የአሜሪካ ፍርድ ቤት ትራምፕ በአገራት ላይ የጣሉትን አብዛኛውን ታሪፍ "ሕገ ወጥ" ሲል ብይን ሰጠ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በበርካታ አገራት ላይ የተጣሏቸው አብዛኞቹ ታሪፎች ሕገ ወጥ ናቸው ሲል ብይን ሰጠ።
ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያስተላለፈው የፕሬዚደንቱን የውጭ ፖሊሲ አጀንዳቸውን ሊያሻሽል የሚችሉ ክርክሮችን ካደመጠ በኋላ ነው።
ውሳኔው ትራምፕ በአብዛኛው የዓለም አገራት ላይ "በአጸፋ" የጣሉት ታሪፍ ላይ እንዲሁም በቻይና ፣ በሜክሲኮ እና በካናዳ ላይ በጣሉት ታሪፎች ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር ነው።
የፌዴራል ጉዳዮችን የሚመለከተው የአሜሪካ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ሰባት ለአራት በሆነ ድምጽ ባሳለፈው ውሳኔ፣ፕሬዚደንት ትራምፕ ታሪፉ የተጣለው 'አስቸኳይ የኢኮኖሚ ኃይል ሕግ' መሠረት ነው ሲሉ ያቀረቡትን መከራከሪያ ሃሳብ " ከሕግ ጋር የሚጻረር" ሲል ውድቅ አድርጎታል።
የትራምፕ አስተዳደር ውሳኔውን ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ጊዜ ለመስጠትም የፍርድ ቤቱ ውሳኔ እስከ አውሮፓውያኑ ጥቅምት 14 ድረስ ተግባራዊ እንደማይሆን ተገልጿል።
ትራምፕ በይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ የተላለፈውን ውሳኔ " ይህ ውሳኔ እንዲጸና ከተፈቀደ አሜሪካን ያጠፋታል" ሲሉ በትሩዝ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ተችተውታል።
" ዛሬ በጣም ደጋፊያችን የሆነው የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በስህተት የጣልነውን ታሪፍ መነሳት አለበት ብሏል፤ ሆኖም በመጨረሻም አሜሪካ እንደምታሸንፍ ያውቃሉ።" ብለዋል በገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ።
ጨምረውም " እነዚህ ታሪፎች ቢነሱ አጠቃላይ ለአገሪቱ አደጋ ነው፣ በፋይናንስ ደካማ ያደርገናል እና ጠንካራ መሆን አለብን" ብለዋል ትራምፕ።
ትራምፕ ታሪፉን የጣሉት በአውሮፓውያኑ 1977 በጸደቀው ዓለም አቀፉ የአስቸኳይ የኢኮኖሚ አቅም ሕግ ( አይኢኢፒኤ) መሠረት እንደሆነ አስረድተዋል።ይህ ሕግ ፕሬዚደንቶች ብሔራዊ አዋጅ ካወጁ በኋላ ያልተለመዱ እና የተለዩ ስጋቶችን ለማስወገድ እርምጃ እንዲወስዱ ሥልጣን የሚሰጥ ነው።
ትራምፕም የንግድ ሚዛን ጉድለት ለአገሪቷ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ነው ሲሉ በንግድ ላይ አስቸኳይ ብሔራዊ አዋጅ አውጀዋል።
ሆኖም ፍርድ ቤቱ ታሪፍ መጣል የምክር ቤቱ ዋና ሥልጣን እንጂ የፕሬዚደንቱ አይደለም ሲል ውሳኔ አሳልፏል።
127 ገጾች ያሉት የፍርድ ቤቱ ውሳኔ አይኢኢፒኤ " ታሪፍም ሆነ ተመሳሳይ ነገር አልጠቀሰም፤ ወይም የፕሬዚደንቱ ታሪፍ የመጣል ሥልጣን ላይ ግልጽ ገደቦችን የያዙ መከላከያዎች የሉትም " ብሏል።
በመሆኑም ግብር እና ታሪፍ የመጣል ሥልጣን የምክር ቤቱ ነው ሲል የአይኢኢፒኤ ሕግ ይህንን ሊሽረው እንደማይችል ውሳኔው አስረድቷል።
ፍርድ ቤቱ ይህን ብይን የሰጠው አነስተኛ የንግድ ተቋማት እና የአሜሪካ ግዛቶች ጥምረት ባቀረቡት ሁለት ክሶች ላይ በሰጠው ምላሽ ነው።
ክሱ የቀረበው ትራምፕ በዓለም አገራት ላይ የ10 በመቶ መነሻ ቀረጥ እንዲሁም በበርካታ አገራት ላይ በምላሹ ታሪፎች እንዲጣል ምክንያት የሆነውን የሥራ አስፈፃሚ ትዕዛዝ ሚያዝያ ወር ላይ ካስተላለፉ በኋላ ነው።
ትራምፕ ይህንን ውሳኔ ያሳለፉበትን እለት አሜሪካ ፍትሃዊ ካልሆነ የንግድ ፖሊሲዎች የተላቀቀችበት "የነጻነት ቀን" ብለውታል።
ግንቦት ወር ላይ ተቀማጭነቱን በኒው ዮርክ ያደረገው ዓለም አቀፍ የንግድ ፍርድ ቤት ትራምፕ የጣሉትን ታሪፍ "ሕገ ወጥ" ብሎት ነበር።ሆኖም ውሳኔው በይግባኝ ሒደት እንዲቆይ ሆኗል።
አርብ ዕለት በይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ የተላለፈው ብይን ከታሪፎቹ በተጨማሪም ትራምፕ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ አደንዛዥ እፅ ለማስቆም ወሳኝ ነው ሲሉ በካናዳ፣ በሜክሲኮ እና በቻይና ላይ የጣሉትን ታሪፍ ውድቅ አድርጎታል።
ሆኖም ውሳኔው በተለያዩ የፕሬዚደንቱ ሥልጣን መሠረት የሚገቡ እንደ ብረትና አልሙኒየም ባሉ ቁሶች ላይ ተግባራዊ አይሆንም።
የይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በውሳኔው ፕሬዚደንቱን ሽንፈት ቢያከናንብም ከፍርድ ቤቱ 11 ዳኞች መካከል ሦስቱ ብቻ በሪፐብሊካኖች የተሾሙ በመሆናቸው ዋይት ሃውስ ሊጽናና ይችላል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ግን ስድስት ሪፐብሊካን ዳኞች ያሉት ሲሆን ሦስቱ በፕሬዚደንት ትራምፕ የተመረጡ ናቸው።















