በዛምቢያ ለግርዛት የተጠለፉ 48 ታዳጊ ወንዶችን መታደግ ተቻለ

ባለስልጣናቱ በወንዶች ግርዛት ካምፕ

የፎቶው ባለመብት, Daily Mail

በዛምቢያ ለግርዛት ታፍነው የተወሰዱ 48 ታዳጊ ወንዶችን ከወንዶች የግርዛት ካምፕ መታደግ እንደተቻለ ተገለጸ።

ቤተሰቦቻቸው ልጆቻችን በግዳጅ ተወስደዋል የሚል ክስ አቅርበው ነበር።

ከነዚህም ውስጥ አንደኛው ታዳጊ ለሁለት ሳምንታት ያህል የኤችአይቪ መድኃኒቱን መውሰድ እንዳልቻለም ባለስልጣናቱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከ10 እስከ 17 ዓመት የሆናቸው ታዳጊ ወንዶች እስከ ስድስት ወራት ድረስ በጫካ ውስጥ ተነጥለው በመቆየት ሚስጥራዊ እና ባህላዊ ወደ ወንድነት የመሸጋገር ስርዓት ያካሂዳሉ።

የግርዛቱ ካምፕ ከሊቪንግስቶን ከተማ ወጣ ብሎ በአንድ የብሔራዊ የዱር አራዊት ፓርክ አቅራቢያ በህገ ወጥ መንገድ የተቋቋመ ሲሆን ዳጊዎቹ ንጽህና በጎደለው እና በአደገኛ ሁኔታዎች ውስጥ ተይዘው እንደነበር ባለስልጣናቱ አስረድተዋል።

በአሁኑ ሰዓት ከዚህ ስፍራ መታደግ ከተቻሉት ታዳጊዎች መካከል ሶስቱ በምላጭ በመገረዛቸው ምክንያት የተፈጠረውን ችግር ለማከም ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸው ተገልጿል።

ከታዳጊዎቹ መካከል አንደኛው በተበከለ ውሃ አማካኝነት በሚተላለፈው ቢልሃርዚያ በተሰኘው በሽታ መጠቃቱንም የዛምቢያ ብሔራዊ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዘግቧል።

ከሁለት ሳምንታት በፊት የተቋቋመው ይህ ወንድነትን የማስመጀመሪያ ካምፕ መቃጠሉንም ዘገባው አስነብቧል።

እንደነዚህ ዓይነት ካምፖች የሚያቋቋሙት ግለሰቦች ሙካንዳ በመባል የሚታወቀውን ስርዓት ለመፈጸም ያልተገረዙ ወንዶችን ፍለጋ አብዛኛውን ጊዜ ትምህርት ቤቶችን ኢላማ ያደርጋሉ ተብሏል። ትክክለኛ ዕድሜ የሚሏቸውንም ታዳጊዎች ሲያገኙ ከመማሪያ ክፍልም ቢሆን በአስገዳጅ መልኩ ይወስዷቸዋል።

ግለሰቦቹ ወላጆቻቸውን የማያማክሩ ሲሆን መምህራኑንም ስለሚያስፈራሩዋቸው ምንም ማድረግ አይችሉም። አንዳንድ ታዳጊዎች በፈቃዳቸው ቢሄዱም በርካቶቹ ተገድደው እና ከባህሉ ውጭ መሆን እንደማይችሉ ይነገራቸዋል።

ይህንን ካምፕ ያቋቋመው ግለሰብ በአገሪቱ የስርዓተ ጾታ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራር በሆኑት ሜንጋ ካቢካ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸውም ተገልጿል።

ባለስልጣኗ ከወላጆች የደረሳቸውን ቅሬታ ለመመርመር ከተለያዩ ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ኃላፊዎችን ቡድን መርተው ወደ አቅራቢያው አቅንተው ነበር።

“ባህላችንን መጠበቅ እንፈልጋለን ነገር ግን ደንበችን መከተል አለብን ። እንደነዚህ አይነት ህግን የሚጻረሩ ተግባራትን መፈጸም አይቻልም” ሲሉ ተናግረዋል።

አንዳንድ ታዳጊዎች ከስፍራው ሌሊት ለማምለጥ ሲሞክሩ በቦታው ላይ በነበሩ ሰዎች አካላዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው የዛምቢያው ደይሊ ሜይል ጋዜጣ ዘግቧል።

ቤተሰቦቻቸው ልጆቻቸው በዚህ ስፍራ እንዲገኙ ፍቃዳቸውን ባይሰጡም እስከ 75 ዶላር ክፍያ እንዲፈጽሙ በስልክ እንደተጠየቁ መናገራቸው ተዘግቧል።

በዛምቢያ ምንም እንኳን የኤችአይቪንም ሆነ ሌሎች ችግሮች እንዳያመጡ በቀዶ ህክምና የሚካሄዱ የወንዶች ግርዛት በጤና ማዕከላት ቢሰጡም አንዳንድ ብሔሮች ባህላዊውን ሁኔታ ይመርጣሉ።