የተሰረቁ የሶማሊያ ሴቶች ፎቶግራፎች ለፖለቲካዊ ፕሮፓጋንዳ ጥቅም ላይ መዋላቸውን ቢቢሲ አረጋገጠ

ሙስሊም እና የሶማሊያ ተፅዕኖ ፈጣሪች እንዲሁም የፋሽን ሞደሎች እንደሆኑ በማስመሰል የተፈጠሩ በርካታ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ጂኦፖለቲካዊ ፕሮፖጋንዳ ይዘቶችን እየለጠፉ መሆናቸውን የቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ምርመራ አረጋገጠ።
ሰማያዊ ሒጃብ ለብሳ የምትስቅ ሴት ምሥል መለያ (ፕሮፋይል) ያላቸው ገጾች በኤክስ፣ በቲክቶክ እና በፌስቡክ የታዩ ሲሆን፣ በአብዛኛው በእነዚህ ገጾች የተጋራው ልጥፍ አገሯን ሶማሊያን ምን ያህል እንደምትወድ የሚገልጽ ነው።
ቢቢሲ በፎቶው ላይ የምትታየውን እና የአኗኗር ዘይቤን በሚመለከት ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነችውን ሴት ያነጋገረ ሲሆን፣ በሁኔታው መደናገጧን እና እነዚህን የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች አይታቸው እንደማታውቅ ተናግራለች።
ስሜ አይጠቀስ ያለችው ይህች ሴት "እነዚህ አካውንቶች የእኔ አይደሉም።ፎቶዎቼን ተጠቅመውባቸው ነው። እኔን በመምሰል ይህንን ያደረጉ ሰዎችን ምንም ላደርጋቸው አልችልም" ብላለች።
ይህች ሴት ያለ እነርሱ እውቅና ፎቶዎቻቸው ተወስደው የሶማሊያን፣ የሱዳንን እና የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስን ፕሮፖጋንዳ ለማስተዋወቅ ጥቅም ላይ ከዋሉ በርካታ ሴቶች መካከል አንዷ ናት።
የቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ሐሰተኛ መረጃን የሚያጣራው ክፍል እና የአረብ ፎረንሲክ ቡድን በዚህ ኔትወርክ ውስጥ ያሉ ከ100 በላይ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾችን መለየት ችሏል።
ይህንን ኦፕሬሽን ማን እንደሚመራው ግን ግልጽ አይደለም።
ሆኖም ገጾቹ በሶማሊያ ውስጥ የሚደረጉ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እንቅስቃሴዎችን የሚያወድሱ በመሆናቸው ይዘቶቹ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ግቦች ጋር እንደሚገናኙ ተንታኞች ያምናሉ።
ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ (ዩኤኢ) በምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና ያላት ሚና ቁልፍ ነው።
ኤምሬትስ የታጠቁ ጽንፈኛ ቡድኖችን ለመከላከል በፀጥታው ዘርፍ ትልቅ ኢንቨስትመንት ያላት ሲሆን፣ ሶማሊያ በምትገኝበት እና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታው ወሳኝ በሆነው በቀይ ባሕር እና በኤደን ሰላጤ የባሕር የኃይል መሠረተ ልማትም አላት።
የሴቶቹን ምሥል የተጠቀሙት የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች በሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ተፋላሚ ለሆነው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) ድጋፋቸውን የሚያሳዩም ይመስላሉ።
የሱዳን ጦር ዩኤኢ ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የገንዘብ እና የጦር መሣሪያ ድጋፍ ታደርጋለች ሲል ከስሷል። አቡዳቢ ግን ይህንን በተደጋጋሚ አስተባብላለች።

የፎቶው ባለመብት, Unknown/Shared on X
ቢቢሲ የማኅበራዊ ሚዲያ መተንተኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ከአውሮፓውያኑ ጥር 2023 እና መስከረም 2025 መካከል ባሉት ዓመታት ውስጥ ይህ መረብ በ111 የኤክስ (በቀድሞው ትዊተር) የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች 47 ሺህ ልጥፎችን ማጋራቱን ደርሶበታል።
እነዚህ ልጥፎች በአጠቃላይ 300 ሺህ ላይኮች ያላቸው ሲሆን፣ 215 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ጋር ደርሰዋል።
እነዚህ አካውንቶች በአብዛኛው የተከፈቱት በደቂቃዎች ልዩነት ሲሆን፣ እንዳይለዩ የገጻቸውን ስም ለውጠዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የተሠሩ ግራፊክ ምሥሎችን እና ሃሽታግ የተጠቀሙ ሲሆን፣ በሁሉም ገጾች በተለያዩ ቋንቋዎች የተጻፉ ተመሳሳይ ልጥፎችን አጋርተዋል።
ይህም "የተቀናጀ እና ትክክለኛ ያልሆነ ባህርይ ያላቸው ገጾች" ምልክት እንደሆኑ የማኅበራዊ ሚዲያ አጥኚዎች አመልክተዋል።
በቅርብ በተከፈቱ እና በተወሰኑ የፌስቡክ እንዲሁም የቲክቶክ ገጾች ላይም የተወሰኑት አካውንቶች ቅጂዎች ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ልጥፎች ተጋርተዋል።
ምንም እንኳን እነዚህ ገጾች በቁጥር አነስተኛ ቢሆኑም የፕሮፓጋንዳው መረብ በሁሉም የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ የተዘረጋ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ይህን የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
ቢቢሲ የተመለከታቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች የሚያሳዩት አካውንቶቹን የሚጠቀሙት ሰዎች የሶማሊያ ዜጎች ወይም ቢያንስ በአገሪቷ ውስጥ የሚኖሩ እንደሆኑ አሳይተዋል።
የአብዛኞቹ ይዘትም የሶማሊያን መንግሥት እና የጦሩን ስኬት የሚያወድሱ ናቸው።
ልጥፎቻቸው የሶማሊያ ሕዝቦችን፣ የከተሞችን እና የመልከዓ ምድር ውበትንም ያደንቃሉ።
ከዚህም ባሻገር እንደ ኢሳቅ፣ ኦጋዴን፣ አጁራን፣ ዲር፣ ዲጊል፣ ዳሮድ እና አኪሾ የተባሉ የሶማሊ ጎሳ ስሞችን እንደ ገጾቻቸው መለያ አድርገው ተጠቅመዋል።
ይህም ምን አልባትም ሶማሊያውያን ተደራሾቻቸው ገጾቹ ትክክለኛ መሆናቸውን እንዲያምኑ ለማድረግ ያለመ ሊሆን ይችላል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ቢቢሲ ሪቨርስ (የመረጃ ማጣሪያ) ኢሜጅ ሰርችን በመጠቀም ከተወሰኑ ምሥሎች ጀርባ ያሉ ትክክለኛ ሰዎችን መለየት ችሏል፤ ምሥሎቹ የታዋቂ ሞዴል እና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች መሆኑንም ደርሶበታል።
ምሥሏ የሶማሊያ መንግሥትን እና ጦሩን የሚያወድሱ ይዘቶችን ለማጋራት በፌስቡክ ገጽ ላይ ጥቅም ላይ ውሎ ያገኘውን የቀድሞ የቁንጅና ውድድር አሸናፊን ቢቢሲ አነጋግሯት ነበር።
እርሷም ፌስቡክ ጭራሽኑ እንደማትጠቀም እና ምሥሏን በመጠቀም ከተከፈተው የፌስቡክ አካውንት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላት ገልጻለች።
አካውንቱ ሃሊማ በሚል ስም ጥቅም ላይ የነበረ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ ግን ወደ የዜና ድረ ገጽነት ተለውጧል። ገጹ በአብዛኛው በአረብኛ ቋንቋ ሶማሊያን የተመለከቱ አዎንታዊ ዜናዎችን ያጋራል።
ሜታ ገጹ ትክክለኛ ያልሆነ ባሕርይ ስለታየበት እየመረመረው እንደሆነ ገልጿል።
ሌሎች አራት ሴቶችም ሳያውቁ ምሥላቸው ጥቅም ላይ መዋሉን አረጋግጠዋል።
ከሴቶቹ መካከል የአንደኛዋ እናት እንዳሉት ልጇ የኤክስ አካውንት የሌላት ሲሆን፣ ምሥሏ በሌሎች ሰዎች ጥቅም ላይ መዋሉንም አታውቅም።
ልጃቸው ከዚህ የፕሮፖጋንዳ መረብ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነትም ሆነ የፖለቲካ ፍላጎት እንደሌላት ገልጸዋል።
ጉርድ ፎቶዋ ከሐሰተኛ የቲክቶክ አካውንቶች በአንዱ ጥቅም ላይ የዋለና በአሜሪካ ተቀማጭነቷን ያደረገች የውበት ተፅዕኖ ፈጣሪ በማናጀሯ በኩል ስትናገር ስለፎቶግራፏ ትክክለኛነት እና ጥቅም ላይ ስለማዋሉ እንደማያውቁ ተናግራለች።
የቲክ ቶክ ቃል አቀባይ የተፅዕኖ ፈጣሪዋ እንደሆነ በማስመሰል የተከፈተው አካውንት ላይ ምርመራ መደረጉን እና የማኅበራዊ ሚዲያ ፖሊሲውን ካላከበሩ ሌሎች ገጾች ጋር መዝጋቱን ገልጸዋል።
ማኅበራዊ ሚዲያው የሌሎችን ምሥል በመጠቀም መረጃዎችን ማጋራትን ጨምሮ ተጠቃሚዎችን የሚያታልሉ አካውንቶችን መጠቀም እንደማይፈቅድ ቲክ ቶክ አክሏል።
"በቲክ ቶክ ላይ የሚካሄዱ ትክክለኛ የመረጃ ልውውጦችን የሚያስተጓጉሉ ሙከራዎችን አንታገስም። እንዲህ ዓይነት ባህሪይ የሚያሳዩ አካውንቶችን ለማስወገድ ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ የሚሠራ ቡድን አለን" ብሏል።
በመካከለኛው ምሥራቅ ተመሳሳይ የማኅበራዊ ሚዲያ የሚሠራጩ የሐሰተኛ መረጃዎች ዘመቻን የመረመሩት እና በኳታር በሚገኘው ኖርዝዌስተርን ዩኒቨርሲቲ የሐሰተኛ መረጃ ባለሙያ የሆኑት ማርክ ኦውን ጆንስ፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቹ "ሐሰተኛ ማንነቶች" የተጠቀሙ እና የሰፊ የመረጃ መረብ አካል መሆናቸውን ተናግረዋል።
'ሐሰተኛ ማንነቶች' ትክክለኛ ያልሆኑ የማኅበራዊ ሚዲያ ማንነቶች ሲሆኑ፣ የሆነን ሃሳብ ለማስተጋባት አሊያም ትክክለኛ ማንነቶችን በመደበቅ የተለያዩ አመለካከቶችን አዛብቶ ለመጠቀም የሚፈጠሩ ናቸው።
እነዚህ ገጾች እንግሊዝኛ፣ ሶማሊኛ እና አረብኛ ቋንቋን በመጠቀም ልጥፎችን አጋርተዋል። ከአረብኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች በተለይም ደግሞ ከወጣት ተጠቃሚዎች ጋር ለመመሳሰል መደበኛ ያልሆኑ የአረብኛ አገላለጾችን ተጠቅመው ተስተውሏል።
መደበኛ አረብኛ ቋንቋ ለሃይማኖታዊ፣ ሥነ ጽሑፋዊ ወይም መደበኛ አገላለጽ ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን፣ ተራ አገላለጾች በሚመረጥበት በይነ መረብ (ኦንላይን) በሚደረጉ የሃሳብ ልውውጦች መጠቀም የተለመደ አይደለም።
የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮቹ እንደሚሉት የዚህ ድርጊት ሰለባዎች ራሳቸው ገጾቹን ሪፖርት ማድረግ ይችላሉ።
ሆኖም ኤክስ እነዚህ አካውንቶች ፖሊሲውን መጣስ አለመጣሳቸውን በተመለከተ የሰጠው አስተያየት የለም።
ሱዳን ላይ ለምን ትኩረት አደረጉ?
በእነዚህ ገጾች ላይ በተደረገ ክትትል ሶማሊ መስለው የቀረቡት ስለሶማሊያ መንግሥት እና በሱዳን ስላለው ጦርነት በኤአይ የተሻሻሉ ምሥሎችን በመጠቀም ተደጋጋሚ መልዕክቶችን ያስተላልፋሉ።
ነሐሴ ወር ላይ በርካታ የሴቶች ምሥሎችን መለያቸው ያደረጉ ገጾች 27 ሰላማዊ ሰዎች በሱዳን ጦር መጨፍጨፋቸውን እና በደቡባዊ ሱዳን አል ኦቤድ መቀበራቸውን ገልጸዋል።
ይህ ክስ በሌላ ይፋዊ በሆነ የመረጃ ምንጭ ላይ የሌለ ሲሆን በማኅበራዊ ሚዲያ ብቻ የታፈነ ይመስላል።
ቢቢሲ ገለልተኛ የሆነውን እና ተቀማጭነቱን በሱዳን ያደረገውን የመረጃ አጣሪ ድርጅት - ቢም ሪፖርትስን የጠየቀ ሲሆን፣ ምንም እንኳን በሱዳን መሬት ላይ ምን እየሆነ እንደሆነ ለማጣራት አስቸጋሪ ቢሆንም በማኅበራዊ ሚዲያ የተጋራውን የሚያረጋግጥ ተጨባጭ መረጃ አለማግኘቱን ገልጿል።
ልጥፎቹ የሱዳን ጦር ደጋፊ የሆነው የሱዳን ቴሌቪዥን የአገሪቷ አየር ኃይል ኮሎምቢያውያን ተዋጊዎችን የያዘውን የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስን አውሮፕላን መትቶ መጣሉን ያሳወቀበትን ዜና ለመገዳደር የተለቀቁ ይመስላሉ።
በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (አርኤስኤፍ) ቁጥጥር ሥር በነበረው አየር ማረፊያ ላይ በተፈፀመው ጥቃት 40 የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸውን ከሁለት ዓመታት በላይ በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እየተፋለመ ያለው ተቀናቃኝ ቡድን አስታውቋል።
የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቹም ለአርኤስኤፍ እና ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ የሚስማሙ ትርክቶችን ለማስተዋወቅ ጥቅም ላይ ውለዋል።
ዩኤኢ፣ አርኤስኤፍን ወይም ከቡድኑ ጋር በመወገን የሚፋለሙ የውጭ ተዋጊዎችን ትደግፋለች በሚል በተደጋጋሚ የቀረበባትን ክስ ውድቅ አድርጋለች።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቹ ጀርባ ያለው ማነው?
ከማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቹ (አካውንቶቹ) ጀርባ ያለውን አካል ማንነት ለማረጋገጥ ያሉት ማስረጃዎች ውስን በመሆናቸው ባለቤታቸው ማን እንደሆነ አይታወቅም።
ሆኖም በዋናነት ሶማሊያን እና መንግሥቷን የሚያወድሱ ሲሆኑ፣ 40 በመቶ የሚሆኑት ልጥፎች በቀጥታ ሶማሊያን ይጠቅሳሉ።
ምንም እንኳን ዘመቻውን የሚያካሂደውን ድርጅት ማንነት ለማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንም አካውንቶቹ የዩኤኢን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ግቦችን የሚደግፉ እና በሶማሊያ ዘንድ ቅቡልነትን ለማግኘት የሚሠራ የሶማሊያ ደጋፊዎች ኔትወርክ ቅርንጫፍ እንደሆኑ ዶ/ር ጆንስ ያምናሉ።
"ሁሉም የሚጠቀሙት ተመሳሳይ ስልት ነው። በተለይ በቀጠናው ለዩኤኢ የውጭ ፖሊሲ ጥቅም ያላቸውን የሆነን አገር ወጣቶች፣ ሳቢ የሆኑ ሰዎችን ይጠቀማሉ። ይህ የሶማሊ ቡድን ነው። ሆኖም የሞሪታኒያ፣ የአልጀሪያ እና የሞሮኮንም ተመልክቻለሁ" ብለዋል።
ዶ/ር ጆንስ እንደሚሉት ወደ ዩኤኢ ሲመጣ አካውንቶቹ አወዳሽ ናቸው።
"የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ስትራቴጂ መደራረብ ቢኖርም ዩኤኢ በአገሪቱ ውስጥ ያላትን ፍላጎት የተመለከቱ አጀንዳዎች የመነጋገሪያ ነጥቦች ናቸው።"
የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቹም በዩኤኢ የተደረገ የምግብ ድጋፍን የሚያሳይ ምሥልን " ዩኤኢ በሶማሊያ የምታደርገው ድጋፍ" ከሚል ጽሑፍ ጋር አጋርተዋል።
የተወሰኑ ሶማሊያውያን ዩኤኢ በሶማሊያ እና በከፊል ራስ ገዝ በሆኑት ግዛቶች የምታደርገውን የገንዘብ ድጋፍ ቢቃወሙም ወሳኝ የሆነው የአገራቱ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ተጠናክሮ ቆይቷል።
ዩኤኢ ራስ ገዝ መሆኗን ባወጀችው ሶማሊላንድ እና በከፊል ራስ ገዝ በሆኑት ፑንትላንድ እና ጁባላንድ ውስጥ በኢነርጂ፣ በትራንስፖርት እና በፀጥታው ዘርፍ ላይ መሠረተ ልማት አላት።
ከዚህ በተጨማሪ የአልሸባብ እና እስላማዊ ታጣቂ ቡድኖችን ለመዋጋት ወታደሮችን የምታሠለጥን ሲሆን፣ የገንዘብ ድጋፍም ታደርጋለች።
በመካከለኛው ምሥራቅ ልምድ ያላቸው ገለልተኛ የሐሰተኛ መረጃዎች ተንታኝ የሆኑት አሌሳንድሮ አኮርሲ እንደሚሉት የዩኤኢ በአገሪቷ ያላትን የውጭ ፖሊሲ ትርክቶች የሚደግፉ ዘመቻዎችን ነቅሶ ማውጣት አይቻልም።
ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የሕዝብ ግንኙነት ድርጅቶች ላይ ጥገኛ የሆኑ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የአቡዳቢ ደጋፊዎች በዚህ በተሳሳተ መረጃ ምኅዳር ላይ ተፅዕኖ ስላላቸው ነው።
"ቀጥተኛ የሆነ ነገር ማለት አስቸጋሪ ነው፤ ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ እንደዚህ የሚያደርጉት በግል የተቀጠሩ የሕዝብ ግኙነት ሥራ የሚሠሩ ድርጅቶች እና ተፅዕኖ ፈጣሪ የኦፕሬሽን ካምፓኒዎች ስለሆኑ ነው" ብለዋል።
ቢቢሲ ጉዳዩን በተመለከተ ለዩኤኢ እና ለሶማሊያ መንግሥት ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ አላገኘም።
በይዘቶቹ ላይ የተሠራው ትንተናም እነዚህ አካውንቶች በማን እንደሚመሩ በቀጥታ አያሳዩም። በመሆኑም ሴቶቹ ፎቶዎቻቸውን ማን እንደወሰደው እና እየተጠቀመበት እንዳለ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው።















