የአሜሪካ ግዛት ያለ ሐኪም ማዘዣ የፅንስ ማቋረጫ መድኃኒቶችን መያዝ ወንጀል ልታደርግ ነው

ሚፌፕሪስተን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካዋ ግዛት ሉዊዚያና ሁለት የፅንስ ማቋረጫ እንክብሎችን ያለ ሐኪም ማዘዣ ይዞ መገኘትን ቅጣት የሚያስከትል ወንጀል ልታደርግ ነው።

ሉዊዚያና እነዚህን በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉ የፅንስ ማቋረጫ እንክብሎችን ቁጥጥር የሚደረግባቸው አደገኛ መድኃኒቶች አድርጋ በመፈረጅ የመጀመሪያዋ የአሜሪካ ግዛት ትሆናለች።

ሚፌፕሪስተን እና ሚሶፐሮስቶል የተባሉትን እነዚህን ሁለት እንክብሎች ካለሐኪም ማዘዣ ይዞ የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ እስር እና በሺዎች የሚቆጠር የዶላር ቅጣት ይጠብቀዋል።

ከፅንስ ማቋረጥ በተጨማሪ ለሌሎችም ሕክምናዎች የሚውሉትን እንክብሎች ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግባቸው እንዲሆኑ የሚያዘው ሕግ በግዛቲቱ ሁለቱም ምክር ቤቶች ተቀባይነት አግኝቶ አልፏል።

በአሜሪካ በስፋት ጥቅም ላይ በሚውሉት መድኃኒቶች ላይ ሉዊዚያና ግዛት የወሰደችው እርምጃ ሌሎችም ግዛቶች ተግባራዊ ሊያደርጉት ይችላሉ ሲሉ ፅንስ ማቋረጥን የሚደግፉ ወገኖች ስጋታቸውን ገልጸዋል።

“ቁጥጥር የሚደረግባቸው አደገኛ መድኃኒቶች” የሚለው ፍረጃ በዋናነት ተግባራዊ የሚደረገው ቫሊየም እና ዛናክስን በመሳሰሉ በጥንቃቄ ካልተወሰዱ ሱስን በሚያስከትሉ መድኃኒቶች ላይ ነው።

ሉዊዚያና ግዛት ያወጣቸው አዲሱ ሕግ ከሐኪም ማዘዣ ውጪ እንክብሎቹን ይዞ መገኘትን የሚከለክል ሲሆን፣ ከዚህ ውጪ ከሆነ ግን የገንዘብ እና የእስር ቅጣት ይከተላል።

ሁለቱ መድኃኒቶች በአሜሪካ የመድኃኒት እና ምግብ አስተዳደር ከ20 ዓመት በፊት አስከ 10 ሳምንታት የሆነውን ፅንስ ለማቋረጥ ጥቅም ላይ እንዲውል ፍቃድ አግኝተዋል። መድኃኒቶቹ በአንድ ላይ የሚወሰዱ ሲሆን መጀመሪያ ፅንስ ለማቆረጥ ሚፌፕሪስተን ከዚያም ሚሶፐሮስቶል ደግሞ ፅንሱን ከማህጸን ለማስወጣት ጥቅም ላይ ይውላል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በተጨማሪም ሚሶፐሮስቶል የሆድ ውስጥ ቁስለትን እና ከወሊድ በኋላ የሚከሰት ደም መፍሰስን ለማከም በሐኪም ትዕዛዝ በተናጠል ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል።

የሉዊዚያና ግዛት አዲሱ ሕግ መጀመሪያ ላይ ትኩረቱ ለአንዲት ሴት ሳታውቅ ፅንስ ማቋረጫ እንክብል መስጠትን ወንጀል ለማድረግ ያሰበ ነበር፤ ኋላ ላይ ግን መድኃኒቶቹን ቁጥጥር የሚደረግባቸው እንዲሆኑ የማድረግ ሃሳብ ተካቶበታል።

ነገር ግን አሁንም ድረስ አብዛኞቹ የፅንስ ማቋረጥ ድርጊቶች በሉዚያና ግዛት ውስጥ ሕገ ወጥ ናቸው። አዲሱ ሕግም በመላዋ አሜሪካ ከሚፈጸሙ የፅንስ ማቋረጦች መካከል ከግማሽ በላይ ለሚሆኑት የሚውሉትን እነዚህን መድኃኒቶች በግዛቲቱ ውስጥ የማግኘት ዕድልን ይገድባል።

ፀረ ፅንስ ማቋረጥ ቡድኖች የግዛቲቱን እርምጃ ያወደሱ ሲሆን፣ መድኃኒቶቹ ከፅንስ ማቋረጥ ውጪ ለሌሎች ሕክምናዎች ጥቅም ላይ የሚውሉ መሆናቸውን በመጥቀስ ከሕጉ አንጻር ሐኪሞች ስጋታቸውን ገልጸዋል።

አንዳንድ የፅንስ ማቋረጥ መብት ተከራካሪዎች ደግሞ ሕጉ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ ሌሎች ግዛቶችም እንደምሳሌ ሊመለከቱት እና እገዳ ሊጥሉ ይችላሉ የሚል ስጋት አላቸው።

ከቀናት በፊት የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ፣ አዲሱን የሉዚያና ግዛት ሕግ “ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ” በማለት የጠሩት ሲሆን፣ ለዚህም የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ተጠያቂ አድርገዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቷ ትራምፕን የወቀሱት በአሜሪካ ውስጥ ፅንስ ማቋረጥን መብት ያደረገውን ሕግ ከሁለት ዓመት በፊት ውድቅ ካደረጉት የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች መካከል አብዛኞቹን በሥልጣን ዘመናቸው በመሾማቸው ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመጪዎቹ ሳምንታት በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የሚፌፕሪስተን እንክብል አቅርቦትን በተመለከተ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።