አፍሪካ በኤድስ የሚከሰት ሞትን ለመግታት ወደ ኋላ ቀርታለች ተባለ

የአፍሪካ አገራት በ2030 በኤችአይቪ ኤድስ አማካኝነት የሚከሰት ሞትን ለማስቀረት የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ወደ ኋላ መቅረታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት አመለከተ።

ነገ ሐሙስ ተከብሮ የሚውለውን የዓለም የኤድስ ቀንን በማስመልከት በድርጅቱ ይፋ የሆነው ሪፖርት እንዳመላከተው በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጭቆና ብሎም አግላይ ሕጎች ለዕቅዱ መጓተት እንደምክንያት ተጠቅሷል።

ተመድ 90 በመቶ የሚሆኑ ኤችአይቪ በደማቸው የሚገኝ ሰዎች ተመርምረው ውጤታቸውን እንዲያውቁ፣ ብሎም ከዚህ ውስጥ 90 በመቶው የፀረኤችአይቪ መድኃኒት እንዲጀምሩ እና ከዚህ ውስጥ ደግሞ 90 በመቶው በደማቸው ውስጥ የሚገኘውን የቫይረስ መጠን ከ200 በታች የማድረግ ዕቅድ አለው።

ከሰሃራ በታች በሉ የአፍሪካ አገራት ውስጥ የሚኖሩ እድሜያቸው ከ15 እስከ 24 የሆኑ ሴቶች እና ልጃገረዶች ከወንዶች ጋር ሲነጻጸር፣ በሦስት እጥፍ ለኤችአይቪ የመጋለጥ ዕድል ሲኖራቸው በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ 5000 አዳዲስ ሴቶች በቫይረሱ ይያዛሉ።

“የአፍሪካ አገራት የሥነ ተዋልዶ ትምህርትን፣ ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች የሚሰጥ አገልግሎት፣ ብሎም የኤችአይቪ አገልግሎቶችን በጋራ በማጣመር መስጠት ይኖርባቸዋል። ይህም በጋራ ተጣምረው የሴቶችን ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት ሊሰጡ ይገባል” ሲሉ የተመድ የኤችአይቪ ኤድስ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ዊኒ ባያኒማ ተናግረዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም መንግሥታት የቫይረሱን ሥርጭት ለመቀነስ እንደ እንቅፋት የተጠቀሱ ሕጎቻቸውን እንዲያነሱም ጠይቀዋል።

“አግላይ ሕጎች ሰዎች ኤችአይቪን የሚመለከቱ አገልግሎቶችን እንዳያገኙ ብሎም የኤችአይቪ ተጋላጭነትን በመጨመር ከፍተኛ ሚና አላቸው። እነዚህ ሕጎች የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎችን ግንኙነትን፣ የወሲብ ንግድን፣ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት መጠቀምን ወንጀል የሚያደርጉ ሕጎች ይጠቀሳሉ” ሲሉም አክለዋል።

ለኤችአይቪ ከፍተኛ ተጋላጭነት ያላቸውን ሰዎች በወንጀል የሚጠይቁ አገራት በምርመራ እና በህክምናው ሂደት ላይ ዝቅተኛ ውጤት የሚያሳዩ ሲሆን፣ በርካታ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ሰዎች ተመርምረው ውጤታቸውን ሳያውቁ ይኖራሉ።