የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ በቤተክርስቲያኗ ላይ ጥቃት እየተፈጸመ ነው አለ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የእምነት አባቶች እና የእምነቱ ተከታዮች ላይ ጥቃት እየተፈጸመ መሆኑን የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ቅዳሜ ጥር 27/2015 ዓ.ም. አስቸኳይ ስብበሳ አድርጎ ባወጣው መግለጫ አመለከተ።

በዚህም የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በወሰዷቸው እርምጃዎች በቤተክርስቲያኗ አባላት ላይ የሕይወት እና የአካል ጉዳት መድረሱ ተገልጿል።

ቅዱስ ሲኖዶሱ በመግለጫው በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የቤተክርስቲያኒቱን ሊቃነ ጳጳሳት ጨምሮ፣ በእምነቱ መሪዎች እና በምእመናን ላይ የተፈጸሙ እና እየተፈጸሙ ናቸው ያላቸውን ሕገ-ወጥ እስር እና ወከባ አውግዟል።

ሲኖዶሱ የቤተክርስቲያኗ ጥያቄ ምላሽ የማያገኝ ከሆነ የእምነቱ ተከታዮች በሚቀጥለው ሳምንት እሁድ የካቲት 05/2015 ዓ.ም. ጠዋት ከየአጥቢያቸው በመነሳት የጥምቀተ ባሕር ወይም የመስቀል በዓል በሚከበርበት አደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲደረግ ጥሪ አስተላልፏል።

መግለጫው ጨምሮም በምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት በሻሸመኔ ከተማ በደብረ ስብሐት ቅዱስ ሚካኤል አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ላይ "መንግሥትን ተገን ያደረጉ ናቸው" ያላቸው ግለሰቦች ወረራ ለመፈጸም ሙከራ ማድረጋቸውንም ገልጿል።

የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብጹዕ አባ ጴጥሮስ በኢትዮጵያ የኦሮሚያ እና የብሔር ብሔረሰቦች ሲኖዶስ በሚል በሕገ-ወጥ መንገድ ተደራጅተው በቤተክርስቲያኒቱ ተቋማትን ላይ በመንግሥት ‘ድጋፍ’ ወረራ እየፈጸሙ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የሃይማኖቱ መሪዎች ላይ ‘እስር እና ማዋከብ’ እንዲሁም ከአገር ስብከታቸው ለቀው እንዲወጡ እየተደረጉ መሆኑን እንዲሁም ሊቀነ ጳጳሶች ወደ አህጉረ ስብከታቸው እንዳይሄዱ ማስፈራሪያ እየተላከ አሳዛኝ ድርጊት እየተፈጸም ነው ብለዋል።

በዚህም ይህንን ለመከላከል እና ቤተ ክርስቲያኗን ለመጠበቅ በወጡ ምእመናን ላይ "ፖሊስ በወሰደው እርምጃ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ የአደባባይ የግድያ ወንጀል ተፈጽሟል" በማለት በቁጥር ያልታወቁ ምእመናንም ላይ ከፍተኛ እና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን አመልክቷል፡፡

ብጹዕ አባ ጴጥሮስ በክስተቱ የሞቱ እና የተጎዱ ሰዎችን ቁጥር ባይጠቅሱም የፈረንሳይ የዜና ወኪል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ (ኤኤፍፒ) ሦስት ሰዎች መገደላቸውን ዘግቧል።

ኤአፍፒ ለቤተክርስቲያኗ ቅርብ የሆነውን ተዋህዶ ሚዲያ ማዕከልን ጠቅሶ እንደዘገበው የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት በከፈቱት ጥቃት ሦስት ሰዎች መገደላቸውን እና አራት ሰዎች መቁሰላቸውን ዘግቧል።

በሻሸመኔ ቅዱስ ሚካኤል አጥቢያ ቤተ-ክርስቲያን ያጋጠመውን የጉዳት መጠን ቢቢሲ ከገለልተኛ አካል ማረጋገጥ አልቻለም።

ባለፉት ቀናት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እውቅና ውጪ የተሰጠ ሹመትን ተከትሎ አለመግባባቶች መፈጠራቸው ይታወሳል።

በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ውስጥ ወሊሶ አቅራቢያ ሶዶ ዳጬ ወረዳ ሐሮ በዓለ ወልድ ቤተክርስቲያን ውስጥ እሁድ ጥር 14/2015 ዓ.ም. 26 የጳጳሳት ሹመት ከፓትሪያርኩም ሆነ ከቅዱስ ሲኖዶሱ እውቅና ውጪ መሰጠቱ ከተሰማ በኋላ ነበር ችግሩ የተፈጠረው።

ይህንን ሹመት ያካሄዱት አባቶች የሚመሩት በአባ ሳዊሮስ ሲሆን፣ ቤተክርስቲያኗ አካታች አይደለችም እና ምዕመናን በቋንቋቸው የእምነቱን ሥነ ሥርዓት እንዲፈጽሙ አላስቻለችም በማለት እርምጃውን መውሰዳቸውን ይናገራሉ።

ይህንንም ተከትሎ በፓትሪያርኩ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሐሙስ ጥር 18/2015 ዓ.ም. ባካሄደው ጉባኤ ድርጊቱ በቤተ ክርስቲያኒቱ የሃይማኖት፣ የቀኖና እና የአስተዳደራዊ ጥሰቶች የሚፈጽም መሆኑን በመግለጽ ውሳኔ አሳልፏል።

በፓሪያሪኩ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ጵጵስና ሹመት የሰጡ እና የተቀበሉ አባቶች ከቤተክርስቲያኒቷ ተወግዘው እንዲለዩ መወሰኑ ይታወቃል።

ይህንን ውሳኔም ተከትሎ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተክርስቲያኗን ቀኖና እና ሕግ ጥሰዋል ተብለው በመወገዝ እና እንዲለዩ የተወሰነባቸው አባቶች ውሳኔውን እንደማይቀበሉ አሳውቀዋል።

የቤተክርስቲያኗ ሲኖዶስም መንግሥት ሕግ እንዲያስከበር የተየቀ ሲሆን፣ ነገር ግን በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የእምነቱ አባቶች እና ምዕመናን ላይ እንግልት እየደረሰ መሆኑን በመግለጽ፣ ጥያቄያቸው ምላሽ ካላገኘ በኢትዮጵያ እና በዓለም ዙሪያ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚጠራ ከቀናት በፊት ገልጸው ነበር።

በዚህም መሠረት በሚቀጥለው እሁድ የቤተክርስቲያኗ ምዕመናን ቤተክርስቲያኗ የተለያዩ በዓለት ወደ ምታከብርባቸው ስፍራዎች በመሰባሰብ በሰላማዊ መንገድ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጥሪ አቅርቧል።

የመንግሥት መንግሥቱም ሆነ የክልል መንግሥት የቤተክርስቲያኗ መሪዎች እያቀረቡት ያለውን አቤቱታ በተመለከተ አስካሁን በይፋ ያሉት ነገር የለም።

ከቀናት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከካቢኔ አባሎቻቸው ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ ሚኒስትሮቻቸው በዚህ ጉዳይ ውስጥ እጃቸውን እንዳየስገቡ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።