የሚድሮክ ኩዊንስ ሱፐርማርኬቶች ስያሜያቸውን ወደ ዓለም አቀፉ ኩባንያ "ካርፉር" ሊቀይሩ ነው

የፎቶው ባለመብት, MIDROC Investment Group
ግዙፉ ዓለም አቀፍ የሱፐርማርኬት ኩባንያ ካርፉር፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት የሚያስችለውን ስምምነት ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር መፈጸሙን አስታወቀ።
በሁለቱ ተቋማት ስምምምነት መሠረት በሚድሮክ የሚተዳደሩት የኩዊንስ ሱፐርማርኬት ቅርንጫፎች በሙሉ ስያሜያቸውን እና የንግድ ምልክታቸውን ወደ "ካርፉር" እንደሚቀይሩ ተገልጿል።
ሱፐርማርኬቶችን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ከ12 ሺህ በላይ መደብሮች ያሉት የፈረንሳዩ ካርፉር፤ ወደ ኢትዮጵያ መግባት የሚያስችለውን ስምምነት መፈጸሙን ያስታወቀው ሰኞ ታኅሣሥ 17/2018 ዓ.ም. ምሽት ባወጣው መግለጫ ነው።
የኩባንያው መግለጫ እንደሚያስተዳው ከሚድሮክ ጋር የተደረገው ስምምነት "የፍራንቻይዝ እና የአቅርቦት አጋርነትን" የተመለከተ ነው። በዚህም መሠረት ሚድሮክ ሚያስተዳድራቸውን የኩዊንስ ሱፐርማርኬቶች ስያሜ "በሙሉ ወደ ካርፉር እንዲቀየር" ያደርጋል።
ሚድሮክ የካርፉርን "የንግድ ስያሜ፣ ሙያዊ ልምዶች እና ምርቶች ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚያሠራጭ" መግለጫው ያስረዳል። "የመጀመሪያዎቹ መደብሮች እስከ 2026 የመጀመሪያ አጋማሽ ድረስ የንግድ ስያሜያቸውን ይቀይራሉ" ሲልም እስከ ሰኔ 2018 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ሥራ እንደሚጀምሩ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ካርፎር ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን አስመልክቶ ዛሬ ፌስቡክ ገጹ ባወጣው አጭር መረጃም "በ2026 አጋማሽ ጀምሮ የመጀመሪያዎቹ ስያሜያቸውን ወደ ካርፉር የሚቀይሩ ነባር የኩዊንስ ሱፐርማርኬቶች አገልግሎት መስጠት የሚጀምሩ ይሆናል" ብሏል።
በግዙፉ ሚድሮክ ስር ከሚገኙ በርካታ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ኩዊንስ ሱፐርማርኬት የመጀመሪያ መደብሩን የከፈተው ከስምንት ዓመት በፊት በ2010 ዓ.ም. ነበር። በአሁኑ ሰዓት ኩዊንስ ሱፐርማርኬት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 13 ቅርንጫፎች አሉት።
የሁለቱ አካላት ስምምነት ያሉትን የኩዊንስን ሱፐርማርኬቶች ስያሜ ከመቀየር ባሻገር አዲስ ቅርንጫፎችን መክፈትንም እንደሚያካትት የካርፉር የዓለም አቀፍ አጋርነት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፓርትሪክ ላስፈርጉስ እንደተናገሩ በመግለጫው ላይ ሰፍሯል።
"አሁን ያሉትን 13 ሱቆች በፍጥነት ከመለወጥ ባለፈ፤ የሚድሮክ እና የካርፉር ኢንተርናሽናል አጋርነት ቡድኖች በሀገሪቱ ያለንን ተግባራት ወደፊት ለማሳደግ እጅ እና ጓንት ሆነው እየሠሩ ይገኛሉ። እስከ 2028 ድረስ ተጨማሪ 17 ሱቆችን ለመክፈት አቅደናል" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"በኢትዮጵያ የችርቻሮ ንግድ ቀዳሚ ተዋናይ" ከሆነው ሚድሮክ ጋር የተደረሰው ስምምነት እንዳስደሰታቸው የገለጹት ፓትሪክ፤ ኩባንያው ለያዘው "የዓለም አቀፍ ፍራንቻይዝ ማስፋፋት ስትራቴጂ ወሳኝ ምዕራፍ" እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የሚድሮን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው፤ "ከመላው የሚድሮክ ቡድን ጋር በመሆን ወደ ካርፉር ዓለም አቀፍ የፍራንቻይዝ መረብ መቀላቀላችንን ሳበስር በታላቅ ኩራት ነው" እንዳሉ መግለጫው ያስረዳል።
ስምምነቱ ሚድሮክ ስለ ኢትዮጵያ ገበያ ያለውን "ጥልቅ ዕውቀት፣ የሚድሮክ ቡድን አባላትን ቁርጠኝነት እና የካርፉርን ምርጥ ተሞክሮዎች" አጣምሮ ለመጠቀም እንደሚያስችል አቶ ጀማል ተናግረዋል።
እነዚህን በመጠቀም "ለኢትዮጵያውያን ደንበኞች ጥራት ያላቸው እና ተመጣጣኝ ምርቶችን እንዲሁም ፍላጎታቸውን በትክክል የሚያሟላ አገልግሎት ማቅረብ እንችላለን" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በበኩሉ የካርፉር እና ሚድሮክ ስምምነት "በኢትዮጵያ የችርቻሮ ንግድ ዘርፍ ላይ ከፍተኛ መነቃቃትን እንደሚፈጥር እና ለተጠቃሚዎች ሰፊ አማራጭን ይዞ እንደሚመጣ ይጠበቃል" ሲል አሞካሽቷል።
ካርፉር ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት የሚያስችለውን ስምምነት መፈጸሙን ይፋ ከማድረጉ አስቀድሞ በኅዳር መጀመሪያ የኩባንያው አመራሮች ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከኢንቨስትመንት ኮሚሽኑ ዶ/ር ዘለቀ ተመስገን ጋር ተወያይተው ነበር።
ውይይቱ ካርፉር "ኢትዮጵያ ውስጥ በጅምላ እና በችርቻሮ ንግድ ላይ በሚሳተፍበት ሁኔታ ላይ" ያተኮረ እንደነበር ኮሚሽኑ በወቅቱ ገልጾ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, MIDROC Investment Group
ካርፉር ወደ ኢትዮጵያ መግባት የቻለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት፤ ለኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ብቻ ክፍት ሆነው የቆዩት የጅምላ እና ችርቻሮ ንግድ ዘርፎች ላይ የውጭ ሀገር ባለሀብቶችም እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል መመሪያ በመጋቢት 2016 ዓ.ም. በማውጣቱ ነው።
ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት የወጣው መመሪያ በኢትዮጵያ የችርቻሮ ንግድ ላይ መሰማራት ለሚፈልጉ የውጭ ባለሀብቶች ጠንካራ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጦ ነበር። የውጭ ባለሀብቶች የችርቻሮ ንግድ ፈቃድ ለማግኘት አምስት ሱፐርማርኬት ወይም ሁለት ሀይፐርማርኬት ለመክፈት መስማማት ነበረባቸው።
ይህ መመሪያው ከወጣ አንድ ዓመት በኋላም በእነዚህ ዘርፎች ለመሰማራት ፈቃድ ያገኘ የውጭ ባለሀብት ስለመኖሩ በይፋ ሳይገለጽ ቆይቷል።
በዚህ መልኩ የተላለፈው ውሳኔ ባለሀብቶችን ለመሳብ "በቂ እንዳልሆነ" የተረዳው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ፤ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች አንስቷል።
የውጭ ባለሀብቶች የችርቻሮ ንግድ ፈቃድ ለማግኘት ሱፐርማርኬት ወይም ሀይፐርማርኬቶችን እንዲከፍቱ የተቀመጠው ቅድመ ሁኔታ "ቢያንስ 2.5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ካፒታል" እንዲያስመዘግቡ በሚል ተቀይሯል።















