አዲሱ የላይቤሪያ ፕሬዝደንት ቃለ-መሐላ ከፈፀሙ በኋላ ንግግራቸውን መጨረስ ተሳናቸው

አዲሱ የላይቤሪያ ፕሬዝደንት ጆሴፍ ቦአካይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አዲሱ የላይቤሪያ ፕሬዝደንት ጆሴፍ ባአካይ ቃለ-መሐላ በሚፈፅሙበት ቀን ንግግራቸውን መጨረስ ተስኗቸው በሌሎች እርዳታ ከአትሮነስ እንዲገለሉ ተደርገዋል።

የ79 ዓመቱ ቦአካይ ለ30 ደቂቃ ያክል ንግግር ካደረጉ በኋላ ነው ንግግራቸውን መቀጠል እንደማይችሉ ፊታቸው ላይ ምልክት ብቅ ማለት የጀመረው።

ሁለት ጊዜ ንግግራቸውን መቀጠል ፈልገው ያልተሳካላቸው አዲሱ ተመራጭ የቃለ-መሐላ ሥነ-ሥርዓታቸው ለደቂቃዎች ሊረበሽ ግድ ሆኗል።

ከሀገሪቱ እየወጡ ያሉ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት ሰውየው በወቅቱ በነበረው ከ30 ዲግሪ ሴልሲየስ የሆነ ሙቀት ምክንያት ድካም ተሰምቷቸው ነበር።

ማሕበራዊ ሚድያ ላይ የተሰራጬ ቪዲዮዎች አንድ ግለሰብ ፊታቸው ላይ ወረቀት እያራገበ ከሙቀት ሊከላከላቸው ሲሞክር አሳይተዋል።

ይህ በሆነ ወቅት በላይቤሪያ ታሪክ በዕድሜ ትልቁ የሆኑት ቦአካይ ቃለ-መሐላ ፈፅመው ነበር።

ሥነ-ሥርዓቱ ካፒቶል ተብሎ በሚጠራው ዋና ከተማዋ ሞኖሮቪያ በሚገኘው የሕዝብ እንደራሴዎች መቀመጫ ቅጥር ግቢ ነው የተከናወነው።

ተመራጩ ፕሬዝደንት ከአትሮነስ እንዲርቁ ከተደረጉ በኋላ አዲሱ ምክትል ፕሬዝደንት ጀረማያህ ኩንግ ለእንግዶች ንግግር አድርገው ለፕሬዝደንታዊ እራት ግብዣ ጥሪ አቅርበዋል።

ቦአካይ ባለፈው ኀዳር በተካሄደው ምርጫ የቀድሞውን ታዋቂ እግር ኳስ ተጫዋች ጆርጅ ዊሃን በጠባብ ውጤት ማሸነፋቸው ይታወሳል።

በምርጫ ወቅት የሰውየው የጤና ሁኔታ አንዱ መነጋገሪያ ነበር።

ነገር ግን በመልካም ጤንነት ላይ መሆናቸውን ለቢቢሲ የተናገሩት ቦአካይ “ዕድሜ እዚህ ሀገር እንደ ፀጋ ሊቆጠር ይገባል” ብለው ነበር።

ፕሬዘደንቱ ንግግራቸውን ከማቋረጣቸው በፊት “የላይቤሪያን ተስፋ ልመልስ ነው የመጣሁት” ሲሉ ለሕዝባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ የላይቤሪያ ፕሬዝደንት ሳሉ ቦአካይ ምክትል ሆነው አገልግለዋል።

እስከ 2018 ድረስ የሰርሊፍ መንግሥትን ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ ዩናይትድ ፓርቲን ተቀላቅለው ለምርጫ ተወዳድረዋል።

ቦአካይ ባለፈው ኅዳር የቀድሞውን ፕሬዝደንት ጀርጅ ዊሃ ያሸነፉት በ20 ሺህ ድምፅ ልዩነት ነው።

ቦአካይ በአውሮፓውያኑ 2017 በነበረው ምርጫ የተሳተፉ ሲሆን የላይቤሪያ ወጣቱ ፕሬዝደንት በሆኑት ጆርጅ ዊሃ ተረትተዋል።