ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ሰሜን ሸዋ ውስጥ የተደጋገመው የአመራሮች ግድያ

ባለፉት ጥቂት ወራት በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ የመንግሥት አመራሮች በክልሉ በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች የሚሰነዘር ጥቃት ዒላማ ሆነዋል።
ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ በርካታ የዞኑ አመራሮች መንግሥት 'ሸኔ' በሚለው የኦሮሞ ነጻነት ታጣቂዎች በተፈጸመባቸው ጥቃቶች ተገድለዋል።
ይህ በታጣቂዎች ጥቃት የሚፈጸምበት የኦሮሚያ ክልል አካባቢ ከአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ክስተቱ በተደጋጋሚ አጋጥሟል።
ረቡዕ የካቲት 12/2017 ዓ.ም. በዞኑ ግራር ጃርሶ ወረዳ የጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታደሰ ተፈሪ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች መገደላቸው ተዘግቧል።
አቶ ታደሰ ከታኅሣሥ ወር መጀመሪያ ወዲህ በሰሜን ሸዋ ዞን አካባቢ በታጣቂዎች የተገደሉ ስድስተኛው የመንግሥት አመራር ናቸው።
ከአንድ ሳምንት በፊት የሰሜን ሸዋ ዞን ሱሉልታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ወርቁ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂ ቡድን በተፈጸማቸው ጥቃት መገደላቸው ይታወሳል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የካቲት 6/2017 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ በሱሉልታ ወረዳ ጥቃት ፈጽሞ የወረዳውን አስተዳዳሪ አቶ አበበ ወርቁን መግደሉን ገልጿል።
የአቶ አበበ ወርቁ ግድያ በተመለከተ መንግሥት 'የለውጡን ጉዞ በተቃወሙ' ታጣቂ ኃይሎች ተገድለዋል ብሏል።
የሱሉልታ ወረዳ በማኅበራዊ ሚዲያ ገፁ ላይ ባወጣው መግለጫ የመንግሥት ባለሥልጣኑ ወደ ሥራ ሲሄዱ በታጠቁ ኃይሎች መገደላቸውን ተናግሯል።
"አቶ አበበ ወርቁ... ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ወደ ሥራ ሲገቡ በታጣቂዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ከተገደሉ በኋላ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ" ብሏል ወረዳው በመግለጫው።
ቢቢሲ ከቤተሰቡ እንደተረዳው አቶ አበበ የተገደሉት ረቡዕ ዕለት የካቲት 5/2017 ዓ.ም. ሲሆን፣ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም በማግሥቱ ተፈጽሟል።
ባለፈው ታኅሣሥ ወር መጨረሻ ላይ በተመሳሳይ ሦስት የዞኑ አመራሮች እና ሌሎች ሁለት ሰዎች በያያ ጉለሌ ወረዳ መገደላቸው ይታወሳል።
በተሽከርካሪ ሲጓዙ የተገደሉት አመራሮች የዞኑ የውሃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ስዩም አበራ የዞኑ አደጋ መከላከል ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጌታሁን እጄታ የዞኑ የፋይናንስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሙሉነህ ግዛው ናቸው።
አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ኃላፊ አመራሮቹ ከመንግሥት ሥራ ሲመለሱ በተፈጸመባቸው ጥቃት እንደተገደሉ በጊዜው ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ተናግረው ነበር።
እኚሁ ኃላፊ ጥቃቱ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን መፈጸሙን ገልጸዋል።
ከአራት ወራት ገደማ በፊት ጥቅምት መጨረሻ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የወጫሌ ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት ንጉሤ ኮሩን ጨምሮ ከ45 በላይ ሰዎች የሚሆኑ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸው ነዋሪዎች ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ተናግረው ነበር።
ለደኅንነታቸው ሲባል ማንነታቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የወረዳው አስተዳዳሪ በታጣቂዎች በተከፈተባቸው ተኩስ ከሞቱት ሰዎች መካከል መሆናቸውን ተናግረዋል።
የወረዳ አስተዳዳሪውን ህልፈተ ሕይወትን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ ግድያውን ያረጋገጠው የሰሜን ሸዋ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ጥቃቱ መንግሥት ሸኔ እያለ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን መፈጸሙን ገልጿል።
የአለልቱ ወረዳ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ "የሕዝብ መሪን በመግደል የሚሳካ ሕልም የለም" ሲል ግድያውን አውግዞ ነበር።
ባለፈው ታኅሣሥ ወር በተመሳሳይ የፖሊስ አዛዥን ጨምሮ ሁለት ሰዎች በታጣቂዎች ተገድለዋል።
የሱሉልታ ወረዳ ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት በፌስቡክ ገፁ ላይ ባሰፈረው መግለጫ እንዳስታወቀው "ሸኔ" የእርቅ ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ በማኅበረሰብ ውይይት ላይ በተሰማሩ ፖሊሶች ላይ ተኩስ ከፍቶ የሁለት ሰዎች ማለፉን አስታውቆ ነበር።
ባለፉት ዓመታት በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱት ታጣቂዎች በመንግሥት ባለሥልጣናት እና በነዋሪዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም ጉዳት በማድረስ እና አግተው በመውሰድ በተደጋጋሚ ይከሰሳሉ።
ከዚህ ቀደም በሰሜን ሸዋ ዞን በኩል በሚያቋርጠው ዋና አውራ ጎዳና ላይ የሕዝብ ማመላለሻ እና የጭነት ተሽከርካሪዎች በታጣቂዎች እንዲቆሙ እየተደረጉ ተደጋጋሚ እገታዎች መፈጸማቸው ይታወሳል።
ተማሪዎች እና ሌሎች መንገደኞችን እንዲሁም ሹፌሮችን ከዕገታ ለማስለቀቅ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ብር መጠየቁን እና መከፈሉን ቤተሰቦች ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ይህ በአካባቢው መንገደኞችን የማገት ድርጊት ባለፉት ወራት ጋብ ያለ ቢሆንም በአካባቢው ባሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ እና ሠራተኞች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ቀጥሏል።
በዚህ ድርጊት መንግሥት ሸኔ የሚለው እና በሽብር ቡድንነት የፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት በተደጋጋሚ በመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ግድያ በተፈጸመበት የሰሜን ሸዋ አካባቢ እንደሚንቀሳቀስ የሚነገር ሲሆን አካባቢዎቹ ከዋና ከተማዋ አዲስ አባባ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ ናቸው።












