‘ሃያሁለት’ በካምፓላ

ጦርነትን፣ መከራን፣ መጎሳቆልን ሸሽተው ቀያቸውን ለቀው ለተሰደዱ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን የኡጋንዳዋ ካምፓላ ቤት ሆናናለች ይላሉ።

ከአገራቸው ርቀው ቤት ንብረት ማፍራት ችለዋል፤ ልጆች ያስተምራሉ።

ኑሯቸውን ማስቀጠል ችለዋል።

በተለይም ካባላጋላና ካሳንጋ የተባሉት የካምፓላ ሰፈሮች የኢትዮጵያውኑ እና የኤርትራውያኑ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

የአገሬው ሰው ራሱ እሱን የተረዳ ይመስላል።

እነዚህን ሰፈሮች የሚያዘወትሩ ኡጋንዳውያን ራሱ አማርኛ ሰላምታ፣ ትግርኛ ቃላትን ያውቃሉ።

በነዚህ ሰፈሮች አገር ቤት በሚመስል ሁኔታ ትግርኛ እና አማርኛ ሲያልፉ ሲያገድሙ ይሰማሉ።

ሰው ሰላምታ ይቀያየርባቸዋል፤ ገበያ ለመሸመትም እንዲሁ።

የልብስ መደብሮቹ የአገር ባህል አልባሳትን ይዘዋል።

የሻይ ቡና ገበያው ደርቷል።

በምሽትም ወጣ ካሉ እንዲሁ የኢትዮጵያውኑና የኤርትራውያኑ ንብረት የሆኑ እንዲሁም የሚያዘወትሩባቸው ክበቦችም የሰፈሮቹ ድምቀቶች ናቸው።

ሰፈሮቹን እንዲሁም ወጪው ገቢውን ከሚያዉቁት መካከል ኤርትራዊው ስደተኛ ተስፊት አብርሃም ይገኝበታል።

ተስፊት በካምፓላ ከአምስት ዓመታት በላይ ኖሯል። የሚተዳደረውም ፎቶ በማንሳት ነው።

"እዚህ አገር 'አንተ ማን ነህ?’፣ 'ከየት ነህ?' 'መታወቂያ ይዘሀል ወይ’?፣ ' የመኖርያ ፈቃድ አለህ ወይ?' ብሎ የሚጠይቅህ ማንም የለም” ይላል።

ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን ከሚያዘጋጇቸው ድግሶች የማይጠፋው ተስፊት በጊዜ ሂደት አካባቢው እንዴት እንደተቀየረና ‘ሐበሻዊ’ ቀለም እንደለበሰ ለውጡን በካሜራው አስቀርቶታል።

ኮምፒውተሩን ከፍቶ በስፍራው ለነበሩት የቢቢሲ ጋዜጠኞች ከጥቂት ዓመታት በፊት የሰፈሮቹ ሁኔታ ምን አይነት ነበር የሚለውን አሳይቷል።

ተስፊት የአካባቢው ሁኔታ መቀየር ብቻ አይደለም የሚያስደንቀው።

ኡጋንዳውያኑ ለሃበሾች የሚያሳዩት ፍቅር እና እንክብካቤ ይገርመዋል፤ መንፈሳዊ ቅናት ይሰማዋል።

ጨዋታ አዋቂው ተስፊት በወሬው መካከል ድንገት “በሉ ተነሱ ሃያ ሁለት ደርሰን እንምጣ” አለ።

እኛም “ሃያ ሁለት ምንድን ነው?” "ለምንስ እንደሱ ተባለ?" የመሳሰሉት ጥያቄዎችን እንጠይቀው ጀመር።

ተስፊትም ላሳያችሁ ብሎን አቀናን።

የካምፓላዋ ሃያ ሁለት

ልምላሜ የተላበሰችው ካምፓላን እያየን፤ በአረንጓዴነቷ እየተደመምን ሙቀቷም እየወበቀን ሰፈሮቹን መቃኘት ጀመርን።

ካንሳንጋ ከሚገኙት የአበሻ ምግብ ቤቶች አንዱ የሆነው አክሰስ ላውንጅ ሻይ ቡና ብለን ወጣን።

እሱን ጎዳና ይዘን ስንሄድም በርካታ የሃበሻ ንግድ ቤቶች እያስደመሙን ፎቶ እያነሳንም ጉዟችንን ቀጠልን።

ከትላልቅ ህንጻዎች እስከ ትንንሽ ሱቆች፣ የውበት ሳሎኖች፣ ቡና ቤቶች ተመለከትን።

አብዛኛዎቹ ቃለ መጠይቅ ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበሩም።

“አሁን ካባላጋላ ደርሰናል” አለ ተስፊት።

በካባላጋላም ኢትዮጵያውያኑ እና ኤርትራውያኑ የራሳቸውን አሻራ እያሳረፉ ስለመሆኑ ማሳያዎቹ ብዙ ናቸው።

የካፌዎቹ፣ የሬስቶራንቶቹ፣ የሱቆቹ መጠሪያዎች አንደኛው ማሳያ ነው።

የካባላጋላ ማዕከል ከሆኑት አንዷ በተለምዶ ሃያ ሁለት የምትባለው የኢትዮጵያውያኑ እና የኤርትራውያኑ የተንጣለለችው ግቢ ናት ።

ይህች ግቢ በርካታ ሬስቶራንቶችን ይዛለች። ስያሜዎቹም በግዕዝ ሆሄያት እና ቁጥሮች ደምቀው ተጽፈዋል።

እነዚህን በመጻፍ ኑሮአቸውን የሚገፉ እንዳሉ ተስፊት ይናገራል።

በዚህች ግቢ ውስጥ ካሉ ሬስቶራንቶች በትግርኛ ‘አደ ባርን ቤት ብልዕን (የእናት ምግብ ቤት እና ባር) የሚል መጠሪያ ያላት አንዷ ናት።

በግቢዋ ጮክ ብሎ የሚሰማው አማርኛ እና ትግርኛ ቋንቋዎች ፤ ድምጽ እና ግርግር የት ነው ያለሁት ብለው ያስጠይቅዎታል።

ከአገራቸው ርቀው ላሉ ስደተኞች ቢያንስ የናፈቃቸውን ምግብ የሚያገኙበት፣ ወዳጅ ዘመድ ያፈሩባት፣ በአገር ቤት ያጡትን የሚያካክሱበት ስፍራ መካከል አንዷ ናት -ሃያ ሁለት።

እርስ በርሳቸው በጦርነት እና ግጭት ከሚናጡ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ቢሰደዱም በዚህች ግቢ ግን ያ ሁሉ ቀርቶ ሳቅና ጨዋታ የደራባት ናት።

ብሄሮችን እየመረጡ፣ ትግራዋይ፣ አማራ፣ ኦሮሞ መባባል የለም።

አገራትን እያነሱ ኤርትራዊ፣ ኢትዮጵያዊ እና ሱዳናዊ በመባባል መናቆር የለም።

የስደት ህይወት አንድ ላይ አምጥቷቸዋል።

በጋራ ማዕድ ይቆርሳለ፣ ይዝናናሉ። የጋራ ብሶታቸውንም ይወያያሉ።

አንድ ጠረጴዛ ላይ ከአንድ ቤት ሻይ፣ ከሌላው ጥብስ ፣ ከሌላው ቡና ያዛሉ።

እንዲያው ‘የእኔ ፣የእኔ’ የሚባል ወንበርና ጠረጴዛ የለም። ከራሳቸውም አልፈው ለአገሬው ሰውም እንጀራ በወጥ መብላት አስለምደዋል።

የሶስት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ መነን በሃያ ሁለት ግቢ ውስጥ የሚገኘው ‘የሐበሻ ሬስቶራንት’ ባለቤት ናቸው።

በአንድ እጃቸው ስኒ በሌላ እጃቸው እጣን ይዘው ቆመው አናገሩን።

አረፍ ብለው ለማውራት ጊዜ ያላቸው አይመስሉም።

ሶስት ልጆች ያሉዋቸው ሲሆን ትልቋ ሴት ልጃቸው ዘጠነኛ ክፍል ደርሳለች።

መነን ከኢትዮጵያ ከተሰደዱ 12 ዓመታት ገደማ ሆኗቸዋል።

ሆኖም ራሳቸውን እንደ ስደተኛ ቆጥረው አይውቁም።

“ካምፓላ [ኡጋንዳ] ጥሩ አገር ነች፣ ነፃነት አለሽ፣ ምንም ችግር ያለባቸው ሰዎች አይደሉም” አሉን በፈገግታ።

[በአዲስ አበባ የምትገኘው ‘ሃያ ሁለት’ ሰፈር ቀን ቀን በቡና ቤቶችና ሬስቶራንቶች የተጨናነቀች፣ ምሽት ላይ ደግሞ ሌቱ አይነጋብኝ የተባሉ የምሽት ክበቦች የበዙባት ሲሆን ቀደም ብሎ ትግርኛ ተናጋሪ የሚበዙባቸው የመዝናኛ ስፍራዎች መገኛ መሆኗ ይታወሳሉ።]

በዚህ ሰፈር ሲንቀሳቀሱ ካገኘናቸው የትግራይ ተወላጆች መካከል በትግራይ ጦርነት ወቅት ብሔርን መሰረት አድርጎ እስራት እና ጥቃት የደረሰባቸው ይገኙበታል።

ሆኖም ይህንኑ አምልጠው እዚሁ ‘ሌላ ‘ሃያ ሁለት’ ያገኙ ይመስላል።

ወደ ወይዘሮ መነን እንመለስ እና እሳቸው “እዚህ ቦታ ‘ይሄ ያንተ ነው’፤ ‘ይሄ የእኔ ነው’ የሚባል ነገር የለም፣ አብረን እንሰራበታለን፤ እዚህ ቦታ ፍቅር እና ትብብር ብቻ ነው ያለው" ሲሉ ይመሰክራሉ።

በአገር ቤት የደፈረሰው ማህበራዊ ትስስርና ግንኙነት እዚሁ ስደት ላይ የታከመ ይመስላል።

አብዛኛዎቹ ደንበኞቻው ከኢትዮጵያ እና ኤርትራ የመጡ ቢሆኑም ሱዳናውያን እንዲሁም ደቡብ ሱዳናውያንም ይገኙበታል።

በካፌያቸው ሻይ፣ ማኪያቶ፣ ቡና እንዲሁም እንዲሁም የጾም ምግቦች አሉ።

በጥዑም ቡናቸው የሚታወቁት መነን ከጥዋቱ 12 ሰዓት በፊት የሚመጡ የቡና ሱሰኛ ደንበኞቻቸውን ያስተናግዳሉ።

ማለዳ መነሳት ስለሚወዱ ደስ ብሏቸው ነው የሚከፍቱት።

አንዳንድ ሃያ ሁለት ውስጥ ያሉ ካፌዎች፣ 24 ሰዓታት ያለ እረፍት ክፍት ሆነው ይሰራሉ።

‘ዓሲምባ’ በካምፓላ

በካንሳንጋም ልክ እንደ ካባላጋላ በተመሳሳይ በተንጣለለ ግቢ በጋራ የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራ ስደተኞች አገኘን።

ዓሲምባ ካፌ አንዷ ናት።

የትግራይ ተወላጇ ሰላም በራኪ ትንሿን ካፌ የሰየመቻት በግዙፉ ተራራ ‘ዓሲምባ’ ነው።

ዓሲምባ በኢሮብ ምድር እምብርት የሚገኝ ታዋቂ ተራራ ሲሆን በተለይም በ60ዎቹ ከኢህአፓ የትጥቅ ትግል ጋር በተቆራኘ ታሪኩ ይጠቀሳል።

‘የዓሲምባ ፍቅር’ የተሰኘው መጽሓፍም የዚያን ትውልድ ማንነት ከሚዘከርበት እና ዋቢ ከሚደረጉ አንዱ ነው።

ኢሮብ የተወለደችው ሰላም ካፌዋን ዓሲምባ ብላ የሰየመቻት ያደገችባትን ቦታ እንዲሁም ታሪካዊ ስለሆነም እንደሆነ ትናገራለች።

ሬስቶራንቷን ከከፈተቻት ጥቂት ወራት ብቻ ቢሆነውም ያላት አገልግሎት ዓመታትን ያስቆጠረ ይመስላል።

በካምፓላ ለሁለት አመት ከአምስት ወር ቆይታለች።

ኢትዮጵያውያን እና ኡጋንዳውያንን ቀጥራ የምታሰራ ሲሆን በተለይም ከኡጋንዳውያን ጋር መስራት እንደሚያስደስታት ትናገራለች።

በወሬያችን መሃል የሚቆላው ቡና መዓዛ ቀልባችንን ሰረቀው።

ሰላም ቡናዋን ቆልታ እንደ ባህሉም “አሸተተችን”

ቡናችንን ፉት እያልን ጨዋታችንን ቀጠልን።

ሰላም ፈገግታ ባይለያትም መሃል ላይ ሃዘን ይነብባታል።

ለዚህም በኤርትራ ወታደሮች ቁጥጥር ስር የሚገኘው ኢሮብ ሁኔታ እንደሆነ ነገረችን።

ጥላው የመጣችው ልጇ፣ ወዳጅ ዘመዶቿ የሌት ተቀን ሃሳቦቿ ናቸው።

በርካታ የአካባቢው ተወላጆች በጦርነቱ ማለቃቸውን የተቀረው ወጣት ወደ ስደት እያመራ እንደሆነ ትሰማለች።

“ከሰላም ስምምነቱ በኋላም ቢሆን አሁን የተሻለ ነው የምንልበት ሁኔታ አይደለም” የምትለው ሰላም ከሆነላት መመለስ እንደምትፈልግ ትናገራለች።

“ስደት ዕድሜህን ነው የሚጨርሰው። ልጄ እና ቤተሰቦቼ ሀገር ቤት ናቸው። ሙሉ ሰላም ከሆነልን ወደ ቤቴ መመለስ እፈልጋለሁ”። ብላለች።

የካምፓላው መሐንዲስ

በትግራይ ጦርነት ምክንያት ወደ ኡጋንዳ የተሰደደው መሃንዲሱ ቢንያም ገብረ መስቀልንም ካምፓላ ላይ አገኘነው።

ከአገር ከመውጣቱ በፊት በአንበሳ ባንክ፣ በአዲግራት እና ሰመራ ዩኒቨርስቲዎች በመሃንዲስነት አገልግሏል።

ቀዬውን ትቶ ከተሰደደ በኋላም ብዙም አልከፋውም።

ስለ ኡጋንዳ ሲናገርም “ ይህች አገር የምትሰራበት፣ የምትኖርባት የተባረከች ናት" ይላታል።

ካምፓላ ከመጣም በኋላ በሚሊዮኖች የሚገመት ውል የወሰደ ሲሆን አንዳንዶቹን ፕሮጀክቶች ቢቢሲ መመልከት ችሏል።

በኢትዮጵያ ከሚገኙት ባልደረቦቹ ጋር በመመካከር የሚሰራው ቢንያም በካምፓላ ያልተለመደ የመኖሪያ ቤቶችን አሰራር እያስተዋወቀ እንደሆነ ይናገራል።

ለአንድ ባለ ሃብት የሰራው የቤት ግንባታ ሌሎች ደንበኞች እንዲመጡ ፈር ቀዶለታል።

እየተገነባ የነበረው ቤታቸውን እንዲህ ቢሆን በሚል እንደዋዛ በሰጠው አስተያየት ነበር ባለሃብቱ ውሉን ለሱ የሰጡት።

ይህ “ዓይኔን የገለጠልኝ” የሚለውን የግንባታ ስራ በስድስት ወር አጠናቆ ጨረሰ።

እሳቸው በስራው ደስተኛ መሆናቸውን የሚናገረው ቢንያም እንደ ጓደኛ እና እንደ አባትም ሆነውኛል ይላል።

የዚህን ቤት አሰራር የተመለከቱ ደንበኞችም መምጣት ጀመሩ።

“በአገራችንና በኡጋንዳ መካከል የቤት ግንባታ ላይ መጠነኛ ልዩነት አለ። እኛ በምን መልኩ እንደምንገነባ አሳየሁዋቸው - ተቀበሉት። በዚህ መሠረት ብዙዎቹ የነበራቸውን ዲዛይን እየቀየሩ ነው፤ ስራልን ይሉኛል” ይላል።

በበሮች፣ መስኮቶች እና ጣርያዎች ላይ ልዩነቶች እንዳሉ የሚናገረው መሐንዲሱ ‘የእኛ’ እያለ የሚጠራውን ግንባታ የሚወዱት እየተበራከቱ ነው ይላል።

ከአገር ሲወጣ የመጀመሪያ የሆነው ቢንያም በቆይታው ለዕውቀትና ለሙያ ከፍ ያለ ግምት እንደሚሰጥ ታዝቧል።

“ለስደት የበቃሁት በጦርነት ምክንያት ቢሆንም ሙያዬን በደንብ የተጠቀምኩበት ግን እዚሁ አገር ነው። ዓይኖቼን ገለጥኩ፤›› በማለት ኢትዮጵያ ውስጥ ለሙያተኝነትና ለእውቀት የሚሰጠው ዝቅተኛ ዋጋ እንዳሳዘነው ያስረዳል።

የአስመራ ኬክ በካምፓላ

ካምፓላን እንዲሁ እየቃኘን የአስመራ ኬክ አገኘን።

የአብሊዝ ኬክ ይባላል።

በካንሳንጋ ከሚታወቁ ጣፋጭ ኬክ ቤቶች አንዷ ናት።

ባለቤቷ ደግሞ በካምፓላ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር የቆየውችው ኤርትራዊቷ ዮሃና ናት።

ስራ ከጀመረች ገና አራት ወሯ ቢሆንም አስመራ በነበረችበት ወቅት ኬክ እየጋገረች ትሸጥ ነበር።

ኡጋንዳ በስደት ከመጣች በኋላ በቤቷ እየጋገረች መሸጥ የጀመረች ሲሆን በኋላም ይህችን ኬክ ቤት ከፈተች።

“የእኛ ሰዎች ወደውታል፤ ቶሎ ነው የለመደልኝ” ትላለች ዮሃናም።

አብዛኞቹ ስደተኞች ኡጋንዳን ወደ ምዕራባውያኑ አገራት ለመሄድ እንደ መሸጋገሪያ ቢያዩዋትም አንዳንዶች ግን ይኸው ኑሯቸው ተመችቷቸዋል።

ከነዚህ መካከል የፎቶ ባለሙያው ተስፊት አንዱ ነው። ካምፓላን በፍቅር ስለሚወዳትም ለውጭ አገር የጀመረው ሂደት ተሳክቶለት እንዳይወጣም ይሰጋል።

አገሩን ለቆ ከወጣ ዘጠኝ ዓመታትን ቢያስቆጥርም ኡጋንዳ ከደረሰ በኋላ ግን ወደ ሌላ አገር ለመሄድ ሃሳብ አልነበረውም።

ነገር ግን ከሁለት ዓመት በፊት በቤተሰቡ አባላት ግፊት ወደ ምዕራቡ አገራት ለመሄድ ሂደቱን ጀምሯል።

ተስፊት የካምፓላ ኑሮውን ይወደዋል።

ከፎቶ ባለሙያነቱ በተጨማሪ በግጥም ድርሰት እና ስደተኞቹን በማነቃቃት ላይ ንቁ ተሳትፎ ያደርጋል። በቅርቡም በቅርቡ 'የነጻነት ንስሃ' [ስሓ ናፅነት] የተሰኘ የግጥም መድብል አሳትሟል።

“ከሀገራችን ለመውጣት ሳንፈራ፣ እዚህ ምን ያስፈራናል?” በማለት ቢያንስ በአገሪቱ በፈላጭ ቆራጭ አስተዳደር ስር ለሚሰቃየው ህዝብ ድምጽ የመሆን ሃላፊነት እንዳለበት ይናገራል።