የ24 ዓመቷ አስክሬን ገናዥ የዕለት ውሎ

የ24 ዓመቷ ወጣት እንግሊዛዊት ቀኗን የምታሳልፈው በእስከሬን ተከባ ነው።
ኢሳቤላ ዋልተን በሞት የተለዩትን “ለመጨረሻ ስንብታቸው ማዘጋጀት ኩራት የሚሰጠኝ ስራ” ነው ትላለች።
ኢሳቤላ ገናዥ ናት። የሟች ፊት ሳይገረጣ፤ አስክሬንን በኬሚካል በማድረቅ ግብዓተ መሬት እስኪፈጸም ሰውነት ሳይፈርስ እንዲቆይ ታደርጋለች።
ቀኗን የምታሳልፈበት የአስከሬን ማቆያ ክፍል በሚሰነፍጥ የኬሚካል ሽታ ተሞልቷል። “. . . ሰዎች የኬሚካሉ ሽታ ይረብሻቸዋል። እኔ ግን ለምጄዋለሁ ምንም አይሸተኝም” ትላለች።
አስከሬን መገነዝ እና በኬሚካል አድርቆ ማቆየት ለ24 ዓመት ወጣት ሴት የተተወ ስራ አይመስልም። እርሷም በዚህ ኢንዱስትሪ የተሞሉት በዕድሜ የገፉ ወንዶች ስለሆኑ ሰዎች በእኔ ስራ ይገራማሉ ትላለች።
ኢሳቤላ ባለፉት አራት ዓመታት ኖቲንግሃም ከተማ በሚገኝ የአስከሬን ማቆያ ቤት በተለያዩ ኃላፊነቶች ስትሰራ ቆይታ አሁን ላይ የአስከሬን ማቆያ ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆናለች።
ኢሳቤላ ስራውን እንደምትወደው ትናገራለች። ቤተሰቦቿም ሁሌም እንደሚደግፏት ትገልጻለች። ጓደኞቿ ግን ሁሌም በምትሰራው ስራ በግራ መጋባት ስሜት መደነቀቻው እንደቀጠለ እንደሆነ ታስረዳለች።
ይህ የአስከሬን ማቆያ ቤት እስከ 80 ሬሳ የመያዝ አቅም አለው። በአማካኝ አንድ አስክሬን እስከ ቀብሩ ድረስ ከ15-20 ቀናት በአስከሬን ማቆያ ቤቱ ይቀመጣል።

ኢሳቤላ ዋትሰን እንደምትለው ብዙ ሰዎች ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ እስከ ቀብራቸው ድረስ በሬሳ ሳጥን ውስጥ ወይም ፍሪጅ ውስጥ ዝም ብለው እንዲቀመጡ እንደሚደረጉ ያስባሉ ትላለች።
እርሷ ግን እንምትለው አስክሬኑ እርሷ ጋር በሚቆይበት ጊዜ የአስክሬኑን ገላ ታጥባለች፣ ጸጉር ታበጥራለች ወይም ትላጫለች፣ ልብስ ታለብሳለች እንዲሁም ሜካፕ ትሰራለች።
በቀብር ወቅት እና ከቀብር በፊት የሟች ቤተሰብ አባላት በሞት ካጧቸው ጋር ጊዜ እንዲያሳልፉ አድርጋለሁ ትላለች።
በሟች ቤተሰብ ፍላጎት እና አቅም የሚመሰረት ሆኖ አንድ አስክሬን ሳይበላሽ እና በሕይወት ያለ ሰውነት እንዲመስል አድርጎ ማቆየት የሚያስችል አገልግሎት እንደሚሰጡም ኢሳቤላ ትገልጻለች።
በተለይ ደግሞ ትላለች ኢሳቤላ፤ በቀብር ስነ-ስርዓት ወቅት የሬሳ ሳጥኑ የላይኛው ክፍል ክፍት የሚሆን ከሆነ አስክሬኑ ሳይበላሽ ማቆየት የግድ ይላል።
“ስራዬም የማከናውነው ረዥም ሰዓት በመውሰድ እንዲሁም ብዙ ጥረት በማድረግ ነው። ሰዎች ለአስከሬን ምን ያክል እንክብካቤ እንደሚደረግ የሚያውቁ አይመስለኝም” በማለት የሥራዋን ሁኔታ ታስረዳለች።
እንደ ኢሳቤላ ከሆነ አንድ አስከሬን ወደ የሬሳ ማቆያ ቤቱ ከመጣ በኋላ ሙሉ ሰውነቱ ይጸዳል። አፍ ንፋስ እንዳይስገባ በስውር ይሰፋል። ከሰውነት አካላት ውስጥ ፈሳሽ እና ጋዝ ተመጥጦ ይወጣ እና በአስክሬን ማድረቂያ ፈሳሾች ይተካል።

አንዳንድ ጊዜ በከባድ አደጋ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች አስከሬን ሲመጣላት የሰውነት አካል መልሶ የመጠገን ስራ እንደምትሰራም ጭምር ኢሳቤላ ትገልጻለች።
ሰም እና ልዩ የሆኑ የመዋቢያ ግብዓቶችን በመጠቀም የተጎዱ አካላትን ለዓይን እይታ ሙሉ መስለው እንዲታዩ እንምትጠግን ትገልጻለች።
እንደ ኢሳቤላ ዋትሰን ከሆነ ከኅዳር እስከ መጋቢት ባሉት ወራት ሕይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር ስለሚበዛ የስራ ጫና እንዳለባት ገልጸ፤ በቀን ከሦስት እስከ አራት አስከሬኖችን እንደምትገንዝ ትገልጻለች።
የሥራዋን ሁኔታ ስትገልጽ በአስከሬን ማቆያ ቤቱ መስኮት የለም። ቀኑን ሙሉ የጸሐይ ብርሃን ልትመለከት የምትችለው ለቡና እረፍት ስትወጣ ብቻ እንደሆነ ትገልጻለች።
ከዚህ በተጨማሪ ከሐንዘተኛ ቤተሰብ ጋር ዘወትር መገናኘት ስሜት የሚረብሽ ስሜት እንደሚፈጥር ታምናለች። ግን ትኩረቴ ሁልግዜም ሙያዬ ላይ እና በምስጠው አገልግሎት ላይ ነው ትላለች።












