ባለቤቷ ለዓመታት ከ50 በላይ በሚሆኑ ወንዶች ያስደፈራት ሴት የፈጠረችው ንቅናቄ

ገና የጠዋት ፀሐይ ብቅ እንዳለች ብዙ ሴቶች ይሰበሰባሉ። መንገድ ዳር ሆነው ዥዜል ፔሊኮንን ይጠብቃሉ።
አንዳንዶቹ አበባ ያመጡላታል። ሌሎቹ "አብረንሽ ነን"፤ "በርቺ" ይሏታል።
ዥዜል በቆራጥ ቁመናዋ ወደ ፍርድ ቤቱ ደጃፍ ታቀናለች።
በፍርድ ቤቱ ለሕዝብ በተመደበ ክፍል ውስጥ መቀመጫ ለማግኘት የሚጠባበቁ ብዙ ናቸው። በቴሌቭዥን የፍርድ ሂደቱን ይከታተላሉ።
ዥዜል የሰባት ልጆች አያት ናት። በደፈሯት ወንዶች ተከባ በፍርድ ቤቱ ቃሏን ትሰጣለች።
ዥዜልን ባለቤቷ በዕፅ እያደነዘዘ ከ80 በላይ በሚሆኑ ወንዶች ለዓመታት አስደፍሯታል።
ወንዶቹን በበይነ መረብ እየፈለገ፣ ወደ ቤታቸው እየጠራ፣ ባለቤቱ መኝታ ክፍላቸው በተኛችበት ለዓመታት አስደፍሯታል።
ባለቤቱን በተደጋጋሚ ሲደፍርና በማያውቋት ወንዶች ሲያስደፍር የሚያሳዩ በሺዎች የሚቆጠሩ ምሥሎችና ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ኮምፒውተሩ ላይ ፖሊስ ካገኘ በኋላ ነበር የፍርድ ሂደቱ የተጀመረው።
ለዓመታት ሲደፍሯት የነበሩ የማታውቃቸው ግለሰቦችና ባለቤቷ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
ኢዛቤል ሙኒር 54 ዓመቷ ነው። "እሷ ውስጥ ራሴን አያለሁ። ከተከሳሾቹ አንዱ ጓደኛዬ ነበር። አስቀያሚ ነው" ትላለች።
የ20 ዓመቷ ሳዲጃ ጀሚል "የሴቶች መብት ንቅናቄ ምሳሌ ሆናለች" ትላታለች ዥዜልን።
ሴቶቹ ከፍርድ ቤቱ ምላሽ ማግኘት ይፈልጋሉ።
በፈረንሳይ ታሪክ ትልቁ የመድፈር ወንጀል የፍርድ ሂደት ነው።
ይሄ ስለ ፈረንሳይ ወንዶች ምን ይላል? የሚለው አንዱ ጥያቄያቸው ነው።
50 ወንዶች ናቸው የተከሰሱት። አንድ ገጠራማ ከተማ ውስጥ ይኖራሉ።
ራሷን ከሳተች ሴት ጋር እንዴት ወሲብ ለመፈጸም ተስማምተው የማያውቁት ሰው መኝታ ቤት ይገባሉ? ሌላው የሴቶቹ ጥያቄ ነው።
ይህ የፍርድ ሂደት ስለወሲባዊ ጥቃትና ሴቶችን በአደገኛ ዕፅ አደንዝዞ ስለመድፈር በይፋ ንግግር እንዲጀመር አድርጓል። ለውጥ ይመጣ ይሆን?
ከሴቶች ፈቃድ ስለማግኘት ያለውን የተዛባ ምልከታ ይለውጥ ይሆን?
የዥዜል ጥንካሬ አንድ ነገር ለውጧል። ማፈር ያለበት ደፋሪው እንጂ የተደፈረች ሴት አይደለችም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከተከሳሾቹ ጀርባ
አቪግኖን ፓላይ ደ ጀስቲስ ፍርድ ቤት ባለፉት ሳምንታት በሰዎች ተጨናንቋል።
ተከሳሾቹ ሲያወሩ፣ ሲቃለዱ፣ ቡና ሲጠጡም ይታያሉ። እንደ ማንኛውም ሰው መደበኛ ሕይወት እንዳላቸው ለፍርድ ቤት ለማሳየት ጠበቆቻቸው የሚጠቀሙበት ስልት ነው ተብሏል።
ጥንዶች ሌሎች ጥንዶችን በመጋበዝ የሚፈጽሙት ወሲብ (swinging) ውስጥ ለመሳተፍ ያሰቡ፣ ሆኖም ግን ያልጠበቁት ነገር ውስጥ የገቡ ወንዶች እንደሆኑ ለመሳልም ተሞክሯል።
'ዴር ቱ ቢ ፌሚኒስት' የተባለው የመብት ተሟጋች ተቋም አባል ኤልሳ ላቦርት "በፍቅር ግንኙነት ውስጥ ያሉ ሰዎች ፍቅረኛቸው ታማኝ እንደሆነ ያስባሉ። ሆኖም ብዙ ሴቶች ራሳቸውን ዥዜል ውስጥ ያዩታል። ይሄ እኔ ላይም ሊከሰት ይችላል ብለው ያስባሉ" ትላለች።
"ሰዎቹ የወንጀል ሊቅ አይደሉም። ኢንተርኔት ላይ ገብተው ባለቤቷን ካገኙ በኋላ ነው ይሄ ሁሉ የሆነው። ማንም ሰው ሊገጥመው የሚችል ነው" ስትልም ታክላለች።
በፈረንሳይ እአአ ከ2012 እስከ 2021፣ 94% የመድፈር ወንጀልና 86% የወሲባዊ ጥቃት ክስ ወደ ፍርድ ቤት አለመወሰዱን ጥናት ይጠቁማል።
ወሲባዊ ጥቃት የሚፈጸመው "ወንዶች ፈጽመውት ማምለጥ እንደሚችሉ ስለሚያስቡ ነው። በፈረንሳይ ወሲባዊ ጥቃት የተበራከተውም ለዚያ ነው" ስትል የመብት ተሟጋቿ ትናገራለች።
'አውሬም አይደሉም፤ ተራ ወንድም አይደሉም'
የፍርድ ሂደቱ በተከናወነባቸው አራት ወራት ተከሳሾቹ ቃላቸውን ሰጥተዋል።
በፍርድ ቤቱ የተመደበው የሥነ ልቦና ባለሙያ ላውራንት ላይት ለፍርድ ቤቱ በሰጠው ቃል "ተከሳሾቹ አውሬም አይደሉም፤ ተራ ወንድም አይደሉም" ብሏል።
አንዳንዶቹ ወንዶች አልቅሰዋል። አንዳንዶቹ የፈጸሙትን ተናዘዋል።
አብዛኞቹ ግን ሰበብ ነው የደረደሩት።
ጥንዶቹ "ጋብዘዋቸው" የተሳተፉበት ድርጊት እንደሆነ አምነው እንደገቡበት ብዙዎቹ ተናግረዋል።
ዥዜል ፈቃዷን እንዳልሰጠች እንዳላወቁ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ሌሎቹ ደግሞ ባለቤቷ ዶምኒክ አስፈራርቷቸው ድርጊቱን እንደፈጸሙ ገልጸዋል።
51ዱ ተከሳሾች የተለያየ የማኅበረሰብ ክፍልን ያሳያሉ።
አንድ ሦስተኛው ልጆች አሏቸው። ግማሾቹ ባለ ትዳር ናቸው፤ ወይም ፍቅረኛ አላቸው።
አንድ አራተኛው ልጅ ሳሉ እንደተደፈሩ ወይም ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ተከሳሾቹ በተያየ ዕድሜና ማኅበራዊ እርከን ላይ ይገኛሉ።
ሁሉም የሚያመሳስላቸው ወንድ መሆናቸው ነው።
'ኮኮ' የተባለ ሕገ ወጥ ወሲባዊ ድረ ገጽ ላይ ነው ከዥዜል ባለቤት ጋር የተገናኙት።
አሁን የተዘጋው ድረ ገጽ 23,000 የወንጀል ድርጊቶች እንደተፈጸመበት ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።
ከተከሳሾቹ 23ቱ (45 በመቶው) ከዚህ ቀደም በሌላ ወንጀል መከሰሳቸውን ቢቢሲ ማወቅ ችሏል።
የሥነ ልቦና ባለሙያው "ወሲባዊ ጥቃት የሚፈጽሙት አንድ ዓይነት ወንዶች ብቻ አይደሉም" ይላል።
ፈረንሳዊቷ ጋዜጠኛ ጁሌት ቻምፒዮን ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለች ነው። የፍራንስ ኢንፎ ዘጋቢ ናት።
"ፈረንሳይ ውስጥ ወንዶች እንዴት ሴቶችን እንደሚመለከቱና ከሴቶች ፈቃድ ስለማግኘት (consent) ያለውን አመለካከት ያሳየ ክስተት ነው" ትላለች።
በፈረንሳይ ስለ መድፈር ያለውን አመለካከት የለወጠ የፍርድ ቤት ጉዳይ ሆኗል።
የፈረንሳይ ወንድ ተዋንያን፣ ድምጻውያንና ጋዜጠኞች ስብስብ በጻፈው ይፋዊ ደብዳቤ ላይ የዥዜል ጉዳይ፣ ጥቃት የሚፈጸመው "በአውሬ ወንዶች ነው" የሚለውን ምልከታ የለወጠ ነው ብለዋል።
"ሁሉም ወንዶች ሊያደርጉት የሚችሉት ነው። የትኛውም ወንድ የተለየ አይደለም። ሁሉም ወንዶች ሴቶችን የሚጨቁን ሥርዓት ተጠቃሚ ናቸው" ብለዋል ወንዶቹ በጻፉት ደብዳቤ።
አባታዊ ሥርዓትን ለሚነቅፉ ወንዶች በአደባባይ እንዲናገሩ ምክንያት ሆኗቸዋል።
"ባህሪያችን የመጣው ከወንድነት ተፈጥሮ ጋር ተያይዞ መሆኑን ማሰብ ማቆም አለብን" ብለዋል።
በፓሪስ በወሲባዊ ጥቃት ላይ አተኩራ የምትሠራው ጠበቃ ካረን ኖብሊንስኪ፣ "ይህ የፍርድ ቤት ጉዳይ ለወጣቶችም ለአዛውንቶችም፣ ለሴቶችም ለወንዶችም አስተማሪ ነው። ሴቶች የሚደፈሩት መጠጥ ቤት ውስጥ ብቻ አይደለም። በቤታቸውም ይደፈራሉ የሚለውን መልዕክት አስተላልፏል" ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
'ሁሉም ወንዶች አይደሉም'
ዥዜል የምትኖው በማዛን ከተማ ነው።
የከተማው ከንቲባ ሉዊስ ቦኔት፣ ዥዜል ላይ ስለደረሰው ነገር ሐዘን እንደተሰማው ቢገልጽም፣ ጉዳዩ 'ተጋኗል' ማለቱ ቁጣ አስነስቷል።
"ከዚህም የከፋ ሊሆን ይችል ነበር" ሲልም ከንቲባው ተደምጧል።
"ልጆች ላይ ቢደርስ ወይም ሴቶች ቢሞቱ ነገሩ የከፋ ይሆናል። አሁን ግን ማንም አልሞተም። በዚህ ጉዳይ ውስጥ ያሉ ቤተሰቦች መልሰው ሕይወታቸውን መገንባት ይኖርባቸዋል" ሲል ከንቲባዊ መናገሩ በመላው ፈረንሳይ እንዲወገዝ ምክንያት ሆኗል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኋላ ላይ ከንቲባው "ከልብ ይቅርታ እጠይቃለሁ" ብሏል።
"ሁሉም ወንዶች ደፋሪ ሊሆኑ ይችላሉ" በሚል ከተጀመረው ንቅናቄ በተቃራኒው 'ሁሉም ወንዶች አይደሉም' የሚል የማኅበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴ ተነስቷል።
"መጥፎ ባህሪ ያላትን ሴት ወክለው ሁሉም ሴቶች እንዲሸማቀቁ አናደርግም። ለምን ወንድ መሆን ብቻ የሚያሰፍር ይደረጋል" ሲል አንድ ግለሰብ በማኅበራዊ ሚዲያ ጽፏል።
ሆኖም ግን ሴቶች ይህንን ንቅናቄ አጥብቀው ተችተዋል። የደረሰባቸውን ጥቃት በመግለጽም በማኅበራዊ ሚዲያ ድምጻቸውን ማሰማት ቀጥለዋል።
ጋዜጠኛዋ ማኖን ማሪኒ "ይሄን የሚሉት ወንዶች ናቸው" ስትል 'ሁሉም ወንዶች አይደሉም' የሚለውን ክርክር ነቅፋለች።
"እስኪ ዝም በሉ። ይሄ ስለእናንተ አይደለም። ስለእኛ ነው። ወንዶች ጥቃት ይፈጽማሉ። ወንዶች ይገድላሉ" ስትል አንድ ግለሰብ በማኅበራዊ ሚዲያ ጽፋለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዕፅ አደንዝዞ መድፈር
ሳንድሪን ጆሶ የምክር ቤት አባል ናት። በዕፅ አደንዝዞ መድፈር (chemical submission) ላይ ንቅናቄ ታደርጋለች።
አምና ጆኤል ጉሪው የተባለ ሴናተር ቤት ሳለች በዕፅ አደንዝዞ ሊደፍራት መሞከሩን ተናግራለች።
ሴናተሩ ድርጊቱን አልፈጸምኩም ሲል አስተባብሏል። ጉዳዩ በቀጣይ ዓመት በፍርድ ቤት ይታያል።
በፈረንሳይ ሕግ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ነው የምትታገለው።
"አሁን ያለው ሕግ ደካማ ነው። ጥቃት ከደረሰባቸው ሴቶች መካከል ፍርድ ቤት የሚሄዱት ጥቂት ናቸው። በቂ የሕክምና፣ የሥነ ልቦና እና የሕግ ድጋፍ የለም። ከወሲባዊ ጥቃት ጋር የተያያዙ ክፍተቶች ብዙ ናቸው" ትላለች።
ከዥዜል ልጅ ካሮላይን ጋር በመሆን ንቅናቄውን ገፍታበታለች።
"ማፈር ያለባት የተደፈረች ሴት ሳይሆን ደፋሪ ነው" ትላለች የዥዜልን አገላለጽ በመዋስ።
ኬሚስቷ ዶ/ር ለይላ ቾውቻይ፣ አደንዛዥ ዕፅ "የኅብረተሰብ ጤና ጉዳይ ሆኖ መታየት የለበት። ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ሲባል አመራሮች በፍጥነት ምላሽ መስጠት አለባቸው። የፍትሕ ጉዳይ ብቻ አይደለም። ሁላችንንም ይመለከተናል" ትላለች።
በፈረንሳይ ሕግ መድፈርን የተመለከተው አንቀጽ ላይ ፈቃድ ስለመስጠት በግልጽ የተቀመጠ ነገር የለም።
ሳንድሪን ለፖሊስ በቂ በጀት መመደብ እንዳለበት ትናገራለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዥዜል የፍርድ ሂደቱ ለሕዝብ ክፍት እንዲሆን ፈቅዳለች።
"ሴቶች የሚያምናቸው ያጣሉ። ውሸታም ስለሚባሉ እውነታቸውን መሆኑን ማሳመን አለባቸው። ዥዜል ጉዳዩን ከሷ በላይ አድርጋዋለች። ወሲባዊ ጥቃት የሚታይበት መንገድ እንዲቃኝ አስችላለች" ትላለች የመብት ተሟጋቿ ኤልሳ።
"ያን ሁሉ አሰቃቂ ቪድዮ በፍርድ ቤት ማየት እንደ ሴት ቀላል አልነበረም። የፍርድ ሂደቱ በወንዶችና በተወሰኑ ሴቶች አመለካከትም ለውጥ የሚያመጣ ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ትላለች ጋዜጠኛዋ ጁሌት ቻምፒዮን።












