አፍጋኒስታን በሳምንት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ በርዕደ መሬት ተመታች

በአፍጋኒስታን ከ1 ሺህ በላይ ሰዎችን የገደለው ሁለት ከባድ ርዕደ መሬት ከተከሰተ ከቀናት በኋላ ምዕራባዊ ክፍሏ በሌላ ርዕደ መሬት ተመታ።

የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ እንዳለው በ6.3 ማግኒቲዩድ የተለካው ርዕደ መሬት የሔራት ከተማ አቅራቢያን መትቷል።

እንደ አካባቢው የጤና ባለሥልጣናት ከሆነ በዚህ ርዕደ መሬት ቢያንስ የአንድ ሰው ሕይወት አልፏል።ሌሎች 100 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸው በግዛቷ በሚገኝ ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

በቅርቡ ተከስቶ በነበረው ርዕደ መሬት ከሞቱት መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሴቶች እና ሕጻናት መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት ድርጅት ዩኒሴፍ መግለጹ አይዘነጋም።

የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ እንዳለው አዲስ የተከሰተው ርዕደ መሬት ማዕከል ያደረገው ከሔራት ሰሜን ምዕራብ 30 ኪሎ ሜትር የሚርቅን አካባቢ ነው።

ሔራት የአፍጋኒስታን ሦስተኛዋ ትልቅ ከተማ ስትሆን ከኢራን ጋር ትዋሰናለች።

ባለፈው ቅዳሜ የተከሰተው ርዕደ መሬት ከሔራት 40 ኪሎ ሜትር ገደማ የምትርቀውን የገጠር ወረዳ ዚንዳጃንን ነበር የመታው።

በአደጋው በዚህ አካባቢ የሚገኙ ከጭቃ የተገነቡና ርዕደ መሬቱን መቋቋም የማይችሉ ቤቶች ወደ ፍርስራሽነት ተለውጠዋል።

የመንደሩ ነዋሪዎች በፍርስራሽ ሥር የተቀበሩ ሰዎችን ለማውጣት ያለማንም እርዳታ አካፋ እና ባዶ እጃቸውን ተጠቅመዋል።

የመሬት መንቀጥቀጡ ካጋጠመ በኋላም በርካታ ነዋሪዎች መጠለያ አጥተው ባዶ ሜዳ ላይ ለመተኛት ተገደው ነበር።

ከአውሮፓውያኑ 2021 ጀምሮ አፍጋኒስታንን እያስተዳደረ ያለው ታሊባንም አሁን ላይ በርካቶች በድንኳን ውስጥ መሆናቸውን ገልጾ፣የቅዝቃዜ ወቅት እየመጣ ሲሄድ ግን ከአንድ ወር በላይ በዚያ መቆየት እንደማይችሉ ተናግሯል።

ታሊባን ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ አፍጋኒስታን ለመንግሥት በቀጥታ የሚሰጠው እርዳታ በመቆሙ በኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች።

አፍጋኒስታን ከምትገኝበት ሥፍራ ጋር በተያያዘም በተደጋጋሚ በርዕደ መሬት ተመታለች።

ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ፓክቲካ ግዛት በ5.9 ማግኒቲዩድ ርዕደ መሬት ተመትታ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች ሲሞቱ፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ያለ መጠለያ ቀርተዋል።