ዣቪ በውድድር ዘመኑ መጨረሻ ባርሴሎናን እንደሚለቅ ይፋ አደረገ

ዣቪ

የባርሴሎናው አሠልጣኝ ዣቪ በውድድር ዘመኑ መጨረሻ ባርሴሎናን እንደሚሰናበት ገለጠ።

የቀድሞው የባርሴሎና እና የስፔን አማካይ በአውሮፓውያኑ 2021 ነው የካታላኑ ክለብ አሠልጣኝ ሆኖ የተሾመው።

ከዚያ ቀደም የካታሩ አል ሳድ ክለብ አሠልጣኝ ሆኖ ሠርቷል።

ምንም እንኳ በ2022 ባርሴሎና ላ ሊጋውን እንዲያነሳ ቢያስችልም ቅዳሜ ምሽት በቪያሪያል 5-3 መረታቱ ለውሳኔው ምክንያት ሆኗል።

ባርሴሎ ላ ሊጋውን ከሚመራው ሪያል ማድሪድ 10 ነጥብ ዝቅ ብሎ ተቀምጧል።

“ለክለቡ ሁሉን ነገር ሰጥቻለሁ። ከራሴ ሁሉ አስቀድሜዋለሁ። የምችለውን ሁሉ ነገር አድርጊያለሁ” ብሏል ዣቪ።

“ደጋፊዎችን ለማስደሰት አሁንም የአቅሜን ማድረግ እቀጥላለሁ።”

የባርሴሎና ተጫዋች እያለ ከክለቡ ጋር 25 ዋንጫዎችን ያነሳው የ44 ዓመቱ ዣቪ ኮንትራቱ አንድ ዓመት ቢቀረውም በሰኔ ወር መጨረሻ በይፋ ክለቡን ይሰናበታል።

በአውሮፓውያኑ 2010 ከስፔን ጋር የዓለም ዋንጫ የበላው ዣቪ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከባርሴሎናው ፕሬዝደንት ዮዋን ላፖርታ ጋር ተመካክሮ እንደሆነ ገልጧል።

“ክለቡ ለውጥ ይፈልጋል ብዬ አምናለሁ” ይላል ዣቪ።

“ለተጫዋቹም ጥሬ ነው። ነፃ ሆነው ይጫወታሉ። በጣም ጫና ውስጥ ሆነን ነው የምንጫወተው። የክለቡ አስተዳዳሪዎችም ቢሆኑ አዲስ ነገር ያስፈልጋቸዋል ብዬ አስባለሁ። ይህ ነው መልዕክቴ። ትክክለኛውን ነገር እያደረግኩ እንደሆነ ይሰማኛል።”

ዣቪ፤ በስፔን ሱፐር ካፕ ፍፃሜ ባርሴሎና በሪያል ማድሪድ 4-1 ከተረታ በኋላ “ተጫዋቾቼ በኔ እምነት ከሌላቸው ሻንጣየን እሸክፋለሁ” ብሎ ነበር።

ነገር ግን ከዚህ ጨዋታ በኋላ ባርሴሎና ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን ቢረታም በአትሌቲክ ቢልባዎ ተረትቶ ከኮፓ ዴል ሬይ ውጭ ሆኗል።

ቅዳሜ ደግሞ በላ ሊጋው በገዛ ሜዳው በቪያሪያል 5-3 ተሸንፏል።

አሠልጣኙ አክሎ ሥራውን እጅግ አድካሚ በሆነበት ወቅት ለመልቀቅ መወሰኑ ለአእምሮ ጤናውም የሚበጅ እንደሆነ ይናገራል።

“ባርሴሎና ውስጥ ሁሌም ዋጋ እንደሌለህ ነው የምታስበው። ክለቡ የሚሠራው እንደዚህ ነው” ብሏል።

ባርሴሎና በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ከናፖሊ ጋር የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ይጠብቀዋል።

“ቻምፒዮንስ ሊግ ብበላ እንኳ ውሳኔዬን አልቀይርም። ለተጫዋቾቹ እነግራቸዋለሁ። እኔ ኃላፊነት የሚሰማኝ ሰው ነኝ። ተጫዋቾቹ አሁን ነፃ እንደሚሆኑ አስባለሁ።”

የስፔን እግር ኳስ ተንታኙ ጉሌም ባላግ ዣቪ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የክለቡ ፕሬዝደንት ዮዋን ላፖርታ ባደረሱበት ጫና ነው ይላል።

ዣቪ የባርሴሎና ተጫዋች ሳለ በ767 ጨዋታዎች 85 ጎሎች አስቆጥሯል።