ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን የሚቃወም ሠልፍ በአሜሪካ ትልልቅ ከተሞች ተካሄደ
በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኙ ከተሞች የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ፖሊሲ በመቃወም በርካታ ሕዝብ ሠልፍ ወጣ።
ተቃዋሚ ሠልፈኞቹ አደባባይ ከወጡባቸው ከተሞች መካከል ኒው ዮርክ፣ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ቺካጎ፣ ማያሚ እና ሎስ አንጀለስ ይገኙበታል።
በኒው ዮርክ ከተማ በዝነኛው ታይምስ ስኩዌር የተካሄደው የተቃውሞ ሠልፍ ቅዳሜ ጠዋት የተጀመረ ሲሆን በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተቀላቅለውታል።
አውራ ጎዳናዎች እና የባቡር ትራንስፖርት መሳፈሪያ ስፍራዎች መፈክር በያዙ የተቃዋሚ ሠልፈኞች ተጥለቅልቀው ነበር።
ተቃዋሚዎቹ ከያዝዋቸው መፈክሮች መካከል "ዲሞክራሲ እንጂ ንጉሣዊ አስተዳደር አንፈልግም" እና "ሕገ መንግሥቱ አማራጭ አይደለም" የሚሉ ይገኙበታል።
ከሠልፉ በፊት የትራምፕ አጋሮች ተቃዋሚዎቹን የግራ ክንፍ አንቅስቃሴ ከሆነው አንቲፋ ጋር ግንኙነት አላቸው ሲሉ ከሰዋቸዋል።
አክለውም "ለአሜሪካ ጥላቻ ያላቸው ሠልፍ" ሲሉም አውግዘውታል።
ቅዳሜ ዕለት የተካሄደው የተቃውሞ ሠልፍ አስተባባሪዎች እና የታደሙ ሠልፈኞች ዝግጅቱ ሰላማዊ ነበር ሲሉ ተናግረዋል።
'ኖ ኪንግስ' በመባል የተሰየመው የተቃውሞ ሠልፍ አስተባባሪዎች በድረ ገጻቸው ላይ ዋናው መርህ ምንም ሁከት የሌለበት ትዕይንተ ሕዝብ ማካሄድ መሆኑን የገለፁ ሲሆን ተሳታፊዎችም ሊኖር ከሚችል ትንኮሳ ሁሉ ራሳቸውን እንዲርቁ አሳስቧል።
በኒው ዮርክ በሠልፉ ላይ የተሳተፉ የተወሰኑ ሰዎች "ዲሞክራሲ እንደዚህ ነው" የሚል ዝማሬ ያሰሙ ነበር።
ሄሊኮፕተሮች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች በሰልፈኞቹ ላይ ሲያንዣብቡ ፖሊሶችም የመንገዱን ዳር ይዘው ቆመው ነበር።
የኒውዮርክ ፖሊስ በአምስቱም የከተማዋ አውራጃዎች ከ100,000 በላይ ሰዎች በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን ለማሰማት መሰባሰባቸውን እና ከተቃውሞ ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት ችግር እንዳልተፈጠረ ገልጿል።
በታይምስ ስኩዌር አንድ የፖሊስ መኮንን ከ20,000 በላይ የጠቃዋሞ ሠልፈኞች በ7ተኛ ጎዳና ላይ መታየታቸውን ግምቱን አስቀምጧል።
ጋዜጠኛዋ ቤት ዛስሎፍ በኒው ዮርክ የተካሄደውን የተቃውሞ ሠልፍ የተቀላቀለችው አሁን ባለው መንግሥት ስለተቆጣች እና እየሆነ ያለው ስለሚያስጨንቃት እንደሆነ ተናገራለች።
የትራምፕ አስተዳደር "ወደ ፋሺዝም እና ወደ አምባገነን መንግሥት" እያመራ ነው ስትልም ሁኔታውን ገልጻዋለች።
"ስለ ኒው ዮርክ ከተማ በጣም እጨነቃለሁ" የምትለው ጋዜጠኛዋ "ከብዙ እና ከብዙ ሰዎች ጋር እዚህ መሆኔ ተስፋ ይሰጠኛል" ብላለች።
በለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ ወደ ዋይት ሐውስ በድጋሚ የመጡት ትራምፕ የፕሬዚዳንታዊ ስልጣናቸውን ወሰን በማስፋት፣ የፌዴራል መንግሥትን አንዳንድ ክፍሎች ለማፍረስ እና የብሄራዊ ዘብ ወታደሮችን ወደ አሜሪካ ከተሞች በማሰማራት ከግዛት አስተዳዳሪዎች ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።
የአስተዳደሩ ከፍተኛ የሕግ አስፈፃሚ አካላት ጠላቶቼ የሚሏቸውን ለፍርድ እንዲያቀርቡም ጠይቀዋል።
ፕሬዚዳንቱ የወሰዱት እርምጃ በችግር ላይ ያለች አገርን መልሶ ለመገንባት አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ አምባገነን ወይም ፋሽስት ናቸው የሚለውን አባባል አስቂኝ ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።
ነገር ግን ተቺዎቻቸው በአስተዳደሩ የሚወሰዱት አንዳንድ እርምጃዎች ሕገ መንግሥታዊ ያልሆኑ እና ለአሜሪካ ዲሞክራሲ ጠንቅ ናቸው ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
በጣሊያን ያደጉት የ68 ዓመቱ ማሲሞ ማስኮሊ ነዋሪነታቸው በኒው ጀርሲ ሲሆን አሜሪካ የትውልድ አገራቸው ባለፈው ክፍለ ዘመን የሄደችበትን ዓይነት መንገድ እየተከተለች መሆኗ ስላሳሰባቸው ተቃውሟቸውን ለመግለጽ አደባባይ መውጣታቸውን ተናግረዋል።
ማስኮሊ "እኔ የሙሶሎኒ ጦርንን ከድቶ የሚደረገውን ትግል የተቀላቀለ ጀግና ጣሊያናዊ ያፈራኝ ልጅ ነኝ" ብለዋል።
ቤተሰባቸው "በፋሺስቶች ተሰቃይቷል እና ተገድሏል" ሲሉ በማስታወስ " ከ 80 ዓመታት በኋላ እንደገና ፋሺዝም በዩናይትድ ስቴትስ አገኛለሁ ብዬ አልጠበኩም ነበር" ሲሉ ስጋታቸውን ተናግረዋል።
ማስኮሊን የትራምፕ አስተዳደር በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ አሜሪካውያን የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ማቋረጣቸው እና ስደተኞችን ከአገር ለማስወጣት እየወሰዱት ያለው እርምጃ ያሳስባቸዋል።
"በጠቅላይ ፍርድ ቤት ላይ መተማመን አንችልም፤ በመንግሥት ላይ መተማመን አንችልም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"በኮንግረሱ ላይ መተማመን አንችልም። አሁን በአሜሪካ ሕዝብ ላይ የተነሱ ሁሉም የሕግ አውጪ፣ አስፈፃሚ እና የፍትህ አካላት አሉን። ስለዚህ እንታገላለን።"
በዋሽንግተን ዲሲ የቬርሟንት ሴናተር በርኒ ሳንደርስ ለሠልፈኞቹ ንግግር አድርገዋል።
"እዚህ የተገኘነው አሜሪካን ስለምንጠላ አይደለም፤ እዚህ ያለነው አሜሪካን ስለምንወድ ነው" ሲሉ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ተናግረዋል።
በዲሲ በተካሄደው ሠልፍ ላይ አንድ ግለሰብ የትራምፕን "አሜሪካን ዳግም ታላቅ ማድረግ" የሚል መፈክር ያለበት ኮፍያ ያደረገ እንደነበር ቢቢሲ ተመልክቷል።
ከተማዋን እየጎበኘ እንደሆነ እና ተቃውሞውን ለማየት መምጣቱን ተናግሯል።
ስሙን ለመናገር ፈቃደኛ ያልሆነው ይህ ግለሰብ ምን እየተካሄደ እንደሆነ "በትክክል ባይገባኝም" ሰዎቹ ግን ሠላማዊ ነበሩ ሲል ተናግሯል፤ ብዙም ሳይቆይ አንዲት ሴት የነቀፋ አስተያየት ጮሃ ሰጥታለች።
ተቃውሞዎቹ ከአሜሪካ ውጭም በመላው አውሮፓ በርሊን፣ ማድሪድ እና ሮም ሰዎች ለአሜሪካ አቻዎቻቸው አጋርነታቸውን የሚያሳዩ ሠልፎች አካሂደዋል።
በለንደን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች በአሜሪካ ኤምባሲ ደጃፍ ተሰባስበው ነበር።
በቶሮንቶ ተመሳሳይ ትዕይንቶች ነበሩ፣ በአሜሪካ ቆንስላ አቅራቢያ ያሉ ሠልፈኞች "ከካናዳ ላይ እጅህን አንሳ" የሚሉ ምልክቶችን ሲያውለበልቡ ነበር።
ፎክስ ኒውስ እሁድ የሚያስተላልፈውን የዶናልድ ትራምፕ ቃለ መጠይቅ ማስቃወቂያ ቅዳሜ ዕለት ሲለቅ የሚካሄዱ ሰልፎችን በተመለከተ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
"ንጉሥ! ይህ ትርዒት አይደለም" ሲሉ ተደምጠዋል በማስታወቂየው ላይ።
"ስለ እኔ እየተናገሩ እንደሆነ ታውቃለህ ። እኔ ንጉሥ አይደለሁም"