የኬንያ ፖሊስ የቀድሞ ጠ/ሚ ራይላ ኦዲንጋን አስከሬን ለመሰናበት የተሰበሰቡ ላይ ተኩስ ከፍቶ ቢያንስ የሦስት ሰዎች ሕይወት አለፈ

በኬንያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋን አስከሬን ለመሰናበት በርካታ ሰዎች በተሰበሰቡበት ስታዲየም ፖሊስ ጥይት እና አስለቃሽ ጭስ በመተኮሱ ቢያንስ የሦስት ሰዎች ሕይወት አለፈ።

ታዋቂው የመብት ተሟጋች ድርጅት ቮካል አፍሪካ ለቢቢሲ እንደገለፀው በግርግሩ ከተገደሉት ሰዎች መካከል የሦስት ሰዎች አስከሬን ወደ ከተማዋ ዋና የሬሳ ማቆያ ክፍል ተወስዷል።

የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ ፖሊስ የተሰበሰቡትን ሐዘንተኞች ለመበተን በተኮሰው ጥይት ሌላ ተጨማሪ አንድ ሰው ሞቷል።

በዋና ከተማዋ ናይሮቢ በሚገኘው ስታዲየም በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ ፖሊሶች የተኮሱት ጥይት ዓይነት እስካሁን ግልፅ አይደለም።

ቮካል አፍሪካ ግን የሞቱት ሰዎች በጥይት መቁሰላቸውን አስታውቋል።

በኬንያ የፖለቲካ መድረክ ላይ ግዙፍ ስም እና ሰብዕና የነበራቸው ራይላ ኦዲንጋ በሕንድ ረቡዕ ዕለት ሕይወታቸው አልፏል።

አስከሬናቸው ሐሙስ ጠዋት በአገሪቱ ዋና አውሮፕላን ማረፊያ የደረሰ ሲሆን ባለሥልጣናቱም በዚያ በተሰበሰበው ከፍተኛ ሕዝብ ምክንያት በረራዎችን ለአጭር ጊዜ ለማስቆም ተገድደዋል።

በአውሮፕላን ማረፊያው አካባቢ የተሰባሰቡ ሐዘንተኞች ወደ ተከለከሉ ስፍራዎች መግባት የቻሉ ሲሆን በዚህምየተነሳ ለሁለት ሰዓታት ያህል "ለጥንቃቄ" በሚል በረራቸወዎች እንዲቋረጡ እና አየር ማረፊያው አንዲዘጋ ተደርጓል።

ከአየር መንገዱ ጀምሮ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች አስከሬኑን የያዘውን መኪና በማጀብ ከመሀል ከተማ በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው ስታዲየም በማጀብ በሰልፍ ተንቀሳቅሰዋል።

የራይላ ኦዲንጋን አስከሬን ለመሰናበት ከተጠበቀው ሕዝብ በላይ በመውጣቱ መጀመርያ ላይ በፓርላማው ሊካሄድ የነበረው የሽኝት ፕሮግራም ወደ ካሳራኒ ስታዲየም እንዲዞር ተደርጓል።

የኦዲንጋን አስከሬን ያዘው መኪና በሕዝብ በተጨናነቀው ስታዲየሙ ሲደርስ በርካታ ሰዎች ከውጭ ሆነው እየጠበቁ ነበር።

ከደቂቃዎች በኋላ ብዙ ሕዝብ የስታዲየሙን በር ጥሶ በመግባቱ ፖሊሶች አስለቃሽ ጭስ ተኩሰዋል።

በስፍራው ሐዘናቸውን ለመግለጽ የተሰበሰቡ ሰዎች በምላሹ በመሸሽ ወደ መውጫው ሮጠዋል።

በስፍራው የነበረ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ሲቪል የለበሱ ሰዎች ሐዘንተኞችን በዱላ ሲደበድቡ ተመልክቷል።

የቮካል አፍሪካ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሁሴን ካሊድ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "በናይሮቢ አስከሬን ማቆያ የተገኙ ባልደረቦቻችን፣ ሦስት አስከሬኖች በጥይት ቆስለው መምጣታቸውን መመልከታቸውን እናረጋግጣለን" ብለዋል።

ሌሎች አስከሬኖች ወደ ሌሎች አስከሬን ማቆያዎች ከተወሰዱ በሚል ሌሎች ባልደረቦቻቸው ክትትል እያደረጉ መሆኑንም አክለዋል።

ትርምሱ ከተረጋጋ በኋላ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶን ጨምሮ ሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት የራይላ ኦዲንጋን አስከሬን ተሰናብተዋል።

የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴውን የሚመሩት ምክትል ፕሬዝዳንት ኪቱሬ ኪንዲኪ ሐሙስ አመሻሽ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡ ቢሆንም ስለ ተፈጠረው ትርምስ እና ስለ ሞቱ ሰዎች ያሉት ነገር የለም።

አርብ ዕለት ለአስከሬኑ በወታደራዊ ክብር ከተሸኘ በኋላ ሕዝቡ "እስከፈለገ ድረስ ተገኝቶ እንዲሰናበት" እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ቅዳሜ ዕለት አስከሬኑ በምዕራብ ኬንያ በቪክቶሪያ ሐይቅ ዳርቻ ላይ ወደምትገኘው እና ጠንካራ ፖለቲካዊ ድጋፍ ወዳላቸው ስፍራ ወደ ኪሱሙ ይጓጓዛል።

ከኪሱሙ በስተ ምዕራብ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቦንዶ በሚገኝ ስፍራ እሁድ ዕለት ቀብራቸው ከመፈጸሙ በፊት የኅብረተሰቡ አባላት በይፋ አንዲሰናበት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

እንደ ቤተሰቡ ገለጻ ከሆነየኦዲንጋ ኑዛዜ የቀብር ስነ ስርዓታቸው በ72 ሰዓታት ውስጥአእንዲፈጸም ነው።

የ80 ዓመቱ የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ረቡዕ ጠዋት በሕንድ የእግር ጉዞ ላይ ሳሉ በመውደቃቸው ወደ ዴቫማታ ሆስፒታል ቢወሰደኑም ሕይወታቸው ሊተርፍ አልቻለም።

የኬንያ መንግሥት የሰባት ቀን ሐዘን አውጇል።

በኬንያ ፖለቲካ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸው እና ለብዙ ዓመታት የአገሪቱ ዋነኛ ተቃዋሚ መሪ ሆኖ የቆዩት ራይላ ኦዲንጋ በአምስት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎች ተወዳድረው ተሸንፈዋል።