እስራኤል ከወራት በኋላ በቤይሩት በፈፀመችው አዲስ ጥቃት ከፍተኛ የሔዝቦላህ ባለሥልጣንን ገደለች

በእስራኤል ጥቃት ጉዳት የደረሰበት የመኖሪያ ሕንጻ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የእስራኤል ጦር በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ደቡባዊ ዳርቻ ላይ በፈጸመው ጥቃት የሔዝቦላህ ከፍተኛ ባለሥልጣንን ገደለች።

የተገደሉት ባለሥልጣን የሔዝቦላህ ዋና ኢታማዦር ሹም ሀይታም አሊ አል ታታባይ መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን ቡድኑን በተለያዩ ከፍተኛ የሥልጣን እርከኖች ላይ ሲያገለግሉ የነበሩ ናቸው ተብሏል።

የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር፤ በዳሂ ዲስትሪክት የመኖሪያ ህንጻ ላይ በተፈጸመ ጥቃት በትንሹ አምስት ሰዎች መገደላቸውን እና 28 ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቋል።

ሔዝቦላህ የታታባይን ሞት አረጋግጦ፣ እስራኤል ጥቃቱን በመፈጸም "ቀይ መስመር" አልፋለች ብሏል።

የእስራኤል ጦር ከወራት በኋላ በደቡባዊ ቤይሩት ጥቃት ሲፈጽም ይህ የመጀመርያው ነው።

ባለፈው ኅዳር ወር በዩናይትድ ስቴትስ እና በፈረንሳይ አደራዳሪነት የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረግም እስራኤል በኢራን ከሚደገፈው ሔዝቦላህ ጋር ግንኙነት አላቸው ያለቻቸውን ሰዎች እና ተቋማት ማጥቃቷን አጠናክራ ቀጥላለች።

የእስራኤል ባለሥልጣናት ሔዝቦላህ ወታደራዊ አቅሙን ዳግም ለማጠናከር እየሞከረ ነው በማለት ይከስሳሉ።

አክለውም የጦር መሣሪያ ወደ ሊባኖስ እያስገባ እና በሮኬቶች እና ሚሳዔሎች ምትክ የሚፈነዱ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እያመረተ መሆኑን በመጥቀስ ግጭት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን ይገልጻሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከጥቃቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ "በእኔ መሪነት የእስራኤል መንግሥት ሔዝቦላህ አቅሙን መልሶ እንዲያጠናክር፤ በእስራኤል መንግሥት ላይም ስጋት እንዲፈጥር አንፈቅድም" ብለዋል።

የሊባኖስ መንግሥት "ሔዝቦላን ትጥቅ ለማስፈታት የገባውን ግዴታ ይፈጽማል" ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

የሊባኖሱ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አውን በደቡባዊ ሊባኖስ ቢያንስ አምስት ቦታዎችን በቁጥጥሯ ሥር አድርጋ የምትገኘው እስራኤል፤ የምትፈጽመውን ጥቃት እንድታቆም እና ከአገሪቱ ለቅቃ እንድትወጣ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና እንዲያደርግ አሳስበዋል።

የእስራኤል ድርጊት ለ13 ወራት ግጭት ያስቆመውን ስምምነት የጣሰ ነው ሲሉም ኮንነዋል።

የሊባኖስ መንግሥት ሔዝቦላህን ትጥቅ ለማስፈታት ቃል ገብቷል።

ነገር ግን ቡድኑ እስራኤል ጥቃቷን ሳታቆም፣ ከሊባኖስ ሙሉ በሙሉ ለቅቃ ሳትወጣ እና ሊባኖሳዊያን እስረኞችን ሳትለቅ ስለ ትጥቅ መፍታት እንደማይወያይ አስታውቋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የምዕራባውያን አገር ዲፕሎማት ለቢቢሲ እንደተናገሩት የሊባኖስ ባለሥልጣናት በትራምፕ አስተዳደር ግፊት እየደረሰባቸው ነው።

ዩናይትድ ስቴትስ እና ዩናይትድ ኪንግደም እንደ አሸባሪ ድርጅት በሚቆጠሩት ሔዝቦላህ ላይ እየታየ ያለው አዝጋሚ ለውጥ የትራምፕ አስተዳደርን ትዕግሥት እያሟጠጠው መሆኑን ዲፕሎማቱ ጠቅሰዋል።

በእስራኤል እና በሔዝቦላህ መካከል በድጋሚ ግጭት የተቀሰቀሰው ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ አማጺ ቡድኑ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን ማስወንጨፍ በመጀመሩ ነው።

ሔዝቦላህ ከጥቃቱ በኋላ በጋዛ ከሚገኙ ፍልስጤማውያን ጎን መቆሙን ተናግሯል።

ከዚያ ወዲህ እስራኤል በአገሪቱ ላይ በፈጸመችው መጠነ ሰፊ ጥቃት ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ 4,000 የሚጠጉ ሰዎችን መገደላቸውን እና ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የሊባኖስ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

እስራኤል በበኩሏ በጦርነቱ ከ80 በላይ ወታደሮቿ እና 47 ንፁኃን ዜጎቿ መገደላቸውን አስታውቃለች።

የአሜሪካ መንግሥት በታታባይ ላይ እአአ በ2016 ማዕቀብ ጥሎ በአሸባሪነት ፈርጇቸዋል። ስለ ግለሰቡ መረጃ ለሚሰጠው ማንኛውም ግለሰብ የ5 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት አቅርቦ ነበር።

አሜሪካ ታታባይ በአንድ ወቅት በሶሪያ እና በየመን የቡድኑን ልዩ ኃይል ሲያዙ የነበሩ እና የሔዝቦላህ ቁልፍ ወታደራዊ መሪ መሆናቸውን ገልጻ፣ በእነዚህ አገራት ያከናወኗቸው ተግባራት ሔዝቦላህ "ቀጠናውን ለማመስ የሚያደርገው እንቅስቃሴ አካል ናቸው" ብላ ነበር።