በናይጄሪያ ከ280 በላይ ተማሪዎች በታጣቂዎች ታገቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በናይጄሪያ ሰሜን ምዕራብ ክፍል ውስጥ በምትገኘው ኩሪጋ ከተማ ከ280 በላይ ተማሪዎች በታጠቁ ኃይሎች ታግተው መወሰዳቸውን የአገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ።
አንድ የዐይን እማኝ እንደተናገሩት ተማሪዎቹ ከመታገታቸው በፊት ከመማሪያ ክፍል ውጪ አንድ ላይ ተሰባስበው ነበር። በቅጽበት ግን የታጠቁ ኃይሎች በሞተር ሳይክል ወደ ግቢው በመግባት ከበባ ፈጽመው ወስደዋቸዋል።
ታጋቾቹ ዕድሜያቸው ከስምንት እስከ 15 ዓመት የሚደርስ ሲሆን፣ አሰስተማሪዎቻቸውም አብረው የእገታው ሰለባ መሆናቸው ተነግሯል።
በናይጄሪያ የታጠቁ ወንበዴዎች በተለይ በአገሪቱ ሰሜን ምዕራብ አካባቢ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አግተዋል።
እስከዚህ ሳምንት ድረስ ግን ቢያንስ በሕጻናት ላይ የሚደርሰው እገታ በአንጻሩ ቀንሶ ነበር።
የተፈጸመው እገታ በአካባቢው ባለሥልጣናት የተረጋገጠ ሲሆን፣ እንደ ባለስልጣናቱ ገለጻ ከሆነ 187 ተማሪዎች ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ 125 ተማሪዎች ደግሞ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መጠለፋቸውን ገልጻዋል።
ከእነዚህ መካከል 25 የሚሆኑት ተማሪዎች ከእገታ አምልጠው መመለሳቸውን ባለሥልጣኑ አሳውቀዋል።
የዐይን እማኙ ደግሞ ጥቃቱ ሲፈጸም አንዲት ተማሪን ተኩሰው የመቷት ሲሆን፣ አሁን በአቅራቢያ በሚገኝ ሆስፒታል የሕክምና ክትትል እያደረገች ነው።
እገታውን ለመከላከል ሙከራ ሲያደርጉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ እና አንድ መምህር በታጣቂዎቹ በተተኮሰ ጥይት ተገድለዋል ተብሏል።
እገታውን ተከትሎ የመንግሥት ኃይሎች ተማሪዎቹን ለማስለቀቅ ወዲያውኑ ዘመቻ ጀምረዋል።
“አንድም ልጅ ታግቶ አይቀርም” በማለት መንግሥት ለወላጆች ቃል ገብቷል። ባለፈው ጥር ወር በዚሁ ትምህርት ቤት ታጣቂዎች ርዕሰ መምህሩን ገድለው ሚስቱን አግተው ወስደዋል።
በተመሳሳይ ከቀናት በፊት በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ ለእንጨት ለቀማ የወጡ ሴቶች ሳይመለሱ ቀርተዋል። ምናልባትም በቦኮሃራም ታግተው ሊሆን ይችላል የሚል ስጋትም አጭሯል።
በእርግጥ ሁለቱ እገታዎች የሚያገናኛቸው ነገር የለም።
በሰሜን ምዕራብ የሚገኙት ታጣቂዎች ከሰሜን ምሥራቅ የቦኮሃራም ቡድን የተነጠሉ ቢሆኑም፣ ምናልባት በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ግን አብረው ሊሠሩ ይችሉ ይሆናል የሚል ጥርጣሬ አለ።
ሐሙስ ዕለት የተፈጸመው እገታ አንሳሩ በሚባል ቡድን የተፈጸመ ሲሆን፣ ይህ ቡድን ከቦኮሃራም የተገነጠለ እና በፈረንጆቹ 2014 በቺቦክ ግዛት ከ200 በላይ ሴት ተማሪዎችን ያገተ ነው።
ዳጎስ ያለ ገቢ ለሚያስገኘው የጠለፋ ተግባር ለማስለቀቂያነት ክፍያ መፈጸም ወንጀል መሆኑን የሚደነግግ አወዛጋቢ ሕግ በ2022 በናይጄሪያ ጸድቋል።
እስካሁን ማንም ተቀጥቶ ባያውቅም ሕጉ እስከ 15 ዓመት ያሳስራል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ ሴቶች በዋና ከተማዋ አቡጃ ታግተው ፖሊስ ሊያስለቅቃቸው ባለመቻሉ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ክፍያውን መፈጸማቸውን ገልጸዋል።












