ኢራናዊቷ የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ተጨማሪ እስራት እንደተፈረደባት ጠበቃዋ ተናገሩ

ናርጌስ ሞሃምዲ በቁጥጥር ሥር የዋለችው በታህሳስ ወር በአንድ መታሰቢያ ዝግጅት ላይ "ቀስቃሽ ንግግር" በማድረጓ ነበር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ናርጌስ ሞሃምዲ በቁጥጥር ሥር የዋለችው በታህሳስ ወር በአንድ መታሰቢያ ዝግጅት ላይ "ቀስቃሽ ንግግር" በማድረጓ ነበር
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የሰላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊዋ ናርጌስ ሞሃመዲ በኢራን ፍርድ ቤት ተጨማሪ የሰባት ዓመት ከስድስት ወር እስራት እንደተፈረደባት ጠበቃዋ ተናገሩ።

ሙስጣፋ ኒሊ እሁድ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በለጠፉት መግለጫ ላይ የሰብአዊ መብት ተሟጋቿ "በመሰብሰብና በወንጀል ተግባር በመተባበር" ስድስት ዓመት፣ እንዲሁም "በፕሮፓጋንዳ እንቅስቃሴዎች" አንድ ዓመት ተኩል በሰሜን ምሥራቅ ማሽሃድ ከተማ በሚገኝ ፍርድ ቤት ተፈርዶባታል።

ሞሃመዲ በታህሳስ ወር በመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ላይ "ቀስቃሽ ንግግሮችን" በማድረጓ በቁጥጥር ሥር መዋሏን በወቅቱ የኢራን ባለሥልጣናት ተናግረው ነበር።

ቤተሰቦቿ በቁጥጥር ስር በዋለችበት ወቅት ከተደበደበች በኋላ ወደ ሆስፒታል እንደተወሰደች ተናግረዋል።

የ53 ዓመቷ ኢራናዊት በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጭቆና በመቃወም ባደረገቻቸው እንቅስቃሴዎች እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2023 የኖቤል የሰላም ሽልማት ተሸላሚ ሆናለች።

ከታህሳስ 14 ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሞሃመዲ ጋር የተገናኘችው ጠበቃዋ ኒሊ፣ አገሪቱን ለቅቃ እንዳትወጣ ለሁለት ዓመታት እገዳ እንደተጣለባት እና ወደ ምሥራቃዊው ኩሽፍ ክልል ለሁለት ዓመታት በግዞት እንትሄድ መወሰኑን ተናግረዋል።

እሷን የሚደግፈው የናርጌስ ፋውንዴሽን ቅዳሜ ዕለት የተካሄደውን ችሎት "ማጭበርበሪያ" ሲል ገልጾታል፤ እንዲሁም ከየካቲት 2 ጀምሮ የረሃብ አድማ እንደጀመረች ይፋ አድርጓል።

ኒሊ ከሦስት ቀናት በፊት ወደ ታሰረችበት ማረሚያ ቤት ከመመለሷ በፊት "በአካላዊ ሁኔታዋ ምክንያት" ወደ ሆስፒታል ተወስዳ እንደነበር ተናግረዋል

ከሞሃመዲ ጋር በስልክ አየተነጋገሩ በነበረበት ወቅትም "ክስተቶቹን እና እንዴት እንደታሰረች ማስረዳት ስትጀምር ስልኩ ተቋረጠ" ሲሉ ሁኔታውን በመግለጫቸው ላይ አስረድተዋል።

የሞሃመዲ የትዳር አጋር ታጊ ራህማኒ ችሎት ፊት በቀረበችበት ወቅት "ይህ የፍትህ አካል ሕጋዊነት የለውም" በሚለው "ጽኑ" እምነቷ እና ሂደቱ "አስቀድሞ ፍጻሜው የተወሰነ" መሆኑን በመግለጽ ምንም ዓይነት መከላከያ እንዳላቀረበች ተናግሯል።

"ምንም እንኳን እንድትገኝ ብትገደድም ምንም ነገር ከመናገር ተቆጥባለች። አንድም ቃል አልተናገረችም፣ አንድም ወረቀት አልፈረመችም።"

ለቢቢሲ የተሰጠውን ፍርድ በተመለከተ ሲናገር "ጭካኔ የተሞላበት እና በጣም ኢ-ፍትሃዊ" ሲል ገልጾታል።

የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችም ውሳኔውን እንዲቃወሙ ጥሪ አቅርቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሞሃመዲ ልጅ ኪያና ራህማኒ የእናቷ ሁኔታ "በጣም እንዳሳሰባት" ተናግራለች።

ሞሃመዲ ከ10 ዓመታት በላይ በእስር ቤት አሳልፋለች። የናርጌስ ፋውንዴሽን አሁን የተጣለባት ተጨማሪ የእስር ጊዜ በአጠቃላይ በእስር የምታሳልፋቸውን ጊዜያት ወደ 44 ዓመታት ከፍ ያደርገዋል።

ከ2021 ጀምሮ "በመንግሥት ላይ የፕሮፓጋንዳ እንቅስቃሴ" እና "የመንግሥት ደህንነት በመጻረር" በሚል ክስ 13 ዓመት ታስራለች፤ እርሷ ግን የቀረቡባትን ክሶች በሙሉ ውድቅ አድርጋለች።

አክቲቪስቷ በታህሳስ 2024 በሕክምና ምክንያት ለሦስት ሳምንታት ከቴህራን አደገኛ የኤቪን እስር ቤት በጊዜያዊነት ተለቅቃ ነበር።

ብዙም ሳይቆይ ወደ እስር ቤት እንድትመለስ የተደረገ ሲሆን በዚያም የተጣለባትን ተደራራቢ የእስር ጊዜ እንድትጨርስ ተደርጋለች።