የቱርክ ዶክተሮች ለገንዘብ ሲሉ ጨቅላ ሕፃናት እንዲሞቱ ምክንያት ሆነዋል ተብለው ተከሰሱ

ጨቅላ ልጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለገንዘብ ሲሉ በሆስፒታሎች መካከል የጨቅላ ሕፃናት ልውውጥ አድርገዋል የተባሉ 47 ሰዎች ቱርክ ውስጥ ለፍርድ ቀርበዋል።

አቃቤ ሕግ እንደሚለው ዶክተሮች፣ ነርሶች እና የአምቡላንስ ሹፌሮች ቢያንስ ለ10 ሕፃናት ሞት ምክንያት ናቸው።

ተከሳሾቹ ሐሰተኛ የሕክምና ማስረጃ በመጠቀም ጨቅላ ሕፃናትን ወደ ግል ሆስፒታሎች በማዘዋወር ሕፃናት ላልተፈለገ ጊዜ ማቆያ ውስጥ እንዲከርሙ አድርገዋል ተብለዋል።

1400 ገፅ ያለው የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው በዚህ ድርጊት የተሰማሩ ሰዎች ሕፃናት በማቆያ እያንዳንዷን ቀን ሲያሳልፉ ገንዘብ ያገኛሉ። ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ ያስተባብላሉ።

ተከሳሾቹ እንደሚሉት ይህን ድርጊት የፈፀሙት ከቅን ልቡና በመነሳት ሲሆን ጨቅላዎቹ ጥሩ የሚባል ሕክምና ሲያገኙ ነበር።

ከተከሳሾቹ መካካል ዶ/ር ፊራት ሳሪ “ሁሉም ነገር የተከናወነው በሕጉ መሠረት ነው” ለአቃቤ ሕግ መናገራቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ የተሰኘው የዜና ወኪል ዘግቧል።

ኢስታንቡል የተከፈተውን ችሎት በርካታ ሰዎች ከፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ ውጭ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ነበር። ድምፃቸውን ሲያሰሙ የነበሩት ሰልፈኞች “ጨቅላዎችን የሚገድሉ ይጠየቃሉ” እንዲሁም “የግል ሆስፒታሎች ሊዘጉ ይገባል” የሚሉ መፈክሮች ይዘው ነው የወጡት።

በአውሮፓውያኑ መጋቢት 2023 ማንነታቸውን ያልታወቀ ሰዎች በሰጡት ጥቆማ መሠረት ነው ፖሊስ ምርመራ ማድረግ የጀመረው።

የቱርክ ፖሊስ ያደረገውን ምርመራውን ተከትሎ 10 ሆስፒታሎች የሥራ ፈቃዳቸውን ተነጥቀዋል።

ተከሳሾቹ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ “በቸልተኝነት ምክንያት ለተከሰተ ሞት” በሚል ወንጀል እንዲሁም በማጭበርበር እና ሐሰተኛ ማስረጃ በመጠቀም በርካታ ዓመታት ሊታሰሩ ይችላሉ።