የናንሲ ፔሎሲ ባለቤት ጠጥቶ በማሽከርከር ጥፋተኛ ተባሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ ባለቤት ጠጥተው መኪና በማሽከርከር ብሎም ጉዳት በማድረስ ጥፋተኛ ተበለው የአምስት ቀን እስር ተፈረደባቸው።
የ82 ዓመቱ ፖል ፔሎሲ በግንቦት ወር ካሊፎርኒያ ናፓ ካውንቲ ውስጥ በመጠጥ ኃይል ውስጥ ሆነው ፖርሽ መኪናቸውን ማጋጨታቸውን እና ጉዳት ማድረሳቸውን አምነዋል።
ሚሊየነሩ ፖል ከዐቃቤ ሕግ ጋር በሚደረግ ድርድር አነስተኛ ፍርድ ይቀበሉ እንጂ ወንጀሉ ከዚህም ለከፋ ጥፋት ይዳርጋቸው ነበር።
በአሜሪካ ኮንግረስ ውስጥ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ከፍተኛ መሪ የሆኑት ናንሲ ፔሎሲ እ.ኤ.አ. ከ1963 ጀምሮ ከፖል ፔሎሲ ጋር በትዳር ቆይተዋል።
ፖል ከዐቃቤ ሕግ ጋር ባደረጉት ድርድር መሠረት ከአምስት ቀኑ በተጨማሪ ሌላ የእስር ቅጣት አይጠብቃቸውም።
ከአደጋውበኋላ በእስር ቤት ሁለት ምሽት አሳልፈው መውጣታቸውም ታውቋል።
ይህንንም ተከትሎ ከአምስት ቀኑ ቅጣት ላይ የሚቀነስ ይሆናል። ለመልካም ሥነ ምግባር ሁለት ተጨማሪ ቀናት የተቀነሰላቸው ሲሆን የመጨረሻው አንድ ቀን የማኅበረሰብ አገልግሎት በመስጠት ይካካሳል።
በፋይናንስ ሥራ ላይ የተሰማሩት ፖል ሌሎች ቅጣቶችም ይጠብቃቸዋል።
ለሦስት ዓመት በዕግድ ላይ የሚቆዩ ሲሆን ለሦስት ወር የሚቆይ እና ስለጠጥቶ ማሽከርከር የሚያስተምር ትምህርት ወስደው ማጠናቀቅ ይጠበቅባቸዋል።
እንዲሁም 7,000 ዶላር የገንዘብ ቅጣትም ይጠብቃቸዋል።
ፖል መንጃ ፈቃዳቸውን ባይነጠቁም የመኪናቸው ሞተር ከመነሳቱ በፊት በትንፋሽ የአልኮል መጠናቸውን የሚለከውን መሳሪያ መጠቀም ይኖርባቸዋል።
ናንሲ ፔሎሲ ባለቤታቸው ላይ የቅጣት ውሳኔ በተላለፈበት ወቅት በችሎት አልተገኙም።
ፖል ፔሎሲ ኦክቪል ካሊፎርኒያ ውስጥ የረዥም ጊዜ ጓደኛቸው እና የዴሞክራቲክ ፓርቲ ለጋሽ ከሆኑት ግለሰብ ቤት ለቀው በወጡበት ወቅት ነበር አደጋው ያጋጠመው።
የፖሊስ መዝገብ እንደሚያመለክተው የ2021 ሞዴል የሆነው ጥቁር ፖርሽ መኪናቸውን በቤታቸው አቅራቢያ ከሚገኝ ጂፕ መኪና ጋር አጋጭተዋል። ሁለቱም ተሽከርካሪዎች ውድመት ደርሶባቸዋል።
ፖል ፔሎሲ የካሊፎርኒያ ሀይዌይ ጠባቂ የፖሊስ መኮንኖችን የሚደግፍ የበጎ አድራጎት ድርጅት አባል መሆናቸውን የሚያሳይ ካርድ አደጋውን ተከትሎ በስፍራው ለተገኙ መኮንኖች አሳይተዋል ሲል ፖሊስ ቅሬታውን አቅርቧል።
ናንሲ ፔሎሲ በወቅቱ በሌላኛው የአሜሪካ ጥግ ሮድ አይላንድ ውስጥ ብራውን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የምረቃ ንግግር ለማቅረብ ተጉዘው ነበር።
ጽሕፈት ቤታቸውም ይህ “የግል ጉዳይ ነው” በማለት ተጨማሪ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።












