በአንጎላ የነዳጅ ጭማሬ ምክንያት በተነሳው የአደባባይ ተቃውሞ ቢያንስ 22 ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በአንጎላ የነዳጅ ጭማሬ ምክንያት በተነሳው የአደባባይ ተቃውሞ አንድ ፖሊስን ጨምሮ 22 ሰዎች ሲገደሉ 200 ግለሰቦች መቁሰላቸውን የአገር ውስጥ ሚኒስትር ማኑኤል ሆመም ገልጸዋል።
በአገሪቱ የተደረገው የነዳጅ ጭማሬ ጋር ተያይዞ ሰኞ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ 1 ሺሀ 200 ተቃዋሚዎች መታሰራቸውን ፖሊስ አስታወቋል።
በታክሲ አሽከርካሪዎች አነሳሽነት የተጀመረው የአደባባይ ተቃውሞ በመላው አገሪቱ የተዛመተ ሲሆን አገሪቱም በቅርብ ዓመታት ውስጥ ካየችው ከፍተኛው እንደሆነ ተገልጿል።
በአገሪቱ ያሉ ትልልቅ የንግድ አንቅስቃሴዎች የቆሙ ሲሆን ትልልቅ የመገበያያ መደብሮች ተዘግተዋል፤ እንዲሁም በርካቶች በቤታቸው ተወስነዋል።
በዋና ከተማዋ ሉዋንዳ በሚገኙ የመንግሥት ሆስፒታሎች የሚሰሩ እና ስማቸውን እንዳይጠቀስ የጠየቁ ዶክተሮች በባለፉት 24 ሰዓታት የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ተጨናንቋል ብለዋል።
ሰኞ እና ማክሰኞ በከተማዋ የተኩስ ድምጽ ይሰማ ነበር።
"የከፋ ጉዳት የደረሰባቸው በርካታ ተቃዋሚዎች መጥተዋል። በሚያሳዝን ሁኔታ አንዳንዶቹ ሞተዋል። የሟቾች ቁጥር ከተገለጸው ኦፊሴላዊው አኃዝ በላይ ሊሆን ይችላል ብለን እንሰጋለን" ሲሉ አንድ ዶክተር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ማኑኤል ሆመም በፕሬዚዳንት ጆአዎ ሎሬን ከተመራ የካቢኔ ስብሰባ በኋላ ረቡዕ ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል።
"ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ በሉዋንዳ፣ ሁአምቦ፣ ቤንጉዌላ እና ሁይላ ግዛቶች የህዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ድርጊቶችን አይተናል። ሆኖም በአገሪቱ ውስጥ ያለው አጠቃላይ የህዝብ ደህንነት በተረጋጋ ሁኔታ ላይ መሆኑን ለዜጎች ማሳወቅ እንፈልጋለን" ብለዋል ሚኒስትሩ።
የመገበያያ መደብሮች፣ ሱቆች እና ባንኮችን ጨምሮ በመላ አገሪቱ በርካታ ህንጻዎች መጎዳታቸውን ወይም መዘረፋቸውን ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
በተፈጠረው አለመረጋጋት አምቡላንሶች፣ አውቶብሶች እና የግል ተሽከርካሪዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
"ተቃዋሚዎች የፈጸሙት ድርጊት ወንጀለኛ ሰርጎ ገቦች ተጨምረውበት ሁኔታውን አባብሰውታል። ክስተቱ ለህዝብ ሰላም ስጋት የመሆን ደረጃ ላይ ደርሷል" ሲሉ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ረቡዕ ዕለት በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ወቅሰዋል።
ፕሬዚዳንት ሎሬንኮ የናፍጣ ዋጋን ከ33 በመቶ በላይ መጨመራቸውን ተከትሎ የተነሱ ስጋቶችን አቃልለው ነበር። ይህ ጭማሬ በነዳጅ ሃብታም በሆነችው አገር ያለውን የነዳጅ ድጎማዎችን ለማንሳት በሚል ነው በቅርቡ ተግባራዊ የሆነው።
ፕሬዚዳንቱ ለሲኤንኤን ፖርቹጋል እንደተናገሩት ተቃዋሚዎቹ የነዳጅን ዋጋ እንደ ምክንያት አድርገው የመንግሥትን ስልጣን ለማሳነስ እየተጠቀሙበት ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
የሶስቱን ቀናት የስራ ማቆም አድማ የጠሩት የታክሲ ማህበራት በተቃውሞዎቹ የተፈጠሩ ዝርፊያና ውድመትን እንደማይደግፉ በመግለጽ ይህ ከነሱ ጋር እንደማይገናኝ ተናግረዋል።
በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት ከፍራንክፈርት ወደ ሉዋንዳ የሚደረገው በረራ ማክሰኞ ምሽት ተሰርዟል።
የሉፍታንዛ ቃለ አቀባይ በረራው መሰረዙን አረጋግጠው፤ "ለተሳፋሪዎቻችን እና ለሰራተኞቻችን ደህንነት ቅድሚያ እንሰጣለን" ብለዋል።
በአገሪቱ መቀመጫውን ያደረጉ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች ለውጭ አገራት ዜጎች የደህንነት ማስጠንቀቂያ አውጥተዋል።















