቶቹ ልጆች በቡድኑ ተገድለውበታል።

ከዓመታት በኋላ የእንደዚህ ዓይነቱ የበቀል ዒላማ አሁን ተደብቀው በሚገኙት አማቱ ላይ አነጣጥሯል።

"[ከ2023 ጀምሮ] ለምን ታሊባን ለመያዝ እያደነው እንደሆነ ልናውቅ አልቻልንም ነበር" ይላል።

"እርግጠኛ ሆነን መነጋር ባንችልም መረጃው አላቸው ብለን እናምናለን"።

ራሂም 'በአፍጋን ማዘዋወር እና እገዛ ፖሊሲ' መሠረት አማቱ ወደ ዩኬ እንዲዘዋወሩ በማስረጃ አስደግፈው ለመከላከያ ሚኒስቴር ለሦስት ጊዜ ማመልከታቸውን ተናግረዋል።

ከዩኬ መንግሥት ጋር በቀጥታ ባለመስራታቸውም ማመልከቻው ውድቅ እንደተደረገባቸው ራሂም ተናግሯል።

በቅርቡ ግን ከእንግሊዝ ጦር ጋር መስራታቸውን የሚያሳይ "አሳማኝ ማስረጃ" ማቅረባቸውን ጠቅሷል።

ከ2023 ጀምሮ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ባቀረቡላቸው ቤቶች ተደብቀው እንደሚገኙ አክሎ ተናግሯል።

"አንዳንድ የታሊባን አባላት እስር ቤት ለአስርት ዓመታት ቆይተዋል። ወደ ሥልጣን ሲመጡ በቀል ነው የፈለጉት" ይላል።

መረጃው አፈትሎኮ በመውጣቱ የዜና ትኩረት በማግኘቱ የማዘዋወር ስራው ተፋጥኖ አማቱ ዩኬ መጥተው ልጃቸውን የራሂም ባለቤት ያገኛናሉ የሚል ተስፋ ሰንቋል።

የመረጃው ማፈትለክ እውነተኛ አደጋ መደቀኑን በመጠቆም ታሊባን እርምጃ እንደሚወስድባቸው ያለውን ከባድ ስጋት "የጊዜ ጉዳይ ነው" ይላል።

የዩኬ መከላከያ ሚኒስቴር አፈትልኮ በወጣው መረጃ ያደረገው ግምገማ በመረጃው ምክንያት ዒላማ የተደረጉ ሰዎች ስለመኖራቸው የተወሰነ ማስረጃ ነው ያለው ብሏል።

የመከላከያ ሚኒስትር ጆን ሄይሊ ለቢቢሲ በዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱ ሰዎች በታሊባን ዒላማ የመሆን እድልን መጨመሩ "በጣም የማይመስል" ነው ብለዋል።

ለዩኬ ጦር ስለ ታሊባን እንቅስቃሴ መረጃ ሲሰበስቡ የነበሩ አንድ ግለሰብ የመረጃውን ማፈትለክ "የእንግሊዝ መንግሥት የፈፀመው ትልቁ ስህተት ነው" ብለውታል።

ግለሰቡ ወደ ዩኬ የተዘዋወሩ ቢሆንም ለቤተሰቦቻቸው ያስገቡት ማመልከቻ ከአፈተለከው መረጃ ውስጥ ሊሆን ይችላል በሚል ስጋት አድሮባቸዋል።

ይህን ተከትሎም ወላጆቻቸውን ከካቡል እንዲወጡ እንደነገሯቸው የገለፁት ግለሰቡ፤ "ፈርተው ነበር። የት እንደሚሄዱ አያውቁም። . . .እስካሁን አልደወሉልኝም" ብለዋል።

ሌላ ግለሰብም ባፈተለከው መረጃ የወላጆቻቸው እና የሁለት ታናናሽ ወንዶሞቻቸው መረጃ እንደሚገኝበት እንደተነገራቸው ገልፀው፤ ቤተሰቦቻቻው ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር ስለነበራቸው ሥራ እንደማያውቁ አስረድተዋል።