በ18 ወራት 40 የጭነት መኪና አሽከርካሪዎች ሲገደሉ፣ ከ200 በላይ ጉዳት ደረሰባቸው

የተቃጠለ የጭነት ተሽከርካሪ

የፎቶው ባለመብት, SM

በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ውስጥ 40 የሚሆኑ ድንበር ተሻጋሪ የጭነት መኪና አሽከርካሪዎች ሲገደሉ፣ ከ200 በላይ የሚሆኑት እገታን ጨምሮ ሌሎች ጉዳቶች እንደደረሰባቸው አንድ የአሽከርካሪዎች ማኅበር ለቢቢሲ ገለጸ።

ጉዞ የኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ማኅበር እንዳለው በአገሪቱ በግጭት ውስጥ በሚገኙ ክልሎች ውስጥ በጭነት ተሽከርካሪዎች እና አሽከርካሪዎቻቸው ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች እየተባባሱ መጥተዋል።

ይህ በአሽከርካሪዎች ላይ የደረሰው የሞት እና የአካል ጉዳት አሃዝ ማኅበሩ መረጃ የደረሰው እና ለማረጋገጥ የቻላቸውን ብቻ የሚያመለክት ነው።

የማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ ዮሐንስ ታምራት፣ ከዚህ ቀደም አሽከርካሪዎችን በማገት ገንዘብ የመጠየቅ ሁኔታዎች እንደነበሩ ጠቅሰው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሰላማዊ አሽከርካሪዎች "መሪ ጨብጠው በተቀመጡበት መኪና ውስጥ" እየተገደሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"በዚህም ምክንያት ሙያውን የሚጠሉ እና ሥራቸውን የሚለቁ አሽከርካሪዎች እየተበራከቱ መጥተዋል" ብለዋል።

ጥቃቶቹ በአብዛኛው በተለይ የመንግሥት ኃይሎች ከታጣቂ ቡድኖች ጋር በሚፋለሙባቸው በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች እንደሚፈፀሙ አቶ ዮሐንስ አመልክተዋል።

በቅርቡም በአማራ ክልል በሚገኘው አዲስ ዘመን ከተማ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ታጅበው እየተጓዙ በነበሩ ተሽከርካሪዎች ላይ በተከፈተ ተኩስ የአንድ አሽከርካሪ ሕይወት ማለፉን ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ነሐሴ 22/2017 ዓ.ም በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከሚገኘው ግዮን የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበር መጋዘን እህል ጭነው ለመውጣት "እናጅማ" ወደተባለ ቀበሌ የገቡ ሁለት የጭነት ተሽከርካሪዎች በታጣቂዎች መቃጠላቸው እና አሽከርካሪዎቹ ከእነ ረዳቶቻቸው ለቀናት ታግተው መቆየታቸውን አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ወደ አካባቢው ማዳበሪያ ዘግይቶ በመግባቱ ምክንያት ከአካባቢው እህል ተጭኖ አይወጣም" የሚል ተቃውሞ እንደነበር ያወሱት እኚህ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ነዋሪ፣ ተሽከርካሪዎቹ በመንግሥት የፀጥታ ኃይል ታጅበው ለመውጣት እየተጠባበቁ ሳለ ጥቃቱ እንደተፈፀመባቸው አስረድተዋል። በወቅቱ የተኩስ ልውውጥ እንደነበርም ነዋሪው ተናግረዋል።

"ታጣቂዎቹ እህሉን ከተሽከርካሪዎቹ ላይ ካወረዱ በኋላ ሌሎች ተሽከርካሪዎች ተመልሰው እንዳይመጡ በሚል ነው ያቃጠሏቸው።" ብለዋል።

በአካባቢው የተለያዩ ታጣቂዎች በመኖራቸው ድርጊቱን ማን እንደፈፀመው መናገር አስቸጋሪ ነው ያሉት ነዋሪው፣ አሽከርካሪዎቹ ግን "የፋኖ ታጣቂዎችን" ተጠያቂ እንዳደረጉ ገልጸዋል።

እንደ ነዋሪው ከሆነ ጥቃቱ የተፈፀመበት ቦታ ከደጀን ከተማ 26 ኪሎ ሜትር ገደማ የሚርቅ ሲሆን በቅርብ ርቀት ላይ የመንግሥት የፀጥታ ኃይል ካምፕ ይገኛል።

የግዮን የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበር አንድ አመራርም በሁለት ተሽከርካሪዎቻቸው ላይ ጥቃት መፈፀሙን አረጋግጠዋል። ሆኖም አመራሩ "ለደኅንነቴ እሰጋለሁ" በማለት ስለ ክስተቱ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

በጭነት ተሽከርካሪዎች እና አሽከርካሪዎቻቸው ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በአማራ ክልል፣ መተማ፣ ሁመራ፣ አዲስ ዘመን እንዲሁም ከወልዲያ ወደ ጎንደር እና ባሕር ዳር በሚወስዱ መንገዶች ላይ፤ በኦሮሚያ ክልል ደግሞ መተሃራ፣ ወለንጭቲ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃም መስመር ባሉ አካባቢዎች በተደጋጋሚ እንደሚፈፀሙ የጉዞ አሽከርካሪዎች ማኅበር ሊቀ መንበሩ አቶ ዮሐንስ ጠቅሰዋል።

ምንም እንኳን በኦሮሚያ ክልል ወለንጪቲ እና መተሃራ ይፈፀሙ የነበሩ ጥቃቶች መንግሥት በሥፍራው የፀጥታ ኃይሎችን በማሰማራቱ እና ከፍተኛ ጥበቃ በማድረጉ ጋብ ቢልም፣ በአማራ ክልል የሚፈፀሙ ጥቃቶች ግን ተባብሰው መቀጠላቸውን ተናግረዋል።

አቶ ዮሐንስ እነዚህ ጥቃቶች በታጣቂዎች እንደሚፈፀሙ የገለጹ ሲሆን፣ ለጥቃቶቹ ኃላፊነት የወሰደ አካል የለም በማለት የታጣቂዎቹን ማንነት እንደማያውቁ ተናግረዋል።

"ይህ ጥቃት እንዴት እንደሚቆም አናውቅም፤ ከመንግሥት አካላት ጋር እየተነጋገርን ነው" ብለዋል።

ጉዞ የአሽከርካሪዎች ማኅበር በሥሩ አንድ ሺህ አባላት ያሉት ሲሆን፣ አባል አሽከርካሪዎቹ ኬንያ እና ጂቡቲን ጨምሮ ከጎረቤት አገራት ነዳጅ፣ ማዳበሪያ እና ሌሎች ጭነቶችን የሚያጓጉዙ ናቸው።

የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ብርሃኔ ዘሩም በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ በተለይም በጭነት ተሽከርካሪዎች እና አሽከርካሪዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል።

የዘርፉ ሰላም እንዳይበላሽ መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ግፊት እያደረግን ነው የሚሉት አቶ ብርሃኔ፣ ይህንን በማስመልከትም ለተወካዮች ምክር ቤት ደብዳቤ መጻፋቸውን ጠቅሰዋል።

"ጉዳዩ ትኩረት ካልተሰጠው እና የመንገዶቹ ደኅንነት ካልተጠበቀ አሽከርካሪዎች በሥራው ላይ የመሰማራታቸው ነገር አጠያያቂ ሊሆን ይችላል" ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አሽከርካሪዎች የበጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ተክሌ ሽፈራው በበኩላቸው በተለያዩ ቦታዎች ላይ ጥቃቶች እንደሚፈፀሙ ገልጸው፤ "በአገሪቱ ባለው የሰላም እጦት ምክንያት በተለይ በአማራ ክልል አሽከርካሪዎች ነጻ ሆነው ማሽከርከር አልቻሉም፤ የተሰጣቸውን ጭነት በአግባቡ እና በሰዓቱ ለማድረስ እየተቸገሩ ነው" ብለዋል።

በቅርቡ ከጂቡቲ ነዳጅ ጭነው በእጀባ እየተጓዙ ባሉ ተሽከርካሪዎች ላይ በተከፈተ ተኩስ የአንድ አሽከርካሪ ሕይወት ማለፉን አቶ ተክሌ ተናግረዋል።

በአብዛኛው ተሽከርካሪዎች ከጂቡቲ ነዳጅ ጭነው ወደ ባሕር ዳር እና ጎንደር የሚገቡት ጋሸና እና ገረገራ የተባሉ አካባቢዎችን አቆራርጠው እንደሆነ የገለጹት አቶ ተክሌ፣ ጥቃቱ የተፈፀመው በደቡብ ጎንደር፣ ገረገራ በተባለ አካባቢ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"መንስኤው የዘራፊ መበራከት ነው" ሲሉም መንግሥት ጥበቃውን አጠናክሮ አሽከርካሪዎች ሥራቸውን እንዲያከናውኑ እንዲያስችል ጠይቀዋል።

በአማራ ክልልም ሆነ በአሮሚያ ክልል በአሽከርካሪዎች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን በተመለከተ የክልሎቹን ባለሥልጣናት ለማነጋገር ቢቢሲ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

በክልሎቹ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖችም እነዚህን ጥቃቶች በተመለከተ ያሉት ነገር ባይኖርም በተደጋጋሚ በሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች እና በከባድ ተሽከርካሪዎች ላይ ለሚፈፀሙ ጥቃቶች የሚቀርብባቸውን ክስ አስተባብለዋል።

በቅርቡ በአማራ ክልል፣ ምዕራብ ጎንደር ዞን "በታቀደ ጥቃት" የአፈር ማዳበሪያ ጭነው በእጀባ ሲጓዙ የነበሩ ቢያንስ 16 ሹፌሮች ሲገደሉ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ደግሞ መታገታቸውን የአካባቢው አስተዳደር እና የአሽከርካሪዎች ማኅበር መናገራቸው ይታወሳል።

ከእነዚህ አሽከርካሪዎች አብዛኞቹ ሟቾች ከጂቡቲ ማዳበሪያ ጭነው በፀጥታ ኃይሎች ታጅበው ሲጓዙ የነበሩ የከባድ መኪና ሾፌሮች መሆናቸው ተነግሯል።

ስለ ጥቃቱ ሰፋ ያለ መግለጫ ያወጣው የዞኑ አስተዳደር መከላከያ ሠራዊት እና የፀጥታ ኃይሎች ላይ "ታቅዶ፣ ሆን ተብሎ፤ ታስቦበት የተዘጋጀ" ሲል ጥቃቱን የገለፀ ሲሆን፤ ሾፌሮች መገደላቸውን አስታውቋል።

ለዚህም "ጽንፈኛ" ሲል የጠራቸውን በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን ተጠያቂ አድርጓል።