በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ወሳኝ ሚና የነበራቸው ሐሰተኛ የጦር መሣሪያዎች

ሃሰተኛ የጦር መሣሪያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ናዚዎች በርካታ የአውሮፓ አገራትን ከወረሩ በኋላ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተፋፍሞ ወደ ፍጻሜው የደረሰው የኅብረቱ ኃይሎች ድል ቀንቷቸው የሰሜናዊ ፈረንሳይ የባሕር ዳርቻ የሆነችውን ኖርማንዲን የተቆጣጠሩ በዚህ ሳምንት ከ80 ዓመት በፊት ነበር።

ይህ የኖርማንዲ ድል በናዚዎች ቁጥጥር ሥር ለወደቁት እና በናዚ የወረራ ስጋት ተደቅኖባቸው ለነበሩ የአውሮፓ አገራት ተስፋን ከመስጠቱ ባሻገር፣ አውሮፓን ወደ ነጻነት የመራ ዘመቻ እንደሆነ ይነገርለታል።

የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት በአሸናፊነት ለመወጣት በርዕየተ ዓለም የተለያዩት ምዕራባውያኑ እና የምሥራቅ ሶሻሊስቶች በጋራ ከመቆማቸው በተጨማሪ ያላቸውን አቅም ሁሉ አሰልፈው ነበር።

ከእነዚህም መካከል ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከፈነዳ በኋላ እንግሊዝ ውስጥ እውነተኛ የሚመስሉ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ማታለያ የሆኑ ታንኮች እና አውሮፕላኖች ተዘጋጅተው ነበር። ይህ የሆነው ናዚዎችን ለማጭበርበር ነው።

80ኛ ዓመት የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲታወስ በሂትለር አገዛዝ ላይ ታሪክ የቀየረውን ክስተት መመልከት ጥሩ አጋጣሚ ነው።

ከስኬታቸው ጀርባ ግን በፊልም ኢንደስትሪው ውስጥ ያሉ እና ሚናቸው ብዙም የማይታወቅ ብዙዎች አሉ። ምክንያቱም ወረራዉ በፓስ-ደ-ካላይስ የእንግሊዝ ቻናል በኩል ሊፈጸም ነው ብሎ ጠላት እንዲየስብ በማድረግ ለማሳሳት ረድተዋል። ለመሆኑ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?

ኮሎኔል ጆን ተርነር የብሪታንያ ጦርን በማስመሰል ጠላትን ግራ ለማጋባት የማታለያ አውሮፕላን ማረፊያዎችን መገንባት ከጀመሩበት እአአ 1940 ይጀምራል።

ተርነር ከጦርነት በፊት የእንግሊዝ አየር ኃይል አባል እና ለጦሩ የአየር ማረፊያዎችን የሚገነቡ ዳይሬክተር ነበሩ። እአአ በ1939 ጡረታ ቢወጡም ግን የጡረታ ጊዜያቸው ተቋርጦ አዲስ የተቋቋመውን ከፍተኛ ምሥጢራዊ ክፍል እንዲመሩ እና የሐሰት የጦር አውሮፕላን ማረፊያዎችን እንዲገነቡ ተጠሩ።

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት

የፎቶው ባለመብት, Alamy

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኤር ማርሻል ሰር ሂዩዝ ዶውዲንግ የአየር ኃይሉ ተዋጊዎች ኃላፊ ነበሩ። የተርነርን ወደ ሥራ መመለስ ተቃወሙ። ገንዘብ ወጥቶ ማታለያ ቁሳቁሶች መሠራታቸውን አልፈለጉም። እውነተኛ የጦር መሣሪያዎችን እና የአየር ማረፊያዎችን መገንባት ነበር ምርጫቸው። ዶውዲንግ “ማስመሰያ” ሳይሆን “የሚጨበጥ ነገር” እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

የአየር ሚኒስቴሩ ግን ተርነር እንዲቀጥሉበት ነገራቸው። ተርነር ችግር ገጠማቸው። ይህም የአውሮፕላን አምራቾች እጅግ በጣም ውስብስብ የሆኑ እና የስለላ አውሮፕላኖችን በትክክል የሚመስሉ ሐሰተኛ አውሮፕላኖችን መሥራታቸው ነበር። በተጨማሪም በጣም ውድ ነበሩ። ተርነር ለሐሰተኛ መሣሪያዎቹ አዲስ አምራች መፈለግ ነበረባቸው። ኖርማን ሎዶን በዚህ ወቅት ብቅ አሉ።

እአአ በ1930ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሎዶን የተባሉ ስኮትላንዳዊ ነጋዴ ከለንደን በስተ ምዕራብ 30 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ መኖሪያ ቤት ገዙ። እአአ በ1932 ሼፐርተን በተባለው መኖሪያ ግቢያቸው ውስጥ የፊልም ስቱዲዮ ከፈቱ። ሁለት ትላልቅ የድምፅ መድረኮችን ገነቡ።

ዘመናዊውን የድምጽ ቴክኖሎጂ ያላቸው ስቱዲዮዎች፣ መልበሻ ክፍሎች፣ ወርክሾፖችን እና ለፊልም ሥራ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን ሁሉ አካተው ገንብተዋል። ስቱዲዮቸውንም 'ሳውንድ ሲቲ' ሲሉ ጠሩት።

የሼፐርተን ስቱዲዮዎች ብዙም ሳይቆዩ ስኬታማ ሆነው በ1939 አቅማቸው በእጥፍ ጨመረ። ሳውንድ ሲቲ አሌክሳንደር ኮርዳን የመሳሰሉ አዘጋጆችን፣ አንቶኒ አስኩትን የመሳሰሉ ዳይሬክተሮች እና የፊልም አርታኢው ዴቪድ ሊያን ያሉ ምርጥ ፊልም ባለሙያዎችን ለመሳብ በቃ።

ሌሎች ተሰጥኦ ያላቸው ባለሙያዎችም በሙያቸው ማደግ ችለው ነበር። የጦርነቱ መቀስቀስ ግን በብሪታኒያ ፊልም ላይ ትልቅ ውድቀት አመጣ። ቴክኒሻኖች ለጦርነት ዘመቱ። ለፊልም የሚውለው ገንዘብም ተንኮታኮተ።

በሃሰተኛ መሣሪያ የጠላትን ትኩረት መቀየር ተቻለ

የፎቶው ባለመብት, Alamy

እአአ በ1940 ተርነር ከሎዶን ጋር ከተገናኙ በኋላ የፊልም ኢንዱስትሪው ሙሉ በሙሉ ሰው ሰራሽ የሆኑ ነገር ግን በካሜራ ሲታዩ እውነተኛ የሚመስሉ መሣሪያዎችን በመሥራት ልምድ እንዳላቸውው ተገነዘቡ። ለእሳቸውም ሐሰተኞቹን አውሮፕላኖች ሊገነቡ ይችላሉ።

ሸፐርተን ለቴክኒሻኖች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በማሰቡ ሎዶን በጨረታ ተሳትፈው 50 ሐሰተኛ ዌሊንግተን እና 100 ብሌንሃይም አውሮፕላኖችን ለመሥራት አሸነፉ። ወጪው በአውሮፕላን አምራቾች ከሚጠየቀው በአንድ ሦስተኛው ያነሰ ነበር። የአየር ኃይሉ ተደሰተ። ተርነር ሐሰተኛ አውሮፕላኖቹን አገኙ። ሎዶን ደግሞ በጦርነት ወቅት ለፊልም ቴክኒሻኖቹ ሥራ ፈጠረ።

3000 ኪሎ ሜትር በላይ ርቆ ደግሞ ካይሮ ውስጥ የእንግሊዝ ጦር አዲስ ክፍል አቋቋመ። ኤ-ፎርስ በመባል የሚታወቀውን ክፍል ፈር ቀዳጁ ሌተና ኮሎኔል ዱድሊ ክላርክ ይመሩታል። ሚናቸው ደግሞ ጣልያኖችን እና ጀርመኖችን በማታለል አቅማቸውን ማሳሳት ነበር።

አንዳንድ ማታለያዎቻቸው ባይሠሩም ግን ከስኬት እና ከውድቀታቸው ተምረዋል። ማታለሉ ውጤታማ እንዲሆን ጠላት አንድ ነገር እንዲያስብ ማድረግ ብቻ በቂ አይደለም። ኃይላቸውን በተሳሳተ ቦታ መተው ወይም ወታደሮችን አዲስ ጥቃት ከሚከፈትበት አቅጣጫ ማራቅ አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝበዋል።

የሌሉ ኃይሎችን በመፍጠር ጥበብ ውስጥ በፍጥነት ዝነኛ ሆኑ። አንድ የአየር ወለድ ብርጌድ በመፍጠር ጣሊያኖች ከኋላቻው ሊጠቁ ሆነው እንዲሰማቸው አደረጉ። በሰሜን አፍሪካ ግን ምንም ዓይነት አየር ወለድ አልነበረም። ስምንተኛው ክፍለ ጦር ከነበረው ጦር በጣም የሚገዝፍ ለማስመሰል ሐሰተኛ የጦር ሠራዊትን ፈጠሩ።

የሌለ ጦር መፍጠር

የፎቶው ባለመብት, Alamy

እአአ በ1942 በተካሄደው በኤል አላሜይን ጦርነት፣ ክላርክ እና አጋሮቻቸው የኅብረቱ ሠራዊት የጦርነቱ አቅጣጫ በስተደቡብ እንደሆነ እንዲያስቡ የሚያደርግ ሥራ ሠሩ። ከአውሮፕላን ሲታዩ ታንኮች እንዲመስሉ ተደርገው የተጋጁ ታንክ ጫኝ መኪኖች በአሸዋው ውስጥ ተዘጋጁ። ካገለገለ ቱቦ ደግሞ ምናባዊ የነዳጅ ማከማቻ መጋዘን ተሠራ።

ጀርመኖች ይህንን ስጋት ለመቀልበስ ሁለት የጦር ክፍሎችን በደቡብ አቅጣጫ አስቀመጡ። ጦርነቱ ሲጀመር ጄኔራል ሞንትጎመሪ ሰሜን በኩል ጥቃት ሰነዘሩ። ጦርነቱ ለ10 ቀናት የቆየ ከባድ ውጊያ ቢደረግበትም ግን ጠላትን ለማሸነፍ ስልቱ እንደረዳ ጥርጥር የለውም።

አታላዩ ዕቅድ

የጦር ዕቅድ ሲወጣ ጠላትን የማታለል አስፈላጊ ነበር። ቴህራን ውስጥ ከጆሴፍ ስታሊን ጋር ስለ ወረራው የተወያዩት ዊንስተን ቸርችል “በጦርነት ጊዜ እውነት በጣም ውድ ከመሆኑ የተነሳ ሁል ጊዜ የውሸት ጠባቂ መሳተፍ አለበት” የሚለውን ሐረግ ተጠቅመዋል። ይህ የኅብረቱን የማታለል ዕይታን በሚገባ ያሳያል።

ጄኔራል ሞንትጎመሪ ከአላሜይን ጦርነት በኋላ ጠላትን በተቻለ መጠን የማታለል ተግባር ከፍተኛ ደጋፊ ሆኑ። የ21ኛው ሠራዊት ቡድን ኃላፊ ሆነው በመሾም እና በኋላም የምድር ጦር አዛዥ ሆነዋል።

ጠላትን በማታለል ቀዳሚ የሆኑት ባልደረባቸው ሌተና ኮሎኔል ዴቪድ ስትራንግዌይስ፣ ጀርመኖች በካሌይ ክልል ውስጥ 15ኛ ሠራዊታቸውን እንዲያቆዩ ለማድረግ ብቸኛው መንገድ ኬንት፣ ኤሴክስ እና ሶፎልክ ውስጥ የተሟላ ሠራዊት እየተቋቋመ መሆኑን በማሳመን ነው ብለዋል። አታላዮቹ እና የእውነት ያልነበሩት 300 ሺህ የሠራዊት አባላት እንዴት ሊፈጠሩ ቻሉ?

ኦፕሬሽን ፎርቲቱድ በመባል የሚታወቀው የማታለል ዘመቻ ውስጥ ብዙ አካላት ነበሩ። ለሁለት ወገን የሚሰልሉ እና ወደ ብሪታንያ የተላኩ፤ በኋላም ለኤምአይ5 መሥራት የጀመሩ ጀርመናውያን ሰላዮች የተሳሳተ መረጃን ለጀርመን ኃላፊዎቻቸው አቀብለዋል። እነዚህ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ሳይንሳዊ ማታለያዎችም ነበሩ። የመርከቦችን ወይም የአውሮፕላኖችን ቡድን ለማመልከት የሐሰት ምልክቶች በሌሉበት ቦታ ተልከዋል።

የሌለውን ጦር ያለ ለማስመሰል አታላዮቹ ስም መስጠት ጀመሩ። የመጀመሪያው የአሜሪካ ጦር ቡድን፣ በምህፃረ ቃል ፉሳግ በመባል ይታወቃል። የሼፐርተን ፊልም ቴክኒሻኖች ለእዚህ የሌለ ጦር ሐሰተኛ ታንኮች እንዲገነቡ ተደረገ።

በብረት ፍሬም ዙሪያ ከጎማ እና ሸራ የተሠራ እንዲሁም በ30 ደቂቃ ውስጥ ሊነፋ የሚችል ታንክ ነው። በመቶዎች የሚቆጠሩ ተመርተው በመሰብሰቢያ ቦታዎች ላይ ተሰልፉ። ትልቅ ከሸራ እና ከእንጨት የተዘጋጀ አውሮፕላንም ሠሩ። እያንዳንዱን አውሮፕላን ለመገጣጠም 30 ሰዎች እና ከስድስት እስከ ሰባት ሰዓት ፈጅቷል።

በተጨማሪም በዶቨር የባሕር ዳርቻ ላይ የውሸት የነዳጅ ማከማቻ ተሠራ። ከእንጨት፣ ከፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች የተሠራው ማከማቻ ከመሬት ሲታይ ምንም አይሰብም። ከ20 ሺህ ጫማ ርቀት ሲታይ ግን እውነተኛ ይመስላል።

ሃሰተኛ ማረፊያዎች

የፎቶው ባለመብት, Imperial War Museum

አንዳንድ ነባር የአሜሪካ እና የካናዳ የጦር ክፍሎች ለፉሳግ እንዲሠሩ ተመድበዋል። ለማታለል እንዲሆንም የአሜሪካ ጦር የሬዲዮ መልዕክቶችን በአካባቢው እንዲልክ ታዟል።

ጀርመኖች እነዚህን ሁሉ መልዕክቶች መፍታት አላስፈለጋቸውም። በደቡብ-ምሥራቅ እንግሊዝ ብዙ ቁጥር ያለው ጦር እየተሰበሰበ መሆኑን ከሬዲዮ መልዕክቱ ብዛት መረዳት ችለዋል።

ግንቦት መጨረሻ ላይ የጀርመን ደኅንነቶች 79 የኅብረቱ የጦር ክፍሎች ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ እንደተሰባሰበ አስቦ ነበር። ትክክለኛው ቁጥር ግን 52 ብቻ ነበር።

እያንዳንዱ ጦር አዛዥ ስለሚያስፈልገው ጄኔራል ጆርጅ ኤስ ፓቶን የፉሳግ አዛዥ ሆነው ተሾሙ። በሚሄዱበት በጋዜጠኞች መከባበቸው እና ስለጦራቸው መነገሩ የጠላት ጆሮ ደረሰ። ጀርመኖች ከኅብረቱ ምርጥ ጄኔራሎች አንዱ በመሆናቸው የአውሮፓን ወረራ እንደሚመሩ አመኑ።

በኖርማንዲ ጦርነቱ ሲጀመር ግን ጀርመኖች ያልጠበቁት ገጠማቸው። በፍጥነት ስህተታቸውን በማረም በጥቂት ቀናት ውስጥ ከደቡብ እና ከምዕራብ ፈረንሳይ ተጨማሪ ጦር ለውጊያው አደረሱ።

ከኖርማንዲ ለመውጣት ለስድስት ሳምንት የተደረገው ትግል ረጅም እና ከባድ ነበር። ነገር ግን በወሳኝ በሆነ መልኩ የጀርመን 15ኛ ጦር በፓስ-ደ-ካላይስ ቆየ።

ጦርነቶች በኖርማንዲ እየተካሄዱ ባለበት ወቅት ከ150 ሺህ በላይ የጀርመን ወታደሮች 321 ኪሜ ርቀው ቁጭ ብለው ነበር። የማታለል ዘመቻው ኦፕሬሽን ፎርቲቲዩድም በጥሩ ሁኔታ ተሳካ።