ሳልማን ሩሺዲ በስለት ከተወጉ በኋላ የመጀመሪያ መፅሐፋቸውን ሊያወጡ ነው

ሳልማን ሩሺዲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

'ዘ ሳታኒክ ቨርስስ' በሚባለው መጽሃፋቸው ዝናን ያተረፉት ታዋቂው ፀሐፊ ሰር ሳልማን ሩሺዲ ከሦስት ዓመት በፊት በስለት ተወግተው በአንድ ዐይናቸው ብርሃኑን ካጡ በኋላ የመጀመሪያቸውን ልብወለድ መፅሐፍ ለአንባቢዎች ሊያደርሱ ነው።

11ኛው ሰዓት የተሰኘው መፅሐፍ ህንድ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ ላይ መቼቱን የሚያደርግ እና ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ታሪኮችን የያዘ ነው።

አዲሱ መፅሐፍ በመድረክ ላይ ሳሉ ጥቃት ከደረሰባቸው ከሦስት ዓመታት በኋላ ፔንጉዊን ራንደም ሀውስ በተባለ አሳታሚ ድርጅት መጪው ኅዳር ወር ይታተማል።

በስለት ጥቃት ያደረሰባቸው አጥቂ በግድያ ሙከራ ባለፈው ወር ነበር 30 ዓመት እስራት የተፈረደበት።

"ሳልማን ሩሺዲ አዲሱ ልብወለድ ባደጉባቸው፣ በኖሩባቸው፣ በጎበኟቸው እና በተሰናበቷቸው ስፍራዎችን የሚዳስስ ነው" ብሏል አሳታሚው።

ፔንጉዊን ራንደም ሀውስ መፅሐፉ በህንድ ሁለት ጠበኛ የሆኑ ሽማግሌዎች የገጠማቸውን ሀዘን የሚዳስስ እንደሆነ ገልጿል።

የሰር ሰልማን ስራ የሆነውን 'ሚድናይትስ ችልድረን' የተባለውን እና ያሸለማቸውን መፅሐፍ ለሚያውቁ አንባቢዎች ቀጣዩ መፅሐፋቸውም በትዳሩ ደስታ የራቀው አስማተኛው ሙዚቀኛ የሚኖሩበትን የቦምቤይ መኖሪያ መንደርን ዳግም ይጎበኛል።

ደራሲው እንዳሉት መፅሐፉ ባለፉት 12 ወራት የተፃፈ እና ሦስት አጫጭር ታሪኮችን ያያዘ ነው።

ታሪኮቹ በአዕምሯቸው የሚመላለሱ ጭብጦች እና አካባቢዎችን የሚቃኝ እንደሆነም ደራሲው አክለው ተናግረዋል።

"ሞት፣ ቦምቤ፣ ስንብት፣ ኢንግላንድ (በተለይም ኬምብሪጅ)፣ ንዴት፣ ቁጣ፣ ሰላም፣ አሜሪካ እና ጎይ. . ." የደመቀ ነው።

የሳልማን ሩሺዲ አዲስ መፅሐፍ ዜና የመጣው በአንድ የሁነት መድረክ ላይ በስለት ሲወጉ ምን እንደተፈጠረ የሚተርኩበት ግለ ታሪካቸው ባለፈው ዓመት ከወጣ በኋላ ነው።

ነሐሴ 2022 ላይ የደረሰባቸው ጥቃት በአንድ ዐይናቸው ብርሃን እንዲያጡ ያደረገ እና ለከባድ ጉዳት የዳረጋቸው ሲሆን፤ ጉበታቸው እና እጃቸው ላይም የነርቭ ጉዳት ገጥሟቸዋል።

የ77 ዓመቱ ደራሲ እ.አ.አ 1988 'ዘ ሳታኒክ ቨርስስ' የተሰኘ በነብዩ መሐመድ ሕይወት ላይ የተመሰረተ ልብወለድ መፃፋቸውን ተከትሎ በሕይወታቸው ላይ ዛቻ በመድረሱ ተደብቀው ዓመታትን አሳልፈዋል።

ይህ መፅሐፍ በወጣ በዓመቱ የኢራን ታላቅ መሪ አያቶላ ኾሚኒ ሳልማን ሩሺዲ የሞት ፍርድ እንዲፈርድባቸው ጥሪ አቅርበው ነበር።

የህንድ እና ብሪታኒያ ዜግነት ያላቸው ፀሐፊው ከ16 በላይ መፅሐፍቶችን ፅፈዋል።