ሩሲያ ፖላንድ ላይ ተፈጽሞ ሁለት ሰዎች በገደለው የሚሳኤል ጥቃት ውስጥ እጄ የለበትም አለች

ፍንዳታ ያገጠመበት ስፍራ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሞስኮ ፖላንድ መንደር ውስጥ ለወደቁት ሚሳኤሎች ኃላፊነት አልወስድም አለች።

ትላንት ማክሰኞ ምሽት ለዩክሬን ድንበር ቅርብ በሆነች የፖላንድ መንደር ውስጥ ሁለት ሚሳኤሎች መተኮሳቸውን ተከትሎ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ውጥረት በተለይም በምዕራባዊያኑ አገራት መሪዎች ዘንድ ተከስቷል።

ፖላንድ ሩሲያ ሰራሽ ሚሳኤሎች ሁለት ሲቪሎችን ገድለዋል ብላለች።

በቡድን 20 አገራት ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ በኢንዶኔዢያዋ ደሴት ባሊ የሚገኙት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፣ በፖላንድ ላይ የተከፈተው ጥቃት ከሩሲያ የመሰንዘር ዕድሉ አነስተኛ መሆኑን ገልጸው ነበር።

ፕሬዝዳንቱ የመጀመሪያ ደረጃ መረጃዎች ጥቃቱ በእርግጥም ''ከሩሲያ በተተኮሰ ሚሳኤል ተፈጽሟል'' የሚለውን ሐሳብ ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው ብለዋል።

ሩሲያ የቀረበባትን ክስ ያስተባበለች ሲሆን ''ሩሲያ በዩክሬን እና በፖላንድ ድንበር ላይ ምንም ዓይነት ጥቃት አልከፈተችም'' ሲሉ የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስትር ተናግረዋል።

በአገራቸው ላይ የቀረበው ክስ ''ሆነ ተብሎ ሁኔታውን ለማባባስ የተደረገ ነው'' ሲሉም ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ ሲያካሂዱ የቆዩት ጆ ባይደን ''ምርመራችንን ሙሉ በሙሉ እስከምናጠናቅቅ ብዙ መናገር አልፈልግም። ነገር ግን መስመሩን ተመልክተን ከሩሲያ የተተኮሰ የመሆነ ዕድሉ ጠባብ መሆኑን መናገር ይቻላል። ግን የምናየው ይሆናል'' ሲሉ አክለዋል።

የኔቶ አባል የሆነችው ፖላንድ ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ወዲህ በግጭቱ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ከርማለች።

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማቴውስ ሞራዊስኪ ዜጎቻቸው እንዲረጋጉ የጠየቁ ሲሆን የአገሪቱ የአየር ክልል ላይ የሚደረገው ጥበቃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የአገሪቱ ፕሬዝዳንት አንድሬ ዱዳ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ጥቃቱን የፈጸመው ማን እንደሆነ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ሆኖ ለመናገር የሚያስችል ድምዳሜ ላይ ገና መድረስ አልተቻለም።

''እስካሁን ድረስ ሚሳኤሉን ማን እንደተኮሰው የሚያሳይ የተሟላ መረጃ የለንም። ነገር ግን ሚሳኤሉ ሩሲያ ሠራሽ የመሆኑ ዕድሉ ከፍተኛ ነው። ነገር ግን ይሄ ምርመራ እየተደረገበት ያለ ጉዳይ ነው'' ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ የቡድን 7 አገራት አስቸኳይ ስብሰባ ያደረጉ ሲሆን፣ ፖላንድ የኔቶን ሕግ አንቀጽ 4 ትተገብራለች ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ አንቀጽ አንድ የኔቶ አባል አገር ጥቃት በደረሰባት ወቅት አስቸኳይ የኔቶ አምባሳደሮች ስብሰባን የመጥራት መብትን ይሰጣታል።

በስብሰባውም አገሪቱ ሉአላዊነት፣ ፖለቲካዊ ነጻነቷ ብሎም ደኅንነቷ መጣስ አለመጣሱን የተመለከተ ውይይት ይደረጋል።

ፕሬዘዳንት ባይደን ከውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን እና ከደህንነት አማካሪያቸው ጋር አስቸኳይ ስብሰባ ሲመሩ

የፎቶው ባለመብት, White House

የምስሉ መግለጫ, የኔቶ አባል አገር በሆነችው ፖላንድ ያጋጠመው ፍንዳታ ከፍተኛ ውጥረትን አስከትሏል።

ከዚህ ቀደም በኔቶ ውስጥ የአዳዲስ የፀጥታ ስጋቶች ጉዳዮች ምክትል ረዳት ፀሐፊ የነበሩት ዶክተር ጃሜ ሺያ እንደሚሉት ፖላንድ አንቀጽ 4ን በመተግበር ረቡዕ ስብሰባውን ልትጠራ ትችላለች።

ነገር ግን ባትጠራ እንኳን የኔቶ ዋና ፀሐፊ የኔቶ አምባሳደሮችን ወዲያውኑ ሊሰበስቡ ይችላሉ ያሉ ሲሆን፤ ይህ ግን አሁን በተከሰተው ፍንዳታ የመሆን ዕድሉ ዝቅተኛ ነው ብለዋል።

የኔቶ አባል አገራት ጉዳዩን በከፍተኛ ትኩረት እየተከታተሉት ሲሆን በርካቶች የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ እንዳያደርገው ስጋት ውስጥ ገብተዋል።

የፈረንሳይ የፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ረቡዕ ጠዋት በሰጠው መግለጫ የሚሳኤሉ መነሻ ''በጥንቃቄ መታየት አለበት'' ሲል አሳስቧል።

''በርካታ የቀጠናው አገራት እንዲህ አይነት መሣሪያ ያላቸው ሲሆን መሣሪያውን መለየት የግድ የተኮሰውን አገር መለየት ማለት ላይሆን ይችላል'' ሲል መግለጫው አትቷል።

''ከፍተኛ የግጭት መባባስ'' እንዳይፈጠርም ፈረንሳይ አሳስባለች።