ሐሰተኛው ዘረኛ የድምጽ ቅጂና የፈጠረው ቀውስ

በማኅበረሰቡ ውስጥ በበጎ ፈቃደኝነት ስራ ላይ የተሰማራው አልፌ ማሎኔ እና ጋዜጠኛ ክርስቲን ግሪፍዝ ሐሰተኛ መሆኑ በተረጋገጠው በጥላቻ የተሞላው ንግግር መጀመርያ ላይ ተረብሸው ነበር

የፎቶው ባለመብት, Getty/BBC

የትምህርት ቤት ኃላፊ ንቀት የተሞላው ንግግር ማድረጋቸው ሲሰማ በማኅበራዊ ሚዲያ በቀላሉ ተሰራጨ።

በአሜሪካ፣ ባልቲሞር መነጋገሪያ ሆነ። የግድያ ዛቻ ይሰነዘርም ጀመር።

ሆኖም ግን ድምጹ እውነተኛ ሳይሆን በዲፕፌክ የተሠራ ነበር።

ፒክስቪል የተባለው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ዘረኛ ንግግር ሲያደርጉ በምሥጢር የተቀዳ ይመስላል።

“በየቀኑ እነዚህን ደደቦች ለምን እንደምታገስ አይገባኝም። ምስጋና አልባ ጥቁር ተማሪዎችን አይሁዳውያን ነዋሪዎች ጭምር” ይላል ድምጹ።

ባልቲሞር ውስጥ ጥቁርና አይሁዳውያን ማኅበረሰብ ከፍተኛ ቁጥር አለው።

ዳይሬክተሩ ኤሪክ ኢስወርት ይባላል። ከሥራው ተባርሮ ምርመራ ተከፈተ።

አልፊ ማሎን የተባለው የአካባቢው ነዋሪ እንደ ሌሎች ጎረቤቶቹ ድምጹ እውነተኛ ነው ብሎ አምኖ ነበር።

“ስለኛ የሚያስቡት በዚህ መንገድ ነው ብለን ስለምናስብ በድምጽ ስንሰማው አንጠራጠርም” ይላል።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የዳይሬክተሩን ድምጽ ሲሰማው ከተለቀቀው ድምጽ ጋር ተመሳሳይ ነው። ስለዚህ አልተጠራጠረም።

በሰዓታት ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ጋር ድምጹ ደርሷል።

ቢቢሲ ይህ በዲፕፌክ የተሠራ ድምጽ ማኅበረሰቡ ላይ ያደረሰውን ቀውስ ምርመራ አድርጓል።

ሐሰተኛ ኤአይ

ክሪስተን ግሪፊትስ ስለ ትምህርት ነው የምትዘግበው። ድምጹ እጇ ሲገባ፣ አንድ ዘረኛ ሰው በምሥጢር በተቀዳ ድምጽ የተጋለጠ ነው የመሰላት።

ዳይሬክተሩን በወኪሎቹ በኩል ስትጠይቅ “ይህን እሱ አላለም። ድምጹ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተሠራና ሐሰተኛ ነው” አሏት።

ይህንን በዘገባዋ ስታካትት ግን ጉዳዩን አደባብሶ ለማለፍ ሙከራ ነው ብለው ያሰቡ ነበሩ።

ፖሊስ ምርመራ ማድረግ ጀመረ።

ዳይሬክተሩ ስሙ ጠልሽቶ፣ ደኅንነቱም አደጋ ውስጥ ወድቆ ነበር። ማስፈራሪያና ዛቻ ይደርሰዋል።

ፖሊስ ጥበቃ ያደርግለት ጀመር።

የባልቲሞር ፖሊስ ኃላፊ ሮበርት መክሎግ፣ ድምጹ ሐሰተኛ ቅጂ መሆኑን ይፋ አደረጉ።

ዲፕፌክ በመሥራት የ31 ዓመቱ ዳዘን ዳሪን ተከሰሰ። የትምህርት ቤቱ አካል ብቃት እንቅስቃሴ ኃላፊ ነበር።

ወደ ሂውስተን፣ ቴክሳስ ሊጓዝ ሲል ፖሊስ አየር ማረፊያ በቁጥጥር ሥር አዋለው።

በሐሰተኛ ቅጂ፣ በስርቆቶችና የዓይን እማኝ በማስፈራራት ተከስሷል።

የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር እንዲባረር በሚል ድርጊቱን እንደፈጸመ ፖሊስ አስታውቋል።

በትምህርት ቤቱ ኮምፒውተር የሰው ሠራሽ አስተውሎት መተግበሪያዎች ተጠቅሞ ነው ሐሰተኛውን ድምጽ ያቀናበረው።

የባልቲሞር ትምህርት ቤቶች ኃላፊት ሚርያም ሮጀርስ፣ ጉዳዩ በትምህርት ቤቱና በማኅበረሰቡም “ከባድ ነበር” ብላለች።

ለምን ሐሰተኛ ቪድዮ ይሠራል?

በማኅበራዊ ሚዲያ የተዘዋወረው ድምጽ እንጂ ተንቀሳቃሽ ምሥል ስላልሆነ፣ በዲፕፌክ መሠራቱን በቀላሉ መለየት አልተቻለም።

ሆኖም ግን በትኩረት ለሰማ ሰው ድምጹ መካከል የተጨመሩ አርትኦቶች ይሰማሉ።

የአንድን ሰው ትክክለኛ ድምጽ ቀድቶ በዲፕፌክ ሌላ ንግግር እንዲያደርግ የሚያስችሉ መተግበሪያዎች አሉ።

የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ጥቁር ተማሪዎችን ‘ሰነፍ’ ብሎ ሲጠራ ይሰማል። ይህንን የማኅበረሰቡ ነዋሪዎች በቀላሉ ያመኑት መሰል መድልዎ ስለሚደርስባቸው ነው።

ድምጹ ሐሰተኛ መሆኑ ቢታወቅም ጉዳቱ ግን ደርሷል።

ዳይሬክተሩ ወደ ሌላ ትምህርት ቤት ተዘዋውሯል።

ሻሮን የተባለች የአካባቢው ነዋሪ እንደምትለው አይሁዳውያን የሚደርሰውን መገለል ስለምታውቅ ድምጹ ሐሰተኛ ነው ብላ አልተጠራጠረችም።

ድምጹ ሐሰተኛ መሆኑን ካወቀች በኋላም በተፈጠረው መድልዎች መገለል ማዘኗ አልቀረም።

በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተሠሩ ድምጾች፣ ምሥሎችና ተንቀሳቃሽ ምሥሎችን ማኅበራዊ ሚዲያዎች ለይተው በግልጽ እንዲያስቀምጡ የሚያስገድድ ፖሊሲ አለ።

“አሁንም ማኅበረሰባችን ውስጥ ድምጹ ትክክል ነው ብለው የሚያምኑ አሉ። ዳይሬክተሩ አሳዝኖኛል። ይሄ የድምጽ ቅጂ እውነተኛ ዘረኛነት ትኩረት እንዳይሰጠው አድርጓል። ከዚህ በኋላ ትክክለኛነቱን የማላውቀውን ነገር ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አላጋራም” ይለል የአካባቢው ነዋሪ አልፊ ማሎን።