ሳንፍራንሲስኮ ለፖሊሶች ‘ገዳይ ሮቦቶችን’ እንዲጠቀሙ ልትፈቅድ ነው

ሮቦቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሳንፍራንሲስኮ የተቆጣጣሪዎች ቦርድ የከተማዋ ፖሊስ የሰው ህይወትን ሊያጠፉ የሚችሉ ሮቦቶችን እንዲጠቀም ድምጽ ሰጥቷል።

እርምጃው ፖሊስ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሲሆን ፈንጂዎች የታጠቁ ሮቦቶችን እንዲያሰማራ ይፈቅዳል።

የከተማዋ ፖሊስ ኤስኤፍፒዲ ለቢቢሲ እንዳስታወቀው በአሁኑ ወቅት ገዳይ መሳሪያዎች የተገጠመላቸው ሮቦቶችን እየተጠቀሙ አለመሆኑን ነው።

ሆኖም ለወደፊቱ የታጠቁና ሊገድሉ የሚችሉ ሮቦቶችን ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

“በአደገኛ የታጠሩና በትጥቅ የተሞሉ ምሽጎችን ለመጣስ ሮቦቶች ፈንጂዎች ወይም ተቀጣጣይ መሳሪያዎች ሊታጠቁ ይችላሉ” በማለት የፖሊስ ቃለ አቀባይ ገልጸዋል።

አክለውም ሮቦቶች “የሰዎች ህይወት ላይ አደጋ የጋረጡ ዓመጸኞች፣ የታጠቁ ወይም አደገኛ ተጠርጣሪዎችን ለማዳከም ወይም አደጋ እንዳያደርሱ ለማድረግ ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ” ብለዋል።

እርምጃውን የደገፉ ተሟጋቾች እነዚህ ሮቦቶች በጣም ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ብቻ ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ተናግረዋል።

ተቃዋሚዎች በበኩላቸው ባለስልጣኑ የፖሊስ ኃይልን በበለጠ ለማስታጠቅ የሚያደርገው ጥረት ነው ሲሉ ተችተዋል።

ውሳኔው ማክሰኞ እለት የተወሰነ ማሻሻያ ተደርጎበት እንዲጸድቅ ተደርጓል።

በዚህም ማሻሻያ መሰረት ፖሊሶች እነዚህን ሮቦቶች መጠቀም የሚችሉት አማራጭ የሚሏቸውን ግጭት የማቀዝቀዣ ስልቶችን በሙሉ አሟጠው ከተጠቀሙ በኋላ ነው።

ቦርዱ ውስጥ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖች ብቻ ሮቦቶችን የመጠቀም ትዕዛዝ መፍቀድ እንደሚችሉም ደንግጓል።

እንደነዚህ ዓይነት ገዳይ ሮቦቶች በሌሎች የአሜሪካ ክፍሎች ጥቅም ላይ ውሏል።

በአውሮፓውያኑ 2016 በዳላስ ቴክሳስ ፖሊስ ሲ-4 የተሰኘ ፈንጂ የታጠቀውን ሮቦት በመጠቀም ሁለት ፖሊሶችን ገድሎ በርካቶችን ያቆሰለውን አልሞ ተኳሽ ለመግደል ተጠቅሞበታል።

ኤስኤፍፒዲ በአሁኑ ወቅት ገዳይ መሳሪያዎች የተገጠመላቸው ሮቦቶች የሌሉት ሲሆን ለወደፊቱ ግን እንደሚያስፈልግም አስታውቋል።