የስትሮው ፊልም ዳይሬክተር ታይለር ፔሪ አንድ ተዋናይ ላይ ወሲባዊ ጥቃት በማድረስ ተከሰሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቅርቡ የወጣው የስትሮው ፊልምን ጨምሮ በበርካታ ፊልሞች የሚታወቀው የፊልም ጸሐፊ፣ ዳይሬክተር እና ተዋናይ ታይለር ፔሪ አንድ ተዋናይ ወሲባዊ ጥቃት አድርሶብኛል ሲል ክስ መሰረተበት።
ተዋናዩ በአንድ የቴሌቪዥን ሾው ላይ በሚተውንበት ወቅት ታይለር ፔሪ ወሲባዊ ጥቃቶች እንዳደረሰበት ገልጾ፤ የ260 ሚሊዮን ዶላር ክስ መስርቷል።
ዴሪክ ዲክሰን የተባለው ተዋናይ ታይለር ፔሪ በኢንተርቴይንመንት ኢንዱስትሪው ላይ ያለውን ዝነኝነት ተጠቅሞ "አስገዳጅ እና ወሲባዊ ብዝበዛ" ሁኔታን ፈጥሮብኛል ሲል በሎስ አንጀለስ በመሰረተው ክስ አቅርቧል።
ዴሪክ ይህ የተፈጸመበት 'ዘ ኦቫል ኤንድ ሩዝለስ' በሚለው ፊልም ላይ በሚተውንበት ጊዜ መሆኑን አስረድቷል።
ተዋናዩ፣ ታይለር ፔሪ የተሳካ ተዋናይ እንደሚያደርገው ቃል ገብቶለት የነበረ ቢሆንም፤ በተቃራኒው "ወሲባዊ ትንኮሳ፣ ጥቃት እንዲሁም አካላዊ ጉዳት አድርሶብኛል" ብሏል።
ተዋናዩ የታይለር ፔሪን ወሲባዊ ፍላጎት አልቀበልም በማለቱ ሙያውን የሚጎዳ በቀል እንደደረሰበት ነው በክሱ ላይ ያተተው።
የታይለር ፔሪ ጠበቃ ክሱን ውድቅ አድርገው ገንዘብ ለማግኘት የተደረገ "ማጭበርበሪያ" ሲሉ ጠርተውታል።
"ይህ ግለሰብ ከታይለር ፔሪ ጋር ቅርበት ፈጥሮ የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ የማጭበርበሪያ ክስ አቅርቧል" ሲሉ ጠበቃው ማቲው ቦይድ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
አክለውም "ታይለር ፔሪ በዚህ አይናወጥም እናም እንዲህ አይነት የፈጠራ ትንኮሳዎች እንደማይሳኩ እርግጠኞች ነን" ብለዋል።
ዲክሰን ከታይለር ፔሪ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቁት በአውሮፓውያኑ 2019 አትላንታ በሚገኘው የታይለር ፔሪ ስቱዲዮ በነበረ ዝግጅት ላይ መሆኑን ይናገራል።
ከትውውቃቸው በኋላም ለወራት ያህል ስለ ትወና ሙያው ሲነጋገሩ እንደነበር ገልጿል።
በዚህም ወቅት ታይለር ከተዋናዩ ጋር ወሲባዊ ግንኙነት እንደሚፈልግ፣ በርካታ ወሲባዊ አስተያየቶች እንደሰጠ እና ተዋናዩ ውድቅ ማድረጉም በክሱ ላይ ተገልጿል።
ከዚያም ታይለር በሚሰራው የቴሌቪዥን ሾው ላይ አንድ የትወና ስራ እንደሰጠው ተገልጿል።
ሆኖም ክሱ እንደሚያትተው "ዲክሰን ታይለር ፔሪን ችላ የሚል ከሆነ ወይም ወሲባዊ ጉዳዮችን የማይቀበል ከሆነ የተሰጠው ገጸ ባህርይ ይሞታል" የሚል ቅድመ ሁኔታ ተቀምጧል ይላል።
ተዋናዩ "ታይለረር ፔሪን ማስደሰት ከቻለ ብቻ ገጸ ባህርዩን ተላብሶ መተወን ይቀጥላል" የሚል እሳቤ እንደነበር ክሱ አስረድቷል።
ክሱ ታይለር በተዋናዩ ላይ ፈጸማቸው የተባሉ በርካታ የወሲባዊ ጥቃት ክስተቶችን ጠቅሷል።
ተዋናዩ ከታይለር ፔሪ የሚመጣው ያላሰለሰ ትንኮሳ ሊቆም ስላልቻለ በፊልሙ ላይ የነበረውን የትወና ሙያ ለመተው እንደተገደደና፤ ከታይለር የቀረበለትን የፊልም ጽሁፍ ስራ ለመስራት ፈቃደኛ አለመሆኑ ተጠቅሷል።















