በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በእስራኤል የማያባራ ጥቃት ውስጥ እንዴት እየኖሩ ነው?

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር ጦርነት በጀመሩበት ዕለት እስራኤል በተመሳሳይ ሊባኖስ ውስጥ ጥቃት ከፍታ እግረኛ ወታደሮችን ጭምር በማሰማራት የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ እያካሄደች ነው።

ማክሰኞ ሌሊት አሜሪካ እና ኢራን የተኩስ አቁም ለማድረግ መስማማታቸውን ተከትሎ ረቡዕ ዕለት የእስራኤል ጦር በመላው ሊባኖስ በሚገኙ "የሄዝቦላህ ዒላማዎች" ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

በዚህ ጥቃት ከ180 በላይ ሰዎች ሲገደሉ ከ700 በላይ ደግሞ መቁሰላቸውን አገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ ያሳያል።

የካቲት 21/2018 ዓ.ም. አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱትን ጦርነት ተከትሎ አያቶላህ አሊ ኻሜኒን መገደል በመቃወም ሄዝቦላህ ወደ እስራኤል ሚሳዔል በማስወንጨፍ ውጊያውን ተቀላልሏል።

እስራኤልም የሄዝቦላህ ወታደራዊ ዒላማዎች ናቸው ያለቻቸውን ስፍራዎች መደብደብ የቀጠለች ሲሆን፣ ይህንን ተከትሎም በርካቶች ከቤታቸው ተፈናቅለው በቤይሩት ጎዳናዎች፣ በአብያተ ክርስቲያናት እና በመጠለያ ስፍራዎች ውስጥ ይገኛሉ።

በርካታ የውጭ አገር ዜጎች በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ ተሰመርተው በሚገኙባት ሊባኖስ ውስጥ ኢትዮጵያውያንም እየተካሄደ ባለው ጦርነት ለችግር መዳረጋቸውን ይናገራሉ።

ቢቢሲ ያነጋገራት በቤይሩት ውስጥ ከሦስት ልጆቿ ጋር የምትኖረው ኢትዮጵያዊት እና ቤቷ የሚገኘው በከተማዋ ውስጥ ሄዝቦላህ በሚንቀሳቀስበት አካባቢ ነው።

ይህ ዳሂይ የሚባል አካባቢ ነው አሁን ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደምም እስራኤል እና ሄዝቦላህ ፍጥጫ እና ግጭት ውስጥ በገቡ ቁጥር የጥቃት ዒላማ መሆኑን ትገልጸለች።

"ባለፈው ዓመትም ብዙ ስቃይና መከራ አሳልፈናል። በዚያ ስጋት ውስጥ ነው አሁኑ እንደተኛን ሌሊት ድብደባው የተጀመረው" ብላለች።

ይህች ኢትዮጵያዊት የምትኖርበት ሕንጻ በእስራኤል ዒላማ ውስጥ እንደነበርም ስትጠቅስ "እኛ እየወጣን ነው የምንኖርበት አፓርታማ ከኋላችን የወደቀው" ስትል ከጥቃቱ ለጥቂት መትረፋቸውን ገልጻለች።

የሦስት ልጆች እናት የሆነቸው ይህች ኢትዮጵያዊት "ልጆቼን ይዤ መሮጤን ነው እንጂ ሌላ ነገር አላስታውስም" በማለት ጥቃቱ ከባድ እንደነበር ጠቅሳለች።

"ከላይ እሳት ሲዘንብ እያየን አጠገባችን የሕንጻ ፍርስራሽ ክምር እየተመለከትን መኖር ከባድ ነው።"

የምትኖርበትን አካባቢ ለቅቃ ከወጣች አንድ ወር እያለፋት መሆኑን የምትናገረው ኢትዮጵያዊቷ እናት በወቅቱ የተፈጠረባት "ድንጋጤው ግን ከውስጣችን አልወጣም" ትላለች።

"በዚያ ላይ እናት ሲኮን ከልጆች ጋር አስቸጋሪ ነው" በጦርነት ውስጥ "ደፋር" የሚባል ሰው እንደማይኖር የምትገልጸው ይህች ኢትዮጵያዊት "ማንኛውም ሰው እኩል ልብ ነው የሚኖረው" በማለት ያለውን ሁኔታ ታስረዳለች።

በደቡባዊ ሊባኖስ ሳይዳ እና እንዳህያ አካባቢ የሚኖሩ ሁለት ኢትዮጵያውያኖች በበኩላቸው በሚኖሩበት መጠለያ አጠገብ የሚገኝ ሕንጻ ላይ ጥቃት መፈጸሙን እና መቃጠሉን ይናገራሉ።

ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ "በመጠለያ ውስጥ ነው ያለነው" የሚሉት እነዚህ እናቶች "ተስፋችን መድኃኒዓለም ነው፤ ሌላ ተስፋ የለንም" ሲሉ ስላሉበት ሁኔታ ለቢቢሲ አማርኛ ተናግረዋል።

በየዕለቱ ሁኔታዎች ከመሻሻል ይልቅ "እየባሰ ነው የሚሄደው" የሚሉት እነዚህ ኢትዮጵያውያን አንድ ወር ከአምስት ቀናት እንደሆናቸው ይናገራሉ።

በቤይሩት በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከእነ ሦስት ልጆቿ ተጠልላ የምትገኘው ኢትዮጵያዊትም ጥቃቱ በተፈጸመበት ዕለት ውጭ ማደራቸውን ታስታውሳለች።

አሁን የተጠለሉበት ቤተ ክርስቲያን ደኅንነቱ የተጠበቀ ቢሆንም እስራኤል እስራኤል በመላው ሊባኖስ የፈጸመችውን ያለውን መጠነ ሰፊ ጥቃት ተከትሎ አካባቢው "በአራት እና በአምስት ሚሳዔሎች መመታቱን" ተናግራለች።

የሚሳዔል ጥቃቱን ተከትሎ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ አቧራ እና ጭስ መግባቱን የምትናገረው ይህች ኢትዮጵያዊት "ለሕጻናቱ አፋቸውን መሸፈኛ ጭምብል አደሏቸው፤ በጣም ድንጋጤ ላይ ነበሩ ልጆቻችን" ብላለች።

ጥቃቱ በሊባኖስ የሚፈጸምበት የሰዓትም ሆነ የቦታ ገደብ እንደሌለው በመግለጽ "ዝም ብለው ነው የሚመቱት" ብላለች።

ማክሰኞ በነበረው ጥቃት በርካታ ሰዎች መጎዳታቸውን የምትገልጸው ይህች ኢትዮጵያዊት "ነዋሪዎች ያሉባቸው ሕንጻዎች ናቸው እየተመቱ ያሉት" በማለት ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጻለች።

የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋፍ ሳላም ከፍተኛ የአየር ድብደባ ከተፈጸመ በኋላ "የሊባኖስ ወዳጆች በሙሉ" የእስራኤልን ወታደራዊ እርምጃ "በሚችሉት መንገድ ሁሉ" እንዲያስቆሙ ተማጽነዋል።

ናዋፍ ሳላም በኤክስ ገጻቸው ላይ "እስራኤል በሊባኖስ በተለይም በዋና ከተማዋ ቤይሩት ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ያልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ በሕዝብ በተጨናነቁ የመኖሪያ ሰፈሮች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈጸሟን ቀጥላለች" ብለዋል።

አሜሪካ እና ኢራን ለሁለት ሳምንት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ሲደርሱ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ግን ይህ "ሊባኖስን አያካትትም" በማለት ግዙፍ ያሉትን ትቃት መፈጸም ቀጥለዋል።

ኢትዮጵያውያን በእንደዚህ ዓይነት አስቸጋሪ ወቅት ለመደጋገፍ እንዲያመቻቸው በሚል የተለያዩ ቡድኖችን ያቋቁማሉ።

የልጆች እናት የሆነችው ኢትዮጵያዊቷ እርሷም 170 በቤይሩት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እናቶች ያሉበት 'ጽናት ማዘርስ' የተሰኘ ቡድን መሥርታ እርስ በእርስ ይደጋገፋሉ።

ከእስራኤል የሚሰነዘርን ጥቃት ሸሽተው በቤተ ክርስቲያን እና ሌሎች መጠለያዎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን "ከመንግሥት ድጋፍ እንደማያገኙ" ትገልጻለች።

"መንግሥት የራሱን ዜጎች ነው የሚደግፈው" የምትለው በቤይሩት የምትኖረው ኢትዮጵያዊት "በመጠለያዎች እና በትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ ለእኛ ለስደተኞች ያ ነገር ክፍት አይሆንም። ለአገሩ ዜጋ ነው ቅድሚያ የሚሰጡት" ስትል ያለውን ሁኔታ ታብራራለች።

በመጠለያ ውስጥ ምግብ ማብሰል ስለማይፈቀድ የተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች የበሰሉ ምግቦችን ለተፈናቀሉት ሰዎች እንደሚያቀርቡ ገልጻለች።

የተደራጁ ኢትዮጵያውያንም እንዲሁ ምግብ እያዘጋጁ በመጠለያ ውስጥ እንደሚያቀርቡ ተናግራለች።

ጽናት ማዘርስ ግሩፕ በመጠለያ ውስጥ ላሉ ምግብ አብስሎ ማቅረብ ሲፈልግ የደረቅ ምግብ እርዳታ ከሚሰጡ ተቀብሎ በማብሰል ያቀርባል።

አርሷ ባለችበት የቤተ ክርስቲያን መጠለያ 200 ያህል ሰዎች የሚገኙ ሲሆኑ ከእነዚህም መካከል ኢትዮጵያውያን እናቶች እስከ 20 እንደሚሆኑ እና ልጆች ደግሞ 28 መሆናቸውን ተናግራለች።

ሀሪሳ በሚባል እና በርካታ ክርስቲያኖች በሚኖሩበት አካባቢ በሚገኙ መጠለያዎች በየቤተ ክርስቲያኑ እንደሚገኙ በመግለጽ እዚያ ያለው ሁኔታ ቤይሩት ካሉበት እነደሚሻል ታስረዳለች።

እስራኤል በሊባኖስ ላይ ጥቃት በከፈተችብ ወቅት በአገሪቱ የክረምት ጊዜ እንደነበር እንዲሁም የአየሩ ሁኔታ በጣም ይቀዘቅዝ እነደነበር እና እንደሚዘንብ ትገልጻለች።

መንገድ ላይ ድንኳን ዘርግተው ለሚኖሩ በጣም አስቸጋሪ ነው፤ ባለፉት ቀናት እየዘነበ ነበር በማለት"የአየሩ ሁኔታም ፈታኝ እንደሆነባቸው አስረድታለች።

በርካታ ኢትዮጵያውያን ከከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው እና አብዛኘው ክርስቲያን ወደ ሆነው ማኅበረሰብ ምንም እንኳን ቅዝቃዜው አስቸጋሪ ቢሆንም በዋና ከተማው ካለው የጎዳና ሁኔታ ይሻላል በሚል እንደሄዱ ጨምራ ገልጻለች።

ቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የተጠለሉት ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ የባንግላዲሽ፣ የሲሪላንካ እና የሱዳን ዜጎች መሆናቸውን ኢትዮጵያውያኑ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

_____

*ማስታወሻ፡ ቢቢሲ ከሊባኖስ ያናገራቸው ኢትዮጵያውያን ስማቸው እንዲገለጽ አልፈቀዱም