ሕይወታቸውን ለከባድ አደጋ አጋልጠው የሚሰደዱ ኤርትራውያን ሰቆቃ

በቱርካና ሐይቅ ላይ ፀሐይ ስትጠልቅ አንዲት እናት ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች በሚጠቀሙት አዲሱ መንገድ ኬንያ ለመድረስ ስትሞክር ሐይቁ ውስጥ የሰጠመችውን ታዳጊ ልጇን ለማስታወስ እያለቀሰች አበቦችን ወደ ሐይቁ ውሃ ትወረውራለች።

ከሦስት ዓመታት በፊት በኬንያ ጥገኝነት የጠየቀችው የጴንጤ ቆስጤ ክርስቲያን እምነት ተከታይዋ ኤርትራዊት ሰናይት መብራህቱ፣ ህያብ የተባለችው የ14 ዓመት ልጇ ባለፈው ዓመት ሕይወቷን ያጣችበትን ቦታ ለማየት ነው ወደ ሰሜን ምዕራብ ኬንያ የሄደችው።

ታዳጊዋ ከባድ ነፋስ ያለበትን ሰፊ ሐይቅ በምሽት ለማቋረጥ የሞከረችው በሕይወት ከተረፈችው ከእህቷ ጋር ነበር።

"የሰው አዘዋዋሪዎቹ ኬንያ ውስጥ እንዲህ ያለ ትልቅ እና አደገኛ ሐይቅ መኖሩን ነግረውኝ ቢሆን ኖሮ ልጄን እንትመጣ አልፈቅድም ነበረ" ስትል ሰናይት በሐይቁ ዳርቻ ላይ ተቀምጣ ለቢቢሲ ተናግራለች።

ሰናይት በኤርትራ ያለውን የሃይማኖት ጭቆና በመሸሽ ከሁለት ትናንሽ ልጆቿ ጋር ኬንያ ዋና ከተማ የገባችው በቱሪስት ቪዛ በአውሮፕላን ነበረ። ሁለቱ ሴት ልጆቿ ግን ለብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ዕድሜያቸው የተቃረበ ስለነበረ ከአገር እንዲወጡ አልተፈቀደላቸውም።

በአንድ ፓርቲ በምትተዳደረው እና በከፍተኛ ደረጃ ወታደራዊ በሆነችው ኤርትራ የግዳጅ ብሔራዊ አገልግሎት ለዓመታት ሊቆይ የሚችል ሲሆን፣ የግዳጅ የጉልበት ሥራንም ሊያካትት የሚችል ነው።

ሰናይት ወደ ኬንያ ከገባች በኋላ ታዳጊ ልጆቿ ከኤርትራ አስወጥታ ከእሷ ጋር እንዲሆኑ እንድታደርግ አጥብቀው ሲለምኗት ከዘመዶቿ ጋር ባደረገው ምክር ገንዘብ ከፍለው ከኤርትራ ማስወጣት እንደሚቻል ትሰማለች።

ከዚያም የሁለቱ ሴት ልጆች ዕጣ ፈንታ በሰው አዘዋዋሪዎች እጅ ላይ ወድቆ ከኤርትራ በእግር እና በመኪና ረጅሙን መንገድ ተጉዘው ሰሜን ኢትዮጵያ ገቡ።

በማስከተል ደግሞ ኢትዮጵያን አቋርጠው በኬንያ ሰሜናዊ ምሥራቅ ክፍል ውስጥ ወደ ሚገኘው እና በዓለም በረሃ ውስጥ ያለ ትልቁ ሐይቅ ወደ ሆነው ቱርካና ዳርቻ ደረሱ።

ኬንያ ውስጥ የምትገኝ አንዲት የሰዎች አዘዋዋሪ ሴት ለቢቢሲ እንዳረጋገጠችው ቱርካና ሐይቅ ስደተኞችን በሕገወጥ መንገድ ለማሻገር በብዛት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው።

"ይህ መስመር አዲስ በመሆኑ ምክንያት የዲጂታል መስመር እያልን ነው የምንጠራው" ብላለች።

በድብቅ ቦታ እና ስሟ በማይጠቀስበት ሁኔታ ለቢቢሲ የተናገረችው የሰው አዘዋዋሪዋ እንደምትለው አንድን ሰው ወደ ኬንያ ሲያዘዋውሩ 1,500 ዶላር ያህል ያገኛሉ፤ ይህም አንድ አማካይ ኬንያዊ ሠራተኛ በወር ከሚያገኘው አራት ዕጥፍ የሚበልጥ ነው።

ይህች ግለሰብ ላለፉት 15 ዓመታት በኬንያ፣ በኡጋንዳ፣ በሩዋንዳ እና በደቡብ አፍሪካ ያለው የግዙፍ የሰዎች ዝውውር መረብ አካል ሆና ቆይታለች። በዚህም በዋናነት ከኤርትራ፣ ከኢትዮጵያ እና ከሶማሊያ የሚሰደዱ ሰዎችን በማዘዋወር ላይ ተሰማርታለች።

ኬንያ በዋና አውራ ጎዳናዎቿ ላይ የምታደርገውን ጥበቃ በማጠናከሯ ምክንያት ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ፊታቸውን ወደ ቱርካና ሐይቅ በማዞር ስደተኞችን ወደ አገሪቱ ማስገባት ቀጠሉ።

በአዲሱ የሰዎች ዝውውር መስመር ላይ ያሉ "ወኪሎች" ስደተኞችን ወደ ናይሮቢ ለመውሰድ የመንገድ ትራንስፖርት በተዘጋጀባት ሎሜክዊ በተባለችው የኬንያ የዓሳ አስጋሪዎች መንደር ውስጥ ተቀብለው ከዚያም የ15 ሰዓታት ጉዞ ያደርጋሉ።

በተጨናነቁ የእንጨት ጀልባዎች ላይ መጓዝ የሚያስከትለውን አደጋ በማሰብ ወላጆች ልጆቻቸውን ብቻቸውን ሐይቁን እንዲያቋርጡ እንዳይፈቅዱላቸው ይህች የሰዎች አዘዋዋሪ ትመክራለች።

"የማገኘው ገንዘብ ያስደስተኛል አልልም፤ ምክንያቱም እንደ እናት በሌሎች ሴቶች ልጆች ላይ መጥፎ ነገር ሲደርስ ስመለከት ደስተኛ መሆን አልችልም" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

"ስደተኞች ከሰሙኝ መምከር እፈልጋለሁ። ከአገራቸው እንዳይወጡ ነው የምለምናቸው" ስትል የብዙዎቹ የሰው አዘዋዋሪዎችን መጥፎ አመለካከት በማንሳት አስጠንቅቃለች።

ለደኅንነቱ ሲል ትክክለኛ ስሙን መግለጽ ያልፈለገው ኤርትራዊው ኦስማን፣ ከሟቿ ህያብ እና ከእህቷ ጋር በተመሳሳይ ጊዜ ነበር ወደ ኬንያ የተሸጋገረው።

ህያብ የነበረችበት ጀልባ ዓይኑ እያየ እንዴት ሐይቁ ላይ እንደተገለበጠ ያስታውሳል።

"ህያብ ከእኛ ፊት ከነበረው ጀልባ ላይ ነበረች። የጀልባው ሞተር እየሠራ ስላልነበረ በከባድ ነፋስ እየተገፋ ሲሄድ ነበረ። ጀልባቸው ወደ ሐይቁ 300 ሜትር ያህል ከገባ በኋላ ተገልብጦ ለሰባት ሰዎች ምክንያት ሆነ።"

የህያብ እህት ሌላ የሰዎች አዘዋዋሪ ጀልባ ደርሶ እስኪያድናት ድረስ እየሰጠመች በነበረችው ጀልባ ላይ ተንጠላጥላ በሕይወት ለመትረፍ ችላለች።

ከ20 በላይ ሰዎችን በጀልባዋ ላይ አጭቀው ከመጠን በላይ በማሳፈራቸው በመጥቀስ የህያብ እናት ሰናይት ለልጇ ሞት የሰው አዘዋዋሪዎቹን ተጠያቂ ታደርጋለች።

"የልጄ ሞት የተከሰተው ገልጽ በሆነ ቸልተኝነት ምክንያት ነው። እነሱ አምስት ሰዎች እንኳን ማሳፈር በማትችለው ትንሽዬ ጀልባ ላይ በርካታ ሰዎችን ጭነው ነበር" ብላለች።

ቢቢሲ ሎሜዊኪ መንደርን በጎበኘበት ጊዜ ሁለት አሳ አስጋሪዎች የኤርትራውያን ይሆናሉ ብለው የሚያምኗቸው የስደተኞች አስከሬን በ300 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና 50 ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው ሐይቅ ላይ ሲንሳፈፉ ማየታቸውን ተናግረዋል።

"በሐይቁ ዳርቻ ላይ አራት አስከሬኖች ነበሩ። ከዚያም ከጥቂት ቀናት በኋላ ሌሎች አስከሬኖችም ወጡ" ብሏል ብራይተን ሎካሌ።

ጆሴፍ ሎሙሪያ የተባለው ሌላ ዓሳ አስጋሪ ደግሞ የሁለት ወንዶች እና የሁለት ሴቶች አስከሬን ማየቱን እና ከመካከላቸው አንዷ ደግሞ ታዳጊ መሆኗን ተንግሯል።

ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት መረጃ በመላው ዓለም ካሉ 580 ሺህ ስደተኛ እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መካከል 345 ሺዎቹ በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ እንደሚገኙ ያሳያል።

እንደ ሰናይት ቤተሰብ ሁሉ፣ በቀጣናው በበርካታ ጦርነቶች ውስጥ በምትሳተፈው፣ መንግሥት ጥብቅ ቁጥጥር በሚያደርግባት፣ ነጻ የፖለቲካ እና የሃይማኖት እንቅስቃሴ በሌለባት አገር ብዙዎች ከወታደራዊ አገልግሎት ለማምለጥ ከኤርትራ ይሰደዳሉ።

በኡጋንዳ የሚገኘው ጠበቃ ሙሉ ብርሃን ለቢቢሲ እንደተናገረው ኤርትራን በሚዋሰኑት ኢትዮጵያ እና ሱዳን ውስጥ ባሉ ግጭቶች ምክንያት ኬንያ እና ኡጋንዳ በኤርትራውያን ስደተኞች ተመራጭ መዳረሻ ሆነዋል።

ሴቷ የሰዎች አዘዋዋሪ እንደተመለከተችው አንዳንድ ስተደተኞች እዚያው ኬንያ ውስጥ መኖር ሲቀጥሉ ሌሎች ደግሞ የስደተኝነት ምዝገባ ቀላል ነው ብለው ወደሚያምኑባቸው ወደ ኡጋንዳ፣ ርዋንዳ እና ደቡብ አፍሪካ ለመሸጋገሪያነት ኬንያን ይጠቀሙባታል።

የሰዎች ዝውውር መረቡ በእነዚህ አገራት ውስጥ ሁሉ የሚንቀሳቀስ ሲሆን፣ ከአንድ አገር "ወኪል" ወደ ሌላው በማቀባበል አስከ መድረሻቸው ድረስ የተያያዘ ነው። አንዳንድ ጊዜም ይህ የሰዎች ዝውውር መረብ ከአፍሪካም ባሻገር አስከ አውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ ይደርሳል።

የሴቷ የሰዎች አዘዋዋሪ ሥራ ስደተኞችን ወደ ናይሮቢ በሚያደርጉት ጉዞ በማቀባበል እና ቀጣይ ጉዟቸው እስኪመቻች እና አስፈላጊው ክፍያን እስኪፈጽሙ ድረስ "በማቆያ ቤቶች" ማሳረፍን ያካትታል።

እስከዚያ ጊዜ ድረስም አንድ ስደተኛ ምናልባትም አስከ አምስት ሺህ ዶላር የሚደርስ ገንዘብ በመክፈል ለቀጣይ ጉዞ ደግሞ ተጨማሪ ገንዘብ ያስፈልገዋል።

ቢቢሲ በአንድ ሕንጻ ውስጥ የሚገኝ አንድ "በማቆያ ቤትነት" የሚያገለግል ቤትን አይቷል። በቤቱ ውስጥ አንድ ፍራሽ ብቻ ያለ ሲሆን አምስት ኤርትራውያን ወንዶች ተቆልፎባቸው ነበር።

በማቆያ ቤት ውስጥ ሲቀመጡ ስደተኞቹ የቤቱን ኪራይ እና ለምግባቸው ይከፍላሉ። ገንዘብ ጨርሰው በረሃብ የሞቱ ሦስት ወንዶች እና አንዲት ወጣት ሴት እንደምታውቅ በሰዎች ማዘዋወር ውስጥ የምትሳተፈው ሴት ትናገራለች።

ሰው አዘዋወሪዎቹም ክስተቱን "መጥፎ ዕድል" በማለት አቃለው አስከሬናቸውን አስወግደውታል።

በተጨማሪም "አዘዋዋሪዎቹ ለሞቿቾ ቤተሰቦች በሕይወት እንዳሉ በመንገር ገንዘብ ሲቀበሉ ቆይተዋል" በማለት ሁኔታውን አስታውሳለች።

ሴት ስደተኞች ደግሞ በአብዛኛው ወሲባዊ ጥቃት ወይም ሰው አዘዋዋሪዎቹን እንዲያገቡ ሊገደዱ የሚችሉበት ሁኔታም እንዳለ የሰዎች አዘዋዋሪዋ ተናግራለች።

ቢሆንም ግን ከፍተኛ ገንዘብ የምታገኝበትን ይህንን የሰዎች ዝውውር ሥራዋን የመተው ሃሳብ ባይኖራትም፣ ሌሎች ግን በዚህ ሂደት ውስጥ ምን እንሚጠብቃቸው ማወቅ እንዳለባቸው ታስጠነቅቃለች።

ምንም እንኳን የ14 ዓመት ልጇ ሞት ሐዘን ቢፈጥርባትም ሰናይት ሌላኘዋ ልጇ ከአደጋው ተርፋ በአዘዋዋሪዎቹም ጉዳት ሳይረደርስባት በመትረፏ መጽናኛ ሆኖላታል።

"ሁሉም ኤርትራዊ ቤተሰብ እያለፈበት ባለው ሁኔታ ውስጥ ነው ያለፍነው" ትላለች ሰናይት።

"ፈጣሪ አገራችንን ጠብቆ፣ ከዚህ ሁሉ ችግር ያውጣን።"