አዲስ ለተቋቋመው የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን የተሾሙት ሳንዶካን ደበበ ማን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, @SandokanDebebe
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 4/2018 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብስባ፤ የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽንን የሚያቋቁም ደንብ ሲያጸድቅ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደግሞ አቶ ሳንዶካ ደበበን የተቋሙ ኮሚሽነር እንዲሆኑ ሾመዋቸዋል።
መቋቋሚያ ደንቡ ዛሬ የጸደቀውን የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽንን በመጀመሪያ ኮሚሽነርነት እንዲመሩ የተሾሙት አቶ ሳንዶካ ደበበ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ በመሆን ሲያገለግሉ ነበር።
በዚህ ኃላፊነት ለሁለት ዓመት የሠሩት አቶ ሳንዶካን ከዚያ በፊት በተለያዩ መንግሥታዊ ኃላፊነቶች ላይ በአመራርነት ቆይተዋል።
አቶ ሳንዶካን ከሐሮማያ ዩኒቨርስቲ በ2001 ዓ.ም. በምግብ ሳይንስ እና በምርት አሰባሰብ ቴክኖሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በምግብ ሳይንስ እና ኒዩትሪሽን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘዋል።
በብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ኢንስቲትዩት በምርምር ሠራተኝነት ያገለገሉት አቶ ሳንዶካን፣ ወደ አዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት ለአንድ ዓመት ከአራት ወራት አስተምረዋል።
ከዚያ በመቀጠል በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል ለአንድ ዓመት ከሦስት ወራት በዋና ዳይሬክተርነት ከሠሩ በኋላ በተመሳሳይ የሹመት ደረጃ ወደ የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ተዛውረዋል።
አቶ ሳንዶካን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን በሰኔ 2012 ዓ.ም. የተሾሙ ሲሆን፣ በኮርፖሬሽኑ ለሁለት ዓመት ከስድስት ወር ገደማ ከሠሩ በኋላ የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ በመሆን በጥቅምት 2015 ዓ.ም. ተሹመዋል።
ሳንዶካን በፕላን እና ልማት ሚኒስቴር የነበራቸው ኃላፊነት፤ በአካባቢ ጥበቃ፣ በአየር ንብረት እና በሥነ ሕዝብ ጉዳዮች ላይ "ፖለቲካዊ አመራር" መስጠት መሆኑን በወቅቱ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረው ነበር።
ሳንዶካን በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በነበራቸው ቆይታ የአየር ንብረትን በተመለከቱ ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎች ላይ ኢትዮጵያን በመወከል በተደጋጋሚ ተገኝተዋል።
ከዚያ በመቀጠል ጥቅምት 2016 ዓ.ም. በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል።
አቶ ሳንዶካን የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊነትን ጨምሮ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ላለፉት 14 ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ደግሞ በአራት ከፍተኛ የመንግሥት ሹመቶች ላይ ተመድበው ሠርተዋል።
የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኮሚሽን ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን "ለሰላማዊ መንገድ" ለመጠቀም የምታደርገውን ጥረት "የመምራት እና የማስተባበር ኃላፊነት" ተጥሎበታል።
ኢትዮጵያ የኒውክሌየር ኃይልን ለኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት፣ ለኢንዱስትሪ ልማት፣ ለምግብ ዋስትና፣ ለጤና አገልግሎት፣ ለሳይንስ እና ምርምር ዘርፎች ለመጠቀም እንዳቀደች የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ዛሬ ያወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በ30 ቢሊዮን ዶላር ሊገነባ ካቀዳቸው "ግዙፍ ፕሮጀክቶች" መካከል አንዱ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሕዳሴ ግድብ በተመረቀበት ጊዜ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫውን ለመገንባት መስከረም 15/2018 ዓ.ም ከሩሲያ ጋር ስምምነት ተፈራርማለች።
ስምምነቱ የተፈረመው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዓለም የአውቶሚክ ፎረም ላይ ለመሳተፍ ወደ ሩሲያ አቅንተው ከፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ከተገናኙ በኋላ ነው።
በአፍሪካ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ያላት አገር ደቡብ አፍሪካ ስትሆን፣ ጥቂት የአፍሪካ አገራት የኃይል ማመንጫውን በመገንባት ላይ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያም ይህንን የኃይል ምንጭ ለመጠቀም ዕቅድ ከያዘች ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ እንደምትገነባ ያሳወቀችው በቅርቡ ሲሆን አሁን ደግሞ ሥራውን የሚመራ የመጀመሪያውን መንግሥታዊ ተቋም አቋቁማለች።
አቶ ሳንዶካን ደበበም የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መሾማቸው ተገልጿል።















