ትራምፕ፤ በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ለተፈረደባቸው የቀድሞ የሆንዱራስ ፕሬዝዳንት ምሕረት እንደሚያደርጉ ተናገሩ

የቀድሞው የሆንዱራስ ፕሬዝዳንት ኹዋን ኦርላንዶ ኸርናንዴዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አደንዛዥ ዕፅ በማዘዋወር ወንጀል በአሜሪካ ፍርድ ቤት ወንጀለኛ ለተባሉት የቀድሞው የሆንዱራስ ፕሬዝዳንት ኹዋን ኦርላንዶ ኸርናንዴዝ ምሕረት እንደሚያደርጉ አስታወቁ።

ትራምፕ ይህንን ውሳኔ ይፋ ያደረጉት አርብ ዕለት ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ልጥፍ ነው። ምሕረት ለተደረገላቸው የቀድሞው ፕሬዝዳንት 'የእንኳን ደስ አለህ' መልዕክት ያስተላለፉት ትራምፕ፤ የኸርናንዴዝ ጉዳይ "በከባድ እና ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ" ተይዞ ነበር ብለዋል።

ኸርናንዴዝ፤ በመጋቢት 2016 ዓ. ም. የጥፋተኝነት ውሳኔ የተላለፈባቸው ወደ አሜሪካ ኮኬይን ለማስገባት አሲረዋል እንዲሁም 'የማሽን ጋን' ይዘው ተገኝተዋል በሚል ነው። ፍርድ ቤት በቀድሞው ፕሬዝዳንት ላይ የ45 ዓመታት እስር ፈርዷል።

የናሽናል ፓርቲ አባል የሆኑት ኸርናንዴዝ ከአውሮፓውያኑ 2014 እስከ 2022 ድረስ ፕሬዝዳንት ሆነው አገሪቷን መርተዋል። በሚያዝያ 2022 ደግሞ አደገኛ የደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን በመምራት ሴራ እንዲሁም በመቶዎች ቶን የሚቆጠር ኮኬይን ወደ አሜሪካ እንዲገባ በማገዝ ወንጀሎች ተጠርጥረው ለፍርድ ወደ ለዋሽንግተን ተላልፈው ተሰጥተዋል።

በኒው ዮርክ ፍርድ ቤት በተካሄደው የክስ ሒደትም ከሁለት ዓመት በፊት ጥፋተኛ ተብለዋል። ትራምፕ ምሕረት መደረጉን ባስታወቁበት ልጥፍ፤ በመጪው እሑድ በሆንዱራስ በሚደረገው አጠቃላይ ምርጫ የወግ አጥባቂዎች ተወካይ ሆነው ለሚወዳደሩት ቲቶ አስፉራ ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።

የሆንዱራስ ምርጫ ውጤትን በተመለከተ የተሰበሰበ የሕዝብ አስተያየት እንደሚያሳየው በእጩነት የቀረቡት ሦስት እጩዎች ተቀራራቢ የአሸናፊነት ግምት ተሰጥቷቸዋል። የመጀመሪያው እጩ የቀድሞው የቴጉሲጋልፓ ከንቲባ እና የአሁኑ የብሔራዊ ፓርቲ መሪ አስፉራ ናቸው።

የገዢው 'ሊብሬ ፓርቲ' እጩ የሆኑት የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር ሪክሲ ሞንካዳ ሌላኛዋ ተወዳዳሪ ናቸው። ሦስተኛው ተፎካካሪ እጩ ደግሞ የሊብራል ፓርቲ ተወካይ የሆኑት የቴሌቪዥን አቅራቢው ሳልቫዶር ናስራላ ናቸው።

ትራምፕ በአርብ ዕለቱ ልጥፋቸው ሞንካዳ እና ናስራላን ተችዋል። ናስራላን "ጽንፍ የወጣ ኮሚኒስት" በማለት የጠሩት ትራምፕ፤ እኚህ እጩ የሚወዳደሩበት ብቸና ምክንያት የመራጮችን ድምጽ በሞንካዳ እና አስፉራን መካከል ለመከፋፈል ነው በማለት ጽፈዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አስፉራን ደግሞ "ለዴሞክራሲ የቆመ" እና የቬንዙዌላ ፕሬዝዳንት የሆኑት ኒኮላስ ማዱሮን ለመታገል የቆመ እጩ በማለት ገልጸዋል።

የትራምፕ አስተዳደር፤ ብዙዎች የተጭበረበረ በሚል ምርጫ ውድቅ ባደረጉት ምርጫ በድጋሚ የተመረጡት የቬንዙዌላ ፕሬዝዳንት ማዱሮንን የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ የወንል ቡድንን ይመራሉ በማለት ከስሷቸዋል።

ትራምፕ አክለውም፤ ማዱሮ "እና የእርሱ የናርኮ-ሽብርተኞች"፤ ኩባን፣ ኒካራጓን እና ቬንዙዌላን ተቆጣጥረዋል ብለዋል።

ከ2022 አንስቶ የሊብሬ ፓርቲን በወከሉት ፕሬዝዳንት ሲዮማራ ካስትሮ እየተመራች ያለችው ሆንዱራስ፤ ከኩባ እና ቬንዙዌላ ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራለች።

ይህም ቢሆን ግን ፕሬዝዳንቷ፤ ለረዥም ጊዜ የቆየውን ተጠርጣሪዎችን ለአሜሪካ አሳልፎ የመስጠት ስምምነት በማስጠበቅ ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን የትብብር ግንኙነት አስቀጥለዋል። በቀጣናው ያለውን የተደራጀ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ዒላማ በማድረግ ላይ የሚሳተፈው የአሜሪካ ዕዝ አሁንም በሆንዱራስ ካምፕ አለው።

አሜሪካ ነሐሴ ወር ላይ ባስጀመረችው የጸረ ናርኮቲክስ ዘመቻ አማካኝነት ከቬንዙዌላ ወደ አሜሪካ አደንዛዥ ዕጽ እያጓጓዙ ነበር ያለቻቸውን ጀልባዎች ላይ ጥቃቶች ፈጽማለች። በእነዚህ ጥቃቶች ከ80 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

የአሜሪካ የጦር ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት እንደሚናገሩት 'ኦፕሬሽን ሳውዘርን ስፒር' የተሰኘው የዚህ ዘመቻ ዓላማ ሰሜን፣ ማዕከላዊ እና ደቡብ አሜሪካ እንዲሁም ካሪቢያንን በሚያካትተው በምዕራባዊው ንፍቀ ክበብ የሚገኙ "የናርኮ-ሽብርተኞችን' ማስወገድ ነው።

ይሁን እንጂ የሕግ ባለሙያዎች፤ አሜሪካ ጀልባዎቹ አደንዛዥ ዕፅ ጭነው የነበረ ስለመሆኑ ምንም ማስረጃ አለማቅረቧን በመጥቀስ የተፈጸሙት ጥቃቶች ሕጋዊነት ላይ ጥያቄ አንስተዋል።