የዩኬ የስለላ ድርጅት በ116 ዓመታት ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ኃላፊ ተሾመለት

የፎቶው ባለመብት, AP
የዩናይትድ ኪንግደም የስለላ ድርጅት ኤም አይ ሲክስ (MI6) በ116 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በሴት ኃላፊ ሊመራ ነው።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1999 የምስጢራዊ ደህንነት መስሪያ ቤቱን የተቀላቀለችው ብሌዝ ሜትሬሊ፤ የድርጅቱ 18ኛ ኃላፊ ሆና በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ከሰር ሪቻርድ ሙር ኃላፊነቷን ትረከባለች።
በአሁኑ ወቅት በደህንነት መስሪያ ቤቱ በቴክኖሎጂ እና በፈጠራ ቢሮ ውስጥ በኃላፊነት እየሰራች የምትገኘው ግለሰቧ፤ ተቋሙን እንድትመራ በመጠየቋ ኩራትና ክብር እንደተሰማት ተናግራለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኬር ስታርመር ሹመቱን "ታሪካዊ" ካሉ በኋላ "የስለላ ተቋማችን ከምን ግዜውም በላይ አስፈላጊ በሆነበት ወቅት" የተሾመች መሆኗን ተናግረዋል።
ኤም አይ ሲክስ የዩናይትድ ኪንግደምን ደህንነት ለማረጋገጥ በሌላ አገር የስለላ ስራዎችን የማካሄድ ኃላፊነት ተጥሎበታል።
ዋና ዓላማው ሽብርተኝነትን ማስቆም፣ የጠላት አገራትን እንቅስቃሴ ማወክ እና የሳይበር ደህንነትን ማጠናከር ናቸው።
በተለምዶ ዋና ኃላፊው "ሲ" በመባል የሚጠራ ሲሆን ብቸኛው በይፋ ማንነቱ የሚገለጽ የደህንነት መስርያ ቤቱ አባል ነው።
የ47 ዓመቷ ሜትሬሊ በአሁኑ ጊዜ የ "Q" ዋና ዳይሬክተር ናት።
ኪው "Q" ሚስጥራዊ የስለላ አባላትን ማንነት ለመጠበቅ ያለመ ወሳኙ የቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ክፍል ነው።
ይህ ክፍል ቻይና በአሻራ ላይ (ባዮሜትሪክስ ሰርቨይላንስ) በመመስረት የምታደርገውን ክትትል ለማለፍ አዳዲስ መንገዶችን ይጠቀማል።
"ኤም አይ ሲክስ ከኤምአይ ፋይቭ እንዲሁም ከዩኬ የሳይበር ደህንነት ተቋም ጋር በመሆን የብሪታንያ ሕዝቦችን ደህንነት ለመጠበቅ እና የዩናይትድ ኪንግደምን ጥቅሞች ለማስከበር ወሳኝ ሚና ይጫወታል" ብላለች።
"ከኤም አይ ሲክስ ደፋር መኮንኖች እና ባለሙያዎች እንዲሁም ከብዙ ዓለም አቀፍ አጋሮቻችን ጋር በመሆን የተጀመረውን ሥራ ለመቀጠል እጓጓለሁ።"
በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ አንትሮፖሎጂ የተማረችው ሜትሬሊ፣ ቀደም ሲል በኤም አይ ፋይቭ፣ የኤም አይሲክስ እህት ኩባንያ ውስጥ የአገር ውስጥ ደህንነት ኤጀንሲ በመሆን በዳይሬክተርነት የሰራች ሲሆን አብዛኛውን ጊዜዋን ያሳለፈችው በመካከለኛው ምሥራቅ እና አውሮፓ ነው።
እአአ በ2024 ከንጉሱ ለእንግሊዝ የውጭ ፖሊሲ ላበረከተችው አገልግሎት ሜዳሊያ ተቀብላለች።
እአአ በታህሳስ 2021 በኤምአይፋይቭ ውስጥ ዳይሬክተር በነበረችበት ወቅት "ዳይሬክተር ኬ" በሚል መጠሪያ ከቴሌግራፍ ጋዜጣ ጋር ባደረገች ቃለ መጠይቅ፤ በዩኬ ብሄራዊ ደህንነት ላይ የሚደርሱ ስጋቶች "በእርግጥ የተለያዩ ናቸው" ብላ ነበር።
"የምንመለከታቸው ስጋቶች በዋነኛነት መንግሥትን በመጠበቅ፣ ሚስጥሮችን በመጠበቅ፣ ሕዝቦቻችንን መጠበቅ፣ ግድያን መመከት፣ ኢኮኖሚያችንን በመጠበቅ፣ ስሱ ቴክኖሎጂዎችን እና ወሳኝ እውቀቶችን መጠበቅ ላይ የተመሰረቱ ናቸው" ስትል ተናግራለች።
አክላም "የሩሲያ መንግሥት እንቅስቃሴ፣ ሩሲያ ራሷ ሳትሆን፣ ስጋት ሆኖ ቀጥሏል" እንዲሁም ቻይና "የዓለምን መንገድ እየቀየረች እና ለእንግሊዝ አስደናቂ ዕድሎችን እና ስጋቶችን እያቀረበች ነው" ስትል አክላለች።















