በሙዚቃ ድግስ ላይ ከሥራ ባልደረባው ጋር ተቃቅፎ የታየው የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ኃላፊ ከሥራው ለቀቀ

የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በኮልድፕሌይ ኮንሰርት ላይ አንዲት ሴት የሥራ ባልደረባውን አቅፎ በትልቁ ስክሪን ላይ ከታየ በኋላ ሥራ መልቀቁን ተገለፀ።
ግለሰቡ ያስተዳድረው የነበረው የቴክኖሎጂ ኩባንያ፣ አስትሮኖመር ባወጣው መግለጫው "አንዲ ባይሮን የሥራ መልቀቂያ አስገብቷል፤ የዳይሬክተሮች ቦርድም ጥያቄውን ተቀብሏል" ብሏል።
ኮልድፕሌይ የተሰኘው የሙዚቃ ባንድ በማሳቹሴትስ ፎክስቦሮው ባቀረበው የሙዚቃ ድግስ ላይ አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት ተቃቅፈው ሳሉ በካሜራ ዕይታ ውስጥ ገብተው በትልቅ ስክሪን ላይ ታይተዋል።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ጥንዶቹ የአስትሮኖመር ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆነው ባይሮን እና የኩባንያው የሰው ኃይል አስተዳዳሪ የሆነችው ክሪስቲን ካቦት መሆናቸውን ዘግበዋል።
ቢቢሲ በቪዲዮው ውስጥ የሚታዩትን የሁለቱንም ሰዎች ማንነት በተናጥል ማረጋገጥ አልቻለም።
ቅዳሜ ዕለት ኩባንያው ባወጣው መግለጫ "ከዚህ ቀደም እንደተገለጸው፣አስትሮኖመር ከምስረታው ጀምሮ ለሚመራበት እሴቶች እና ባህሎች ቁርጠኛ ነው።መሪዎቻችን በሥነ ምግባርም ሆነ በተጠያቂነት አርአያ እንዲሆኑ ይጠበቃል፤ እና በቅርቡ ይህ መስፈርት ሊሟላ አልቻለም።"
መቀመጫውን በኒውዮርክ ያደረገው ኩባንያው ቦርዱ ቀጣዩን ድርጅቱን የሚመራ ኃላፊ ፍለጋ እንደሚጀምር እና ዋና የምርት ኦፊሰር በጊዜያዊነት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው እንደሚያገለግሉ ተናግሯል።
ጥንዶቹ ረቡዕ ምሽት በነበረው የኮልድፕሌይ የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ተቃቅፈው እየተዝናኑ ሳለ በካሜራ እይታ ውስጥ እንደገቡ በፍጥነት ለመደበቅ ሲሞክሩ የሚያሳየው ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አይተውታል።
ጥንዶቹን ከካሜራ ዕይታ ሲሸሹ እና ሲደበቁ የተመለከተው የኮልድፕሌይ ድምጻዊ ክሪስ ማርቲን ለተሰበሰበው ሕዝብ "ወይ የድብቅ ግንኙነት ላይ ናቸው፤ ወይም በጣም ዓይን አፋር ናቸው" ብሎ ነበር።
አስትሮኖመር በሁለቱ ግለሰቦች ግንኙነት ላይ ምርመራ መጀመሩን አስታውቆ፣ ቪዲዮው በበርካቶች ዘንድ ከታየ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ፈቃድ እንዲወጣ አድርጎ ነበር።















