አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ዜጎቻቸው በአስቸኳይ ከሊባኖስ እንዲወጡ አሳሰቡ

በርካታ አየር መንገዶች ወደ ሊባኖስ የሚያደርጉትን በረራ ሰርዘዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በርካታ አየር መንገዶች ወደ ሊባኖስ የሚያደርጉትን በረራ ሰርዘዋል።

በመካከለኛው ምስራቅ አይቀሬ የተባለ ሰፊ ጦርነት ማንዣበቡን ተከትሎ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ካናዳ ዜጎቻቸው ከሊባኖስ በአስቸኳይ እንዲወጡ አሳሰቡ።

በቤይሩት የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ዜጎች “በተገኘው ቲኬት” ከሊባኖስ በአስቸኳይ እንዲወጡ አሳስቧል።

የዩኬ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ እንዲሁ በቀጠናው ያለው ሁኔታ በፍጥነት ሊቀያየር ስለሚችል ዜጎች ከሊባኖስ እንዲወጡ አሳስበዋል።

እስራኤል የሐማስ የፖለቲካ መሪ የነበሩትን እስማኤል ሃኒያ በኢራን ከገደለች በኋላ ኢራን “ከባድ” የአጸፋ ምላሽ እሰጣለሁ ብላለች።

ከሃኒያ ግድያ በፊት ደግሞ እስራኤል መቀመጨውን ሊባኖስ ያደረገው የሄዝቦላ ከፍተኛ አዛዥ የነበረውን ፉአድ ሹከር ቤይሩት ውስጥ መግደሏ ይታወሳል።

ኢራን የሐማሱ መሪ በቴህራን መገደላቸው እንዲሁም የምታስጥቀው የሄዝቦላ መሪ ቤይሩት ውስጥ መገደሉ አስቆጥቷል።

ከጥቂት ወራት በፊት እስራኤል በሶሪያ የሚገኘውን የኢራንን ቆንስላ በቦምብ ካጋየች በኋላ ቴህራን በመቶዎች የሚቆጠሩ ድሮኖችን እና ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል መተኮሷ ይታወሳል።

ብዙዎች መሰል የበቀል እርምጃ ከኢራን የሚወሰድ ከሆነ ሰፊ ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል ይላሉ።

ሄዝቦላም እንዲሁ እስራኤል ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት የሚከፍት ከሆነ እስራኤል በምላሹ ሙሉ ወታደራዊ አቅሟን ልትጠቀም ትችላለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ቅዳሜ ሐምሌ 27/2016 ዓ.ም. ምሽት ላይ ሄዝቦላ ወደ እስራኤል በመቶዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን አስወንጭፏል።

ማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ የወጡ ተንቀሳቃሽ ምስሎች የእስራኤል የአየር መከላከያ ሰርዓት ‘አይረን ዶም’ ወደ እስራኤሏ ቤይት ከተማ የተተኮሱ ሮኬቶችን አየር ላይ ሲመታ አሳይተዋል።

ሮኬቶቹ በሰው ላይ ያደረሱት ጉዳት ስለመኖሩ እስካሁን የተባለ ነገር የለም።

ከአሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንገድም በተጨማሪ የዮርዳኖስ እና የካናዳ መንግሥታት ዜጎቻቸው ከሊባኖስ እንዲወጡ እንዲሁም ወደ ሊባኖስ ጉዞ ከማድረግ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

የአሜሪካ ኤምባሲ ባወጣው ማሳሰቢያ ላይ ከሊባኖስ የማይወጡ ዜጎቹ ዘለግ ላለ ጊዜ እራሳቸውን ከልለው ማቆየት የሚችሉበት ሁኔታን እንዲያመቻቹ አሳስቧል።

ይህ ማሰሰቢያ የወጣው በርካታ አየር መንገዶች ወደ ሊባኖስ የሚያደርጉትን በረራ እየሰረዙ ባሉበት ወቅት ነው።

ዩኬ ዜጎችን ከሊባኖስ ለማስወጣት ተጨማሪ የሠራዊት አባላትን የሚጨመር የባለሙያዎች ቡድን ወደ ቀጠናው እንደላከች አስታውቃለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በጋዛ ተፈናቃዮችን አስጠልሎ በነበረ ትምህርት ቤት ላይ የእስራኤል ጦር በፈጸመውን የአየር ጥቃት 17 ሰዎች መገዳለቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

እስራኤል ትምህርት ቤቱ የሐማስ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ ሆኖ ሲያገለግል ነበር ብላለች።