"የ2010ሩ ተስፋ፣ አምባገነናዊ መንግሥት ለመገንባት በታቀደ ፕሮጀክት ተከድቷል" - ኦፌኮ

የኦፌኮ አመራሮች

የፎቶው ባለመብት, Oromo Federalist Congress - OFC

ተቃዋሚው የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከሰባት ዓመታት በፊት "በታሪካዊ ዴሞክራሲያዊ መደላድል ተስፋ" የተጀመረው "ለውጥ" " 'የባከነ ተስፋ' ዜና መዋዕል ሆነው ተጠናቋል" አለ።

ፓርቲው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን መምጣት የተጀመረው "ተስፋ"፤ "አምባገነናዊ መንግስት ለመገንባት በታቀደ ፕሮጀክት ተከድቷል" ሲል ተችቷል።

ኦፌኮ ይህን ያለው የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሐምሌ 12 እና 13/ 2017 ዓ.ም. በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ካደረገ በኋላ ባቀረበው "የመጨረሻ ግምገማ" ነው።

"ኦሮሚያ እና መላው ኢትዮጵያ አንዱ ሌላውን በሚያባብስ አውዳሚ አዙሪት" መወጠራቸውን የጠቆመው ፓርቲው፤ የሃገሪቱን "ደዌዎች በመመርመር ወደ ፍትሃዊና የተረጋጋ" ነገ ለመጓዝ ያስችላሉ ያላቸውን መንገዶች ጠቁሟል።

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ በአራት ገጾች ባወጣው መግለጫ ቅድሚያ የሰጠው "ለሀገራዊ ቀውሶች ግምገማ" ሲሆን፤ "የሃገሪቱ ሌሎች ቀውሶች ሁሉ የሚመነጩበት መሰረታዊው ቀውስ ፖለቲካዊ ነው" ሲሉ አቋሙን አስታውቋል።

ከሰባት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የመጣው "ተስፋ"፤ አምባገነናዊ መንግሥት ለመገንባት በታቀደ ፕሮጀክት ተከድቷል" ያለው ተቃዋሚው ኦፌኮ፤ ይህ የሆነው "ከፖለቲካዊ ውይይት ይልቅ ወታደራዊ ኃይልን በተደጋጋሚ በመምረጥ" መሆኑን ገልጿል።

ይህም በበኩሉ በሶስት ተያያዥ "ጥቃቶች" የሀገሪቱን "ማህበራዊ መዋቅር በታትኖታል" ብሏል።

"መንግሥት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን በዘዴ አፍርሷል" ሲል የወቀሰው ኦፌኮ ለዚህም የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን፣ ጋዜጠኞችን እና የማኅበራዊ አንቂዎችን እስር እንዲሁም በፓርቲዎች፣ መገናኛ ብዙኃን እና በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ የወጡ "አፋኝ ህጎችን" በማሳያነት ጠቅሷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የመገናኛ ብዙኃን እና የምርጫ አዋጆች ማሻሻያ በተያዘው ዓመት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቃቸው ይታወሳል።

ከዚህ በተጨማሪም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ማሻሻያ በሂደት ላይ የሚገን ሲሆን ማሻሻያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች 'በፖለቲካ አድቮከሲ' እና በምርጫ ጉዳዮች ላይ የሚኖራቸውን ተሳትፎ የሚገድብ ድንጋጌ ተካትቶበታል።

የእነዚህ ድርጊቶች ድምር "የፖለቲካ ምህዳሩን ሙሉ በመሉሙ በመዝጋት ለበርካታ ተቃዋሚ ኃይሎች ጦርነት ብቸኛ አማራጭ እንዲመስል አድርገዋል" ያለው ኦፌኮ፤ የዚህ ወጤትም "አሁን አገሪቱን እየበላ ያለው አውዳሚ ጦርነት ነው" ብሏል።

በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ጦርነት እየተካሄደ መሆኑን እንዲሁም በትግራይ ያለው "ስስ ሰላም እየተሸረሸረ" መሆኑን ጠቁሟል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግሥት "በአፍሪካ ቀንድ አለመረጋጋትን በሚያስፋፋ ኃላፊነት የጎደለው የውጭ ፖሊሲ" የተከተለ ነው የሚል ክስ አቅርቧል።

ፓርቲው "የቀይ ባህር መዳረሻን ለማግኘት የሚደረገው ግትር ጥረት፣ እየጨመረ ከመጣው የጦርነት ነጋሪት መጎሰም ጋር ተዳምሮ ከኤርትራ ጋር ያለውን ውጥረት በአደገኛ ሁኔታ አባብሶ የጦርነት ስጋት እንዲያንዣብብ አድርጓል" ብሏል።

የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት "ብሄራዊ ጥቅም" የሚካድ አለመሆኑን የጠቆመው የኦፌኮ መግለጫ፤ "ይህን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር እየተኼደበት ያለው አደገኛ መንገድ" ለሀገሪቱ "ከፍተኛ መዘዝ" እንዳያስከትል አስጠንቅቋል።

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ የሀገሪቱን ማኅበራዊ መዋቅር "በታትኖታል" ያለው ሌላኛው ጉዳይ "የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ውድቀት" ነው።

መንግሥትን "መሰረታዊ ፍላጎቶችን ችላ በማለት የገፅታ ግንባታ ላይ ፕሮጀክቶች ላይ በማተኮር" የሚከሰው ኦፌኮ፤ "በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መኖሪያና መስሪያ ቤቶች ያለ በቂ ካሳና ያለ ህጋዊ አካሄድ እንዲፈርሱና ዜጎች ጎዳና ላይ እንዲበተኑ አድርጓል" ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም "[መንግስት] 'የኢኮኖሚ ሊበራላይዜሽን' በሚል ስም ሥርዓቱ የሀገራችንን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለውጭ ጥቅሞች አሳልፎ የሰጠ ሲሆን፣ ለሚቀጥሉት ትውልዶች ከባድ ሸክም የሚሆን የሀገር ዕዳ አከማችቷል" ሲል ወቅሷል።

"በህብረ ብሄራዊ ፌደራላዊ ሥርዓት ላይ የሚፈጸም ስልታዊ ጥቃት"ም እንዲሁ ማኅበራዊ መዋቅሮችን "በታትኗል" ሚል በፓርቲው ተጠቅሷል።

ኦፌኮ "ማዕከላዊና አምባገነናዊ መንግሥትን እንደገና ለመመስረት" ታስቦ በህብረ-ብሔራዊ ፌደራላዊ ሥርዓት ላይ የሚካሄደው "ስልታዊ የማዳከም ዘመቻ"፤ "የሀገራዊው ቀውስ ማዕከል" መሆኑን ጠቅሷል።

የተቃዋሚ ፓርቲው በግምገማው "የመርህ አቋሙን" አስታውቋል፤ "የአንድነት ጥሪ"ም አቅርቧል።

በኦሮሞ ልሂቃን ና የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ያለው "የእርስ በርስ ሽኩቻ" እንዲያበቃ ጥሪ ያቀረበው ፓርቲው፤ የጋራ ግንባር ለመፍጠር "ለሁሉም እውነተኛ ኃይሎች የትብብር እጃችንን እንዘረጋለን" ብሏል።

በተጨማሪም ፓርቲው የዴሞክራሲያዊ ሽግግር ፍኖተ ካርታ እንዲኖር "መሰረታዊ" ያላቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ለመንግስት አቅርቧል።

ከቅድመ ሁኔታዎቹ መካከል በቀዳሚነት የተጠቀሰው "/ሁሉም ጦርነቶች እንዲቆሙና ሁሉን አቀፍ የሰላም ሂደት እንዲጀመር" የቀረበው ጥያቄ ነው።

እንዲሁም "ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ" እና በመገናኛ ብዙኃን እና በሲቪል ማኅበረሰብ ላይ የወጡ አፋኝ ህጎች እንዲሻሩ" ጠይቋል።

ከዚህ በተጨማሪም "በክልሎች ራስ ገዝ አስተዳደር ላይ የሚደረገው ህገ-መንግሥታዊ ያልሆነ ጥቃት እንዲቆም ይፋዊና ህጋዊ አስገዳጅነት ያለው ቃል እንዲገባ" ጥያቄ አቅርቧል።

አራተኛው የኦፌኮ ቅድመ ሁኔታ ከምርጫ ቦርድ ጋር የተያያያዘ ሲሆን፤ "የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሁሉም ፓርቲዎች ስምምነትና ግልጽ በሆነ መንገድ እንደገና እንዲዋቀር" ጠይቋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ፓርቲው ጥያቄ ያቀረበበት ሌላኛው ጉዳይ የጸጥታ ኃይሎች፣ የፍትህ አካላትና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ የመንግስት ተቋማት በምርጫው ሂደት "ፍጹም ገለልተኛ እንዲሆኑ የሚያረጋግጥ ይፋዊና አስገዳጅ ስምምነት" እንዲኖር ነው።

የመጨረሻው የኦፌኮ ቅድመ ሁኔታ "የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እንዲመለስ" የሚጠይቅ ሲሆን "ለከባድ ዕዳና ችግር የዳረጉን የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ሙሉ በሙሉ እንዲቀየሩና በምትኩ በምግብ ዋስትና፣ በስራ ፈጠራና ብዙኃኑን በሚጠቅሙ ኢንቨስትመንቶች ላይ ትኩረት እንዲደረግ" የሚጠይቅ ነው።

የኦፌኮ ማዕከላዊ ኮሚቴ በመግለጫው ማገባደጃ ላይ ለተለያዩ አካላት ጥሪዎችን አቅርቧል።

ለሁሉም የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ኃይሎች" ባቀረበው ጥሪ " 'የዴሞክራሲ ቃል ኪዳን' እንድንፈጥር እንጋብዛችኋለን። የሁሉንም የኢትዮጵያ ብዝሃ ህዝቦች መብት የሚያከብር፣ የተባበረና ሰላማዊ አማራጭ በጋራ እናቅርብ" ብሏል።

የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት

የፎቶው ባለመብት, Oromo Federalist Congress