ቻትጂፒቲ ራሳቸውን ለማጥፋት የሚያስቡ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ይፋ አደረገ

ራስ የማጥፋት አዝማሚያን ጨምሮ ሌሎችም የአእምሮ እክሎች የገጠሟቸው የቻትጂፒቲ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ኦፕንኤአይ ይፋ አደረገ።

በአንድ ሳምንት ውስጥ ቻትጂፒቲን ከሚጠቀሙ ሰዎች መካከል 0.07 በመቶ የሚሆኑት ከመጠን ያለፈ መነቃቃት (mania)፣ የተዛባ የእውነታ ዕይታ (psychosis) እና ራስን ለማጥፋት ማሰብ (suicidal thoughts) እንደሚታይባቸው አስታውቋል።

በሰው ሠራሽ አስተውሎት አማካይነት የቻትጂፒቲ ተጠቃሚዎች ከሚያደርጉት ንግግር በመነሳት የአእምሮ ጤናቸውን ሁኔታ ለማወቅ ተችሏል።

ኦፕንኤአይ የአእምሮ ሕመም የሚያሳዩ ሰዎች "እጅግ ጥቂት ናቸው" ቢልም፤ ባለሙያዎች በበኩላቸው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚገጥማቸው እክል እንደሆነ አስረድተዋል።

ቻትጂፒቲ በየሳምንቱ 800 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች አሉት። መተግበሪያው ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን በመላው ዓለም ባለሙያዎች ማሰማራቱን ኦፕንኤአይ ገልጿል።

ከእነዚህ ባለሙያዎች መካከል በ60 አገራት የሚሠሩ 170 የሥነ ልቦና ባለሙያዎች እና ሕክምና ሰጪዎች ይገኙበታል።

እነዚህ ባለሙያዎች የቻትጂፒቲ ተጠቃሚዎች የሥነ ልቦና ባለሙያ በአካል አግኝተው እንዲያማክሩ ምክር ይሰጣሉ።

ኦፕንኤአይ ባለሙያዎች ማሰማራቱን ቢገልጽም እንኳን ተቋሙ የአእምሮ ጤናን በተመለከተ ይፋ የሚያደርጋቸው አሐዞች ጥያቄ አስነስተዋል።

በሳን ፍራንሲስኮ፣ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ካሊፎርንያ የሚያስተምሩት ዶ/ር ጄሰን ናጋት "በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩ የመተግበሪያው ተጠቃሚዎች 0.07% ውስን ቁጥር ቢመስልም ችግሩ የከፋ ነው" ብለዋል።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት የሥነ ልቦና ድጋፍ ተደራሽነትን "በጥቂቱ ቢያሰፋም ውስንነቶች አሉበት" ሲሉም ባለሙያው አስረድተዋል።

ከቻትጂፒቲ ተጠቃሚዎች መካከል 0.15 በመቶ የሚሆኑት "ራስን ስለማጥፋት" እንደሚያወሩ ተቋሙ ይፋ አድርጓል።

የኦፕንኤአይ ቻትቦች ራሳቸውን ለመጉዳት ወይም ለማጥፋት ለሚያስቡ ሰዎች "በተገቢው እና ሐዘኔታ በተሞላው መንገድ ምላሽ እንዲሰጥ" ለማድረግ እንደሚሠራ ገልጿል።

ኦፕንኤአይ ከአእምሮ ጤና ጋር በተያያዘ የሚቀርቡበትን ትችቶች በተመለከተ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ፤ ጉዳዩን በአንክሮ እንደሚከታተል ምላሽ ሰጥቷል።

ቻትጂፒቲ ለተጠቃሚዎች ከሚሰጠው ምላሽ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ክሶች ተከፍተዋል።

በቅርቡ ካሊፎርንያ የሚኖሩ ጥንዶች ቻትጂፒቲ ታዳጊ ልጃቸው ራሱን እንዲያጠፋ እንደገፋፋው በመግለጽ ኦፕንኤአይን ከሰዋል።

የ16 ዓመቱ አዳም ሬን ጉዳይ ኦፕንኤአይ ከተከሰሰባቸው ከሞት ጋር የተያያዙ ወንጀሎች ከባዱ ነው።

በዩኒቨርስቲ ኦፍ ካሊፎርንያ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሕግ ባለሙያ ፕሮፌሰር ሮቢን ፍሌድማን "ቻትቦት የአእምሮ ሕመም ላለባቸው ሰዎች ምክር የሚሰጥ ይመስላል፤ ምክሩ ግን እውነተኛ አይደለም" ብለዋል።

የቻትጂፒቲ ተጠቃሚዎች የአእምሮ ሕመም እንዳለባቸው ከታወቀ በገጹ ማስጠንቀቂ ሊቀመጥ እንደሚገባም ባለሙያዋ ተናግረዋል።