ኤልክላሲኮ፡ ሪያል ማድሪድ ‘ሊረሳው በሚገባው 30 ደቂቃ’ 4 ግቦች ተቆጥረውበት በባርሴሎና ተሸነፈ

ሌዋንዶውስኪ እና የቡድን አጋሮቹ ደስታቸውን ሲገልጹ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በጉጉት ሲጠበቅ በነበረው የኤል ክላሲኮ ፍልሚያ ባርሴሎና 4 ለምንም ሪያል ማድሪደን በመርታት በስድስት ነጥብ ልዩነት ሊጉን መምራት ጀመረ።

ማድሪዶች ያለመሸነፍ ክብረ ወሰናቸውን ወደ 43 ጨዋታዎች ለማሳደግ ወደ ሜዳ ቢገቡም በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ በቤርናባው ክፉኛ ለመደቆስ ተገደዋል።

“ከበርካታ ያለመሸነፍ ጉዞዎች በኋላ በዚህ መልኩ መሸነፍ ከባድ ነው” ሲሉ የማድሪዱ አሠልጣኝ ካርሎ አንቼሎቲ ተናግረዋል።

የሁለቱ ኃያላን ቡድኖች የመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታ ያለምንም ግብ ተጠናቋል።

በ54ኛው ደቂቃ እንግዶቹ በአጥቂው ሮበርት ሌዋንዶሰውስኪ ጎል ቀዳሚ ሆኑ።

ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ፖላንዳዊው አጥቂ ሁለተኛ ግቡን በማስቆጠር የባርሴሎናን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አደረገ።

አጥቂው ሃትሪክ ሊሠራባቸው የሚችልባቸውን ሁለት ኳሶችን ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል።

ስፔናዊው ላሚን ያማል ለባርሴሎና ሦስተኛውን ግብ ከማስቆጠር ባለፈ በ17 ዓመቱ በኤልክላሲኮ ጨዋታ ላይ ኳስ እና መረብ ያገናኘ በዕድሜ ትንሹ ተጫዋች ለመባልም በቅቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ብራዚላዊው ራፊንሃ ደግሞ አራተኛው ግብ ከመረብ አሳርፏል።

ፈረንሳዊው አጥቂ ክሊያን ምባፔ በመጀመሪያው የኤልክላሲኮ ፍልሚያ ሽንፈት ያስተናገደ ሲሆን፣ ሁለት ከመረብ ያሳረፋቸው ኳሶች ደግሞ ከጨዋታ ውጪ ተብለው ተሰርዘዋል። የባርሴሎናው ግብ ጠባቂ ኢናኪም ተደጋጋሚ ሙከራዎችን አጨናግፎበታል።

ባለፈው ዓመት ከሪያል ማድሪድ በ10 ነጥብ ርቆ የጨረሰው ባርሴሎና እምነቱን በወጣት ተጫዋቾች ላይ በመጣል ውድድር ዓመቱን ጀምሯል።

ዘንድሮ 10 ጨዋታዎችን በማሸነፍ በአንድ ጨዋታ ብቻ መሸነፋቸው የሃንሲ ፍሊክ ቡድን በትክክለኛ መስመር ላይ መሆኑን እያሳየ ነው።

ከወጣቶቹ ያማል ኮከቡ ቢሆንም ትላንት ምሽት ለጎል የሚሆን ኳስ ያቀበሉት ካሳዶ እና ባልዴም በድንቅ አቋም ላይ ይገኛሉ።

በቋሚ አሰላለፍ ወደ ሜዳ ከገቡት ተጫዋቾች ስድስቱ የባርሴሎና አካዳሚ ውጤቶች ሲሆኑ የቡድኑን የአጥቂ መስመር የሚመራው ደግሞ አንጋፋው ሮበርት ሌዋንዶውስኪ ነው።

የ36 ዓመቱ አጥቂ በዘንድሮው ዓመት 11 የላሊጋ ጨዋታዎች 14 ግቦችን አስቆጥሯል።

ወጣቶችን ልምድ ካላቸው ጋር አቀናጅቶ ወደ ሜዳ የገባው የካታሎኑ ቡድን በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ማድሪድን በቀላሉ እጅ ሊያሰጥ ችሏል።

እንግዳው ቡድን ወደ ፊት ጠጋ ብሎ በመጫወት ማድሪዶች በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

“የኋላ መስመራችንን ወደ ፊት ጠጋ አድርገን እንጫወታለን። አደገኛ ቢመስምልም ግን አደገኛ አይደለም” ብለዋል አሠልጣኝ ፍሊክ።

ፒኤስጂ እያለ በተደጋጋሚ ባርሴሎና ላይ ግቦችን ማስቆጠር የቻለው ምባፔ በትላንት ምሽቱ የኤልክላሲኮ ጨዋታከባድ ምስት ለማሳለፍ ተገዷል።

በተደጋጋሚ የጨዋታ ውጭ መስመር ጥሶ ለመግባት ያደረገው ሙከራ ሳይሳካለት ቀርቷል።

በሊጉ ስድስት ግቦችን ከማስቆጠሩም በላይ በመጀመሪያዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ምንም ኳስ ከመረብ አለማገናኘቱ ፈረንሳዊው በስፔን የጠበቀውን ዓይነት አጀማመር እንዳላሳየ ያመለክታል።

ባለፈው ዓመት በላሊጋው 19 ግቦችን ያስቆጠረው እንግሊዛዊው ጁድ ቤሊንግሃም ዘንድሮ ደካማ ከመሆኑም በላይ አንድም ጎል ማስቆጠር አልቻለም።

“በመጀመሪያው አጋማሽ በጥሩ ሁኔታ ተጫውተናል። ግን ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች አልተጠቀምንም” ብለዋል አንቼሎቲ።

“ለ60 ደቂቃ ያህል ተፎካከርናል። የመጨረሻውን 30 ደቂቃ ግን መርሳት ይኖርብናል” ሲሉ አክለዋል።