ኬንያ ከሶማሊያ ጋር ያላትን ድንበር ከ15 ዓመት በኋላ ዳግም ልትከፍት ነው

የኬንያ መከላከያ ኃይል አባላት

የፎቶው ባለመብት, Washington Post via Getty Images

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ኬንያ ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው አልሸባብ የሰነዘረባትን ጥቃት ተከትሎ የዘጋችውን የሁለቱን አገራት ድንበር ዳግመኛ ልትከፍት መሆኑን ገለፀች።

ኬንያ ከሶማሊያ ጋር ያላት ድንበር በእስላማዊ ታጣቂ ቡድን አልሻባብ በተሰነዘረበት ጥቃት ምክንያት ዘግታ የቆየች ሲሆን ከ15 ዓመታት በኋላ በሚያዝያ ወር ዳግመኛ እንደምትከፍት ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ አስታውቀዋል።

ሶማሊያ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ታጣቂው ቡድን በኬንያ ውስጥ ተከታታይ ጥቃቶችን ፈጽሟል።

ከእነዚህም ውስጥ እንደ አውሮፓውያኑ በ2013 በዋና ከተማዋ ናይሮቢ በሚገኝ የገበያ ማዕከል ላይ የተፈፀመው እና 67 ሰዎችን የገደለው ጥቃት አንዱ ሲሆን ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ በጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ የተፈፀመው እና 148 ሰዎችን የገደለው ጥቃት ይገኝበታል።

ከዚህ በፊት እአአ በ2023 ድንበሩ ዳግም እንደሚከፈት ተገልጾ የነበረ ቢሆንም ተጨማሪ ጥቃቶች በመፈጸማቸው ዕቅዱ ለሌላ ጊዜ ተላልፎ ቆይቷል።

ሩቶ ሁለቱን አገራት የሚያገናኙ መተላለፊያዎችን እንደገና ለመክፈት የተወሰነው ለዓመታት የተደረገን የጸጥታ ግምገማ ተከትሎ መሆኑን ተናግረዋል።

እርምጃው ደህንነትን አደጋ ላይ እንዳይጥል ለማድረግ ከፍተኛ የጸጥታ ኃይሎች ስምሪት እንደሚኖር ጨምረው ገልጸዋል።

ኬንያም በድንበር በኩል ሕገወጥ የጦር መሳሪያዎችና ሌሎች የኮንትሮባንድ እቃዎች ይገባሉ የሚል ስጋት አላት።

ፕሬዝዳንቱ ዕቅዱን የገለጹት በሰሜን ምሥራቅ ኬንያ ውስጥ የምትገኘውን እና በርካታ የሶማሊያ ጎሳ አባላት መኖሪያ በሆነችው የድንበር ከተማ ማንዴራን በጎበኙበት ወቅት ነው።

"በማንዴራ የሚገኙ ኬንያውያን ድንበሩ ለረጅም ጊዜ በመዘጋቱ ምክንያት በሶማሊያ ከሚገኙ ዘመዶቻቸውና ከጎረቤቶቻቸው ጋር መቆራረጣቸው ተቀባይነት የለውም" ሲሉ ሩቶ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

የድንበሩ ዳግም መከፈት "ለሕዝባችን የጋራ ብልጽግና ድንበር ተሻጋሪ የንግድ ልውውጥን" ያሳድጋል ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

በንግግራቸው በተደጋጋሚ ለጥቃት ዒላማ የሆኑትን የማንዴራን ነዋሪዎች በሙሉ "ከአልሸባብ ጋር በሚደረገው ውጊያ ተቀላቀሉን። እነዚህ አልሸባብ ከንቱ ናቸው፤ ኬንያ ከእናንተ ጋር እንደምትሰራ ቃል እገባላችኋለሁ፤ እነዚህን ወንጀለኞች እና አሸባሪዎችን ለመዋጋት አግዙን።"

አልሸባብ በናይሮቢ በሚገኘው የዌስትጌት ሞል እና በጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ላይ ከፈጸመው ጥቃት በተጨማሪ፣ እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 በማንዴራ ካውንቲ በተሽከርካሪ ላይ ባደረሰው ጥቃት 28 ተሳፋሪዎች ሲገደሉ ከአምስት ዓመታት በኋላ ደግሞ በናይሮቢ በሚገኝ ሆቴል ላይ በፈጸመው ጥቃት ቢያንስ 21 ሰዎችን ሕይወታቸውን አጥተዋል።

እአአ በ2015 ኬንያ በሁለቱ አገራት ድንበር አካባቢ ታጣቂዎቹን ለመከላከል በሚል 680 ኪ.ሜ የሚረዝም አጥር ለመገንባት ፍላጎት እንዳላት ገልጻ 10 ኪሜ የሚሸፍን የሽቦ አጥር ከገነባች በኋላ ዕቅዱ ተቋርጧል።

ይህ ለሦስት ዓመት ያህል የተካሄደው የአስር ኪሎ ሜትር የሽቦ አጥር ግንባታ 35 ሚሊዮን ዶላር እንደወጣበት ተገልጾ ነበር።