የዴንማርክ ንግሥት በአዲስ ዓመት ንግግራቸው ሳይጠበቅ ንግስና በቃኝ አሉ

የዴንማርክ ንግሥት ማርጋሬት ሁለተኛ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የዴንማርክ ንግሥት ማርጋሬት ሁለተኛ

የዴንማርክ ንግሥት ማርጋሬት ሁለተኛ የአውሮፓውያኑን አዲስ ዓመት በማስመልከት ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር ሳይጠበቅ ከዙፋኑ እንዲሚወርዱ ተናገሩ።

ንግሥት ማርጋሬት ሁለተኛ በንግግራቸው ከሁለት ሳምንታት በኋላ ለ52 ዓመታት ከነገሱበት ዙፋን እንሚወርዱ ይፋ አድርገዋል።

የ83 ዓመቷ ንግሥት ንግሥናውን ለወንድ ልጄ ልዑል አልጋ ወራሽ ፍሬድሪክ አስረክባለሁ ብለዋል።

ማርጋሬት ሁለተኛ እአአ 1972 ላይ የአባታቸው ንጉሥ ፍሬድሪክ 4ኛ ሞትን ተከትሎ ነበር ዙፋን ላይ የወጡት።

ንግሥቷ ከወራት በፊት በጀርባቸው ላይ ያደረጉት ቀዶ ሕክምና ሥልጣን ለቀጣይ ትውልድ እንዲያሸጋግሩ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

ማርጋሬት ለተደረገላቸው ድጋፍ የዴንማርክ ሕዝብን አመስግነው ከንግሥና የምወርድበት “ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው” ብለዋል።

የንግሥቷን ከዙፋን መነሳት ተከትሎ የ55 ዓመቱ ልዑል አልጋ ወራሽ ፍሬድሪክ የዴንማርክ፣ የግሪንላንድ እና ፋሮ አይላንድ ንጉሥ እና ርዕሰ ብሔር ይሆናሉ።

ንግሥት ማርጋሬት በዴንማርክ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ሲሆን ብዙ የአገሪቱ ዜጎችም ንግሥቷ እስከ ሕልፈታቸው ድረስ በዙፋኑ ላይ ይቆያሉ ብለው ይጠብቁ ነበር።

ንግሥት ማርጋሬት በዴንማርክ ታሪክ ለረዥም ዓመታት በንግሥና የቆዩ ተብለው ተመዝግበዋል።

በብዙዎች ዴይዚ ብለው የሚጠሯቸው ንግሥት ማርጋሬት፤ ብዙ ሲጋራ በማጤስ እንዲሁም ሞባይል ስልክ እና ኢንተርኔት በመጥላት ይታወቃሉ።

እናታቸውን በመተካት መንበሩን የሚረከቡት ልዑል አልጋ ወራሽ ፍሬድሪክ ለአካባቢ ጥበቃ ባላቸው ተቆርቋሪነት ይታወቃሉ።

ልዑል አልጋ ወራሹ በሙያ ጠበቃ ከሆነችው ልዕልት ሜሪ አራት ልጆችን ወልደዋል። እነዚህ ወላጆች የልጆቻቸው አስተዳደገ ከሌሎች የተለያ እንዳይሆን በሚል በመንግሥት ትምህርት ቤቶች እንዲማሩ እስከማድረግ ደርሰዋል።

ንግሥት ማርጋሬት ለጥበብ ሥራዎች ትልቅ ፍቅር ያላቸው ሲሆን ብዙ ጊዜያቸውን አርቲስት ሆነው ያሳልፋሉ።

ንግሥቷ ትምህርታቸውን በዩናይትድ ኪንግደም ጊርተን ኮሌጅ እንዲሁም ለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ተከታትለዋል።

እአአ 1967 ላይ ከፈረንሳይዊ ዲፕሎማት ጋር ትዳር መስርተው ባለቤታቸው እአአ 2018 በሞት ተለይተዋቸዋል።

ንግሥቷ ሳይጠበቅ ከዙፋኑ እራሳቸውን እንደሚያገሉ ይፋ ባደረጉበት የአዲስ ዓመት ንግግራቸው በመካከለኛው ምስራቅ እና በዩክሬን ስላለው ጦርነት እንዲሁም ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ ትኩረት መሰጥት እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል።