ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ 'ከሦስተኛው ዓለም አገራት' የሚመጡ ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ቋሚ ዕገዳ ሊጥሉ ነው
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "ከሁሉም የሦስተኛው ዓለም አገራት" ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚያደርግ "ዘላቂ ዕገዳ" ለመጣል ዕቅድ እንዳላቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስታወቁ።
ትራምፕ ይህንን ዕቅዳቸውን ያስታወቁት በአሜሪካውያን ዘንድ የሚከበረውን "የምስጋና ቀን" በዓልን ምክንያት በማድረግ ባሰፈሩት መልዕክት ላይ ነው።
ይህ የፕሬዝዳንቱ ሃሳብ የተሰማው ባለፈው ረቡዕ አንድ አፍጋኒስታናዊ ስደተኛ ዋሽንግተን ውስጥ ሁለት የብሔራዊ ዘብ አባላት ላይ ተኩሶ ክፉኛ ካቆሳላቸው እና የአንደኛዋ ሕይወት ካለፈ በኋላ ነው።
ትራምፕ ይህንን ጥቃት ተከትሎ ለ19 የውጭ አገር ዜጎች የተሰጡ የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ እንደሚመረምር አዝዘዋል።
ትራምፕ በጽሑፋቸው "አሜሪካ ሙሉ ለሙሉ እንድታገግም ከሁሉም የሦስተኛ ዓለም አገራት የሚመጡ ስደተኞች ላይ ቋሚ እገዳ እጥላለሁ" እንዲሁም "በባይደን ዘመን ወደ አገሪቱ እንዲገቡ የተደረጉ ሚሊዮኖች ፈቃድን እሰርዛለሁ" ሲሉ ትሩዝ በተባለው የራሳቸው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ላይ አስፍረዋል።
የአሜሪካ የዜግነት እና የኢሚግሬሽን አገልግሎት ረቡዕ ዕለት ከብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ጋር በተያያዘ ለ19 አገራት ዜጎች ከዚህ ቀደም በአሜሪካ የተሰጡ የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃዶች እንዲሁም የቀረቡ ማመልከቻዎችን እንደሚመረምር አስታውቋል።
ከዚሁ ውሳኔ በተከታይነትም ፕሬዝዳንቱ "የሦስተኛው ዓለም" ካሏቸው አገራት የሚመጡ ስደተኞችን ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚያደርግ ቋሚ ውሳኔ እንደሚያሳልፉ አስታውቀዋል።
ትራምፕ ምንም ዓይነት ዝርዝር ማብራሪያ ሳይሰጡ በደፈናው "የሦስተኛው ዓለም አገራት" በማለት የጠቀሷቸው በምጣኔ ሀብት ዕድገት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉትን በዓለም ደቡባዊ ንፍቀ ክበብ ውስጥ የሚገኙትን አገራት እንደሆነ ይታመናል።
ከዕገዳው በተጨማሪም "ለአሜሪካ ጠቃሚ ሀብት የማይሆኑ ወይም አገሪቱን መውደድ የማይችሉትን" ጭምር ከአሜሪካ እንዲወጡ እንደሚያደርጉ አመልክተዋል።
እንዲሁም ዜጋ ላልሆኑ ሰዎች የሚሰጠው ሁሉም የፌደራል መንግሥቱ ጥቅማ ጥቅሞች በሙሉ እንደሚያስቆሙ አስታውቀዋል።
"የአገሪቱን ሰላም የሚያናጉ፣ ክስ ያላባቸው ዜግነት ያገኙ የውጭ ሰዎችን ዜግነት መግፈፍ፣ የደኅንነት ስጋት የሆኑ፣ ከምዕራቡ ሥልጣኔ ጋር የማይስማሙ የውጭ ዜጎችን" ከአሜሪካ የማባረር ዕቅድ አላቸው።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ላይ ባሰፈሩት ረጅም ጽሑፍ ላይ "አብዛኞቹ" በአሜሪካ የሚኖሩ የውጭ ዜጎች "በቀውስ ውስጥ ካሉ አገራት፣ ከእስር ቤት፣ ከአእምሮ ሕሙማን ተቋማት የወጡ እንዲሁም ወሮበሎች ወይም ዕጽ አዘዋወሪዎች ናቸው" በማለት በአገሪቱ ለሚከሰቱ የወንጀል ድርጊቶች ተጠያቂ አድርገዋቸዋል።
ስደተኞችን በተመለከተ በትራምፕ አስተዳደር እየቀረቡ ያሉት ሃሳቦች ይፋ የሆኑት የ29 ዓመቱ የቀድሞ የሲአይኤ ሠራተኛ አፍጋኒስታናዊ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ነው።
ግለሰቡ በአፍጋኒስታን ጦርነት ወቅት የአሜሪካ ወታደሮችን የረዱ አፍጋናውያን ወደ አሜሪካ እንዲገቡ ባደረገው አሠራር መሠረት ወደ አገሪቱ የገባ ነው።
ሕገወጥ ስደትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስዱ በመግለጽ በዳግም የምርጫ ቅሰቀሳቸው ጊዜ የተናገሩት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከተመለሱ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስደዋል።
በዚህም ምክንያት ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንደቀነሱት እየተነገረ ነው።
ባለፈው ጥቅምት ወር የአሜሪካ መንግሥት እንዳስታወቀው በመጪው የአውሮፓውያን ዓመት 7,500 ብቻ ስደተኞችን እንደሚቀበል አስታውቋል። ይህም አሃዝ ከ1980 ወዲህ በጣም ዝቅተኛው ነው።