እስራኤል በመላው ሊባኖስ በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ 182 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

እስራኤል ረቡዕ ዕለት በመላው ሊባኖስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የገደለና ያቆሰለ ከፍተኛ የአየር ድብደባ ፈጸመች።

የአገሪቱ ባለሥልጣናት በኢራን የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረግም በሊባኖስ የታጠቀው የሄዝቦላህ ቡድን ላይ የሚደረገው ጦርነት ግን ቀጥሏል ብለዋል።

እስራኤል ወደ ሊባኖስ የእግረኛ ጦሯን ካሰማራች ወዲህ የተደረገ ግዙፍ የአየር ጥቃት እንደሆነ የገለፀች ሲሆን በ10 ደቂቃ ውስጥ ከ100 በላይ የሄዝቦላህ የዕዝ ማዕከላትንና ወታደራዊ ቦታዎችን መደብደቧን አስታውቃለች።

የቤይሩት ደቡባዊ ዳርቻዎች፣ ደቡባዊ ሊባኖስ እና የምሥራቅ ቤካ ሸለቆ በጥቃቱ ዒላማ ከሆኑ ቦታዎች መካከል ናቸው።

የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር ቢያንስ 182 ሰዎች መሞታቸውን አስታውቆ ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል ገልጿል።

ሚኒስቴሩ አክሎም ጥቃቱን ተከትሎ 890 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን አስታውቋል።

በቤይሩት ግዙፍ የአየር ጥቃት ከተፈጸመ ከሰዓታት በኋላ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ከሕንጻ ፍርስራሾች ውስጥ የተጎዱ ሰዎችን ይፈልጉ ነበር።

በፍርስራሹ መካከል በሕይወት የተረፉ፣ የተጎዱ፣ የሞቱ፣ በፈገግታ የተሞሉ የቤተሰቦች ፎቶዎች፣ የልብስ ቁርጥራጮች፣ ያልተጠናቀቁ የትምህርት ቤት የቤት ስራዎች ይታያሉ።

አብዱልቃደር ማህፉዝ የቆሰለውን ወንድሙን ለመጠየቅ በመጣበት ነበር።

"እዚህ ብዙ የሰውነት ክፍሎች ነበሩ። ሰዎች ብቻ ናቸው የተጎዱት። ሕዝቡ ምን ማድረግ አለበት? ምንም ማድረግ አንችልም" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ጥቃቶቹ የተፈጸሙት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ቢሮ የአሜሪካ እና የኢራንን ስምምነት ያሸማገለችው ፓኪስታን የተኩስ አቁም ስምምነት በሊባኖስ የተከሰተውን ግጭት ይሸፍናል የሚለውን ንግግራቸውን ውድቅ ካደረገ በኋላ ነው።

በዋሽንግተን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮላይን ሌቪት ሊባኖስ የስምምነቱ አካል እንዳልሆነች ተናግረዋል።

ስምምነቱ ይፋ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ምንም ዓይነት ጥቃት መፈጸሙ ያልተገለጸው ሄዝቦላህ ምላሽ የመስጠት መብት እንዳለው ገልጾ፣ የተፈናቀሉ ቤተሰቦች ወደ ቤታቸው ለመመለስ ከመሞከራቸው በፊት መደበኛ የተኩስ አቁም ስምምነት እስኪደረግ ድረስ እንዲጠብቁ አስጠንቅቋል።

የሊባኖስ ፕሬዝዳንት "ሊባኖስን በአካባቢያዊ ሰላም ውስጥ ለማካተት የሚደረገውን ጥረት" እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በሄዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል ለአስርት ዓመታት የዘለቀው ግጭት ያገረሸው ቡድኑ በኢራን ጦርነት የመጀመርያ ቀን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ በመገደላቸው እና እአአ በኅዳር 2024 የተደረሰ የተኩስ አቁም ስምምነት እያለ በሊባኖስ ላይ በየቀኑ እየተፈጸመ ያለውን የእስራኤል ጥቃት በመቃወም ሮኬቶችን በመተኮሱ ነው።

የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር በጦርነቱ ምክንያት ከ1,700 በላይ ሰዎች መገደላቸውን እና ከእነዚህም ውስጥ ቢያንስ 130 ሕፃናት እንደሚገኙበት አስታውቋል።

እስራኤል 1,100 የሚሆኑ የሄዝቦላህ ተዋጊዎችን መግደሏን ገልጻለች።

ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን ይህም ከአጠቃላይ ሕዝቡ ውስጥ ከአምስቱ አንዱ ማለት ነው።

የእስራኤል ወታደሮች የሄዝቦላህ መሠረተ ልማትን ለማፍረስ እና ተዋጊዎቹን አባርሮ የደኅንነት ቀጣና ለመመስረት በሚል በድንበሩ አቅራቢያ ያሉ መንደሮችን አውድመዋል።

ይህ ደግሞ ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላም አንዳንድ አካባቢዎች በእስራኤል ጦር እጅ ሊቆዩ እንደሚችሉ እና ብዙ ነዋሪዎች ወደ መኖሪያቸው መመለስ ላይፈቀድላቸው ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

የእስራኤል ባለሥልጣናት ከኢራን ጋር ስምምነት ቢኖርም በሊባኖስ የሚያደርጉትን ዘመቻ ለመቀጠል ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።

የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ወታደራዊ ምንጮችን ጠቅሰው እንደዘገቡት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ጦሩ በወረራው የበለጠ ለመግፋት ምንም ፍላጎት የሌለው ሲሆን ሄዝቦላህን በኃይል ትጥቅ ማስፈታት እንደማይችሉም መናገራቸው ተጠቅሷል።

ታዛቢዎች ሄዝቦላህ ባለፈው ጦርነት በከፍተኛ ሁኔታ እንደተዳከመ በሰፊው ቢታመንም በዚህ ግጭት ውስጥ ባሳየው ወታደራዊ አቅም መገረማቸውን ገልጸዋል። ቡድኑ በተደጋጋሚ ወደ ሰሜን እስራኤል ሮኬቶችን እና ድሮኖችን ከመተኮስ ባለፈ በደቡባዊ ሊባኖስ ከእስራኤል ወታደሮች ጋር ውጊያ ገጥሟል።

ይሁን እንጂ በሊባኖስ ውስጥ ሄዝቦላህ አገሪቱን ወደማይፈለግ ጦርነት በመክተት እና የኢራንን ጥቅም ለመጠበቅ በሚል በግጭት ውስጥ በመሳተፉ ብዙዎች ተጠያቂ ያደርጉታል።

ሄዝቦላህ አሁንም በሊባኖስ ሺዓዎች ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ አለው።

ጦርነቱን ተከትሎ በርካቶች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን ትምህርት ቤቶች ወደ መጠለያነት ተቀይረዋል።

በርካቶች በሕዝብ መሰብሰቢያ ስፍራዎች በወጠሯቸው ድንኳኖች እና በመኪናዎች ውስጥ ለመተኛት ተገድደዋል።

ተፈናቃዮች ወደ ሌሎች ማኅበረሰቦች ዘንድ መምጣታቸው የእስራኤል ጥቃት ሰለባ እንሆናለን በሚል የጎሳ ውጥረቶች እንዲባባሱ ምክንያት ሆኗል።

እአአ በ2024 የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረገ በኋላ የሊባኖስ መንግሥት ሄዝቦላህን ትጥቅ ለማስፈታት ዕቅድ እንዳለው አስታውቋል።

ይህ እቅድ እስራኤል በ15 ዓመታት የሊባኖስ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ሊባኖስን በመውረሯ ምክንያት በ1980ዎቹ የተፈጠረ ነው። ነገር ግን እስካሁን ድረስ ቡድኑ የጦር መሳሪያዎቹ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ለመወያየት ፈቃደኛ አልሆነም።

የቀድሞው የጦር አዛዥ የነበሩት ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አውን ይህ መከፋፈልን ሊያባብስና ወደ አመፅ ሊያመራ እንደሚችል በማስጠንቀቅ ኃይል መጠቀምን አውግዘው ነበር። አዲስ ለተቀሰቀሰው ግጭት በሰጡት አስተያየትም ምንም እንኳን አገራቱ ዲለፕሎማሲያዊ ግንኙነት ባይኖራቸውም መንግሥታቸው ከእስራኤል ጋር በቀጥታ ለመደራደር ክፍት መሆኑን ተናግረዋል።

ነገር ግን እስራኤል እስካሁን ድረስ የቀረበውን ግብዣ ችላ ብላዋለች።