ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቱርክ በእስር ላይ የሚገኙት ዝነኛው ከንቲባ ከ2000 ዓመታት በላይ እንዲፈረድባቸው ጠየቀች
የቱርክ ትልቋ ከተማ ኢስታንቡል ዐቃቤ ሕግ ዝነኛው ከንቲባ ኢክሬም ኢማማጉሉ በተከሰሱበት 142 የሙስና ወንጀሎች ከ828 እስከ 2,352 ዓመታት የእስር ዘመን እንዲፈረድባቸው ጠየቀ።
ኢማማጉሉ የፕሬዚዳንት ጣይብ ኤርዶዋን ዋነኛ የፖለቲካ ተቀናቃኝ ተደርገው የሚቆጠሩ ሲሆን ከባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ ይገኛሉ።
የኢስታንቡል ከንቲባ እና ተቃዋሚው የሪፐብሊካን ፒፕልስ ፓርቲ (ሲኤችፒ) ምንም ዓይነት ጥፋት እንዳልፈጸሙ በመከራከር ፕሬዚዳንቱ እና አጋሮቻቸው የኤርዶዋንን ተቀባይነት ማሽቆልቆሉን ተከትሎ እርምጃ ወስደዋል ሲሉ ይከስሳሉ።
ነገር ግን የከተማዋ ዋና ዐቃቤ ሕግ ኢማሞግሉን ብቻ ሳይሆን 401 ሰዎች ላይ ክስ የመሠረቱ ሲሆን ከከንቲባው ጋር በሙስና የተዘፈቀ የወንጀል ቡድን "በመመስረት እና በመምራት" ክስ መስርቶባቸዋል።
ከስምንት ወራት ምርመራ በኋላ ዐቃቤ ሕግ አኪን ጉርሌክ እንደተናገሩት 105 በእስር ላይ የሚገኙት ተጠርጣሪዎቹ ጉቦ በመቀበል እንዲሁም በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ላይ የተሰማራ ትልቅ ወንጀለኛ ድርጅት መስርተዋል ብሏል።
በዚህም የተነሳ በቱርክ ላይ የደረሰው ኪሳራ 3.8 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን አቃቤ ሕጉ ጨምረው ተናግረዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ 2028 በሚደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ኢማማጉሉ የሲኤችፒ ፓርቲ እጩ ሆነው የተመረጡ ሲሆን 12 ክሶች ጉቦ በመስጠት፣ ሰባት ሕጋዊ ያልሆነ ገንዘብን ሕጋዊ በማስመሰል እና ተጨማሪ ሰባት በመንግሥት እና የሕዝብ ድርጅቶች ላይ የማጭበርበር ወንጀል ክሶች ቀርቦባቸዋል።
አናዶሉ የዜና ወኪል ክሱ በ2,430 ዓመት እስራት እንደሚያስቀጣ ገምቷል።
በመጋቢት ወር ከንቲባው በቁጥጥር ሥር ሲውሉ ከፍተኛ ተቃውሞ ተቀስቅሶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሲታሰሩ ፖሊስም ተጨማሪ መጠነ ሰፊ እርምጃ ወስዷል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከንቲባው በኢስታንቡል ወጣ ብሎ በሚገኘው የማርማራ እስር ቤት ውስጥ ታስረው ይገኛሉ።
በከንቲባው ላይ ከቀረቡት የሙስና ክሶች በተጨማሪ በስለላ እና የትምህርት ማስረጃቸውን በማጭበርበር ወንጀሎች አቃቤ ሕግ ክስ መስርቶባቸዋል። የትምህርት ማስረጃቸው ከዚህ ክስ በኋላ ውድቅ ሆኗል።
የቱርክ ባለስልጣናት ከንቲባው የፍትህ አካላትን ለፖለቲካ መሣሪያነት እየተጠቀሙበት ነው በሚል ያቀረቡትን ውንጀላ ውድቅ አድርገዋል። ሆኖም የዩኒቨርሲቲ ዲፕሎማ ከሌላቸው በ2028 ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር አይችሉም።
የፓርቲው መሪ ኦዝጉር ኦዝል በኤክስ ገጻቸው ላይ "ይህ ክስ የሕግ ጉዳይ አይደለም፤ ሙሉ በሙሉ ፖለቲካዊ ነው። ዓላማው ባለፈው ምርጫ ያሸነፈውን ሲኤችፒን ማስቆም እና ፕሬዚዳንታዊ እጩውን ማገድ ነው" ሲሉ ጽፈዋል።
ቀደም ሲል የሲኤችፒ የፓርላማ ቡድን ስብሰባ ላይ ፓርቲያቸውን ወክሎ ማንም ሰው ለፕሬዚዳንትነት እንደማይወዳደር ተናግረው ነበር።
"ወንጀሉ የአገሪቱ ቀጣይ ፕሬዚዳንትነት ሆኖ መወዳደሩ ነው፤ ሌላ ወንጀል የለበትም!" ሲሉም ተደምጠዋል።
የ54 ዓመቱ ኢማሞግሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ከንቲባ ሆነው የተመረጡት እአአ በ2019 ሲሆን ዳግም እአአ በ2024 የገዢውን ኤኬ ፓርቲ እጩ ወደ አንድ ሚሊዮን በሚጠጋ ድምጽ በመብለጥ አሸንፈዋል።
ቀደም ሲል የኢስታንቡል ዐቃቤ ሕግን በመሳደብ እና በማስፈራራት ተከስሰው በሐምሌ ወር የተፈረደባቸውን የአንድ ዓመት ከስምንት ወር እስራት ይግባኝ ብለው ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ ናቸው።
የምርጫ አስፈፃሚዎችን በመተቸት ቀደም ሲል የተፈረደባቸውን የእስር ቅጣት ላይም ይግባኝ ጠይቀዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት የቀረበባቸው የስለላ ክስ ኢማሞግሉ ለዓለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፍ በሚል የኢስታንቡል ነዋሪዎችን መረጃ አሳልፈው ሰጥተዋል የሚል ነው።
ኢማሞግሉ ቱርካውያንን "ይህን የስለላ ረብ የለሽ ክስ እርሱት" ሲሉ ጠይቀዋል።
የፓርቲው መሪ የሆኑት ኦዝጉር ኦዝል ከንቲባውን ከእስር ላለመፍታት ወንጀሎችን እየፈጠሩ ነው ሲሉ ባለስልጣናትን ከስሰዋል።
"በምርጫ ማጭበርበር፣ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በመያዝ፣ ሌባ፣ አሸባሪ እና ሰላይ ሆኖ በተመሳሳይ ጊዜ መሆን ይችል ነበር?" ሲሉ ማክሰኞ ዕለት ለተሰበሰቡት የፓርላማ አባላት የፓርቲው ተወካዮች ጠይቀዋል።