ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሐዋርድ ዩኒቨርስቲ ለራፐሩ ዲዲ የሰጠውን የክብር ዲግሪ ነጠቀ
በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው ታሪካዊው የጥቁር ዩኒቨርስቲ ሐዋርድ ለአሜሪካዊው ራፐር ሺን “ዲዲ” ኮምብስ የሰጠውን የክብር ዲግሪ ለመንጠቅ ውሳኔ አስተላለፈ።
ዩኒቨርስቲው ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው ራፐሩ የቀድሞውን ፍቅረኛውን ካሳንድራ “ኬሲ” ቩንቱራን በሆቴል ኮሪደር ላይ ሲደበድብ የሚያሳይ ከደህንነት መቆጣጠሪያ (ሲሲቲቪ) የተገኘ ቪዲዮ ሲኤንኤን ማስተላለፉን ተከትሎ ነው።
“በቅርቡ በተለቀቀው ቪዲዮ ላይ ላይ የታየው ባህርይ ከሐዋርድ ዩኒቨርስቲ መሰረታዊ እሴቶች እና እምነቶች ጋር የማይጣጣም በመሆኑ የተቋሙን ከፍተኛ ክብር መገለጫ ለመያዝ ብቁ አይደለም” ሲልም ዩኒቨርስቲው አርብ ዕለት በሰጠው መግለጫ አትቷል።
ሲኤንኤን የለቀቀው ቪዲዮ ሾን ኮምብስ በወቅቱ ፍቅረኛው የነበረችው ካሳንድራን ወደ መሬት ገፍትሮ ከጣላት በኋላ በወደቀችበት ሲመታት ያሳያል።
ራፐሩ ቪዲዮው መውጣቱን ተከትሎ በቀድሞ ፍቅረኛው ካሳንድራ “ካሲ” ቬንቱራ ላይ ባደረሰው ጥቃት መጸጸቱን በመግለጽ ይቅርታ ጠይቋል።
ሙዚቀኛው በኢንስታግራም ገፁ በለቀቀው ቪዲዮ "ይቅርታ ለማይገባው" ድርጊቱ ሙሉ ኃላፊነት እንደሚወስድ ተናግሯል።
"ባደረግኩት ጊዜ እጅግ ፀፅቶኝ ነበር። አሁንም በጣም ተፀፅቻለሁ።" ብሏል ዲዲ በመግለጫው።
አክሎም "በወቅቱ ባለሙያ የሆነ ሰው እንዲረዳኝ ሞክሬ ነበር። የሥነ-ልቡና ባለሙያ ምክር ወስጃለሁ። ፈጣሪዬንም ይቅርታ እና ሞገስ መልሶ እንዲያላብሰኝ ጠይቄዋለሁ።በጣም ይቅርታ።"ብሏል።
ሐዋርድ ዩኒቨርስቲ የክብር ዲግሪውን ለራፐሩ የሰጠው በአውሮፓውያኑ 2014 ነበር።ከክብር ዲግሪው በተጨማሪም በስሙ የሚሰጠውን የትምህርት ዕድል (ስኮላርሺፕ) እንደሚያቆም እና እንዲሁም ከራፐሩ ጋር የተደረገውን “የስጦታ ስምምነት” እንደሚያቋርጥ ዩኒቨርስቲው ገልጿል።
የስጦታው ስምምነት ራፐሩ ሾን ኮምብስ ከተሰኘው ፋውንዴሽኑ በኩል ያደረገው የአንድ ሚሊዮን ልገሳ አካል ነው።
የሾን ኮምብስ ፋውንዴሽን በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
የቀድሞ የረዥም ጊዜ ፍቅረኛውን ኬሲ ቬንቱራን ጨምሮ አራት ሴቶች ሙዚቀኛው ወሲባዊ እና አካላዊ ጥቃት አድርሶብናል ሲሉ ክስ መስርተውበታል።
ባለፈው ኅዳር ካሳንድራ በመድፈር እና የወሲብ ንግድ በመፈፀም ዲዲን ከሳው ጉዳዩ ከፍርድ ቤት ውጭ በድርድር ችሎት እንዲጠናቀቅ ተደርጎ ነበር።
ራፐሩ በዚያንም ወቅት ድርጊቱን እንዳልፈጸመ እና ገንዘብ በአፋጣኝ ለማግኘት የተደረገ “የሚያሳምም ውንጀላ ሲል ነው” የፈረጀው።
ከሁለት ወራት በፊት ሎስ አንጀለስና ማያሚ የሚገኙ የራፐሩ መኖሪያ ቤቶች በፌዴራል የምርመራ ቡድን አባላት ድንገተኛ ፍተሻ ተደርጎባቸዋል።