የቱርክ ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ ስለ ጋዛ ሕጻናት እንዲናገሩ ተማፀኑ

የቱርክ ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ በጋዛ ጦርነት ስለሚሰቃዩ ሕጻናት እንዲናገሩ ጥሪ አቀረቡ።

ኤሚን ኤርዶዋን የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት ሩሲያ በዩክሬን ላይ ባካሄደችው ሙሉ ወረራ ስለተጎዱ ሕጻናት የሚያደርጉትን ድጋፍ አድንቀው ይህንን ለፍልስጤማውያን ሕጻናትም "በመናገር እንዲቀጥሉት" ጠይቀዋል።

በቱርክ ፕሬዝዳንት ገጽ ላይ ቅዳሜ ዕለት በተለጠፈው በዚህ የተማጽኖ ደብዳቤ ላይ ኤሚን ኤርዶዋን ጋዛ "የሕጻናት መቃብር" ሆናለች ብለዋል።

ለሜላኒያ ትራምፕ "ድምፃችንን እና ጥንካሬያችንን በዚህ ኢ-ፍትሃዊነት ላይ አንድ ማድረግ አለብን" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፉ የምግብ ዋስትና ባለሙያዎች በጋዛ ከተማ ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች በረሃብ እየተሰቃዩ መሆናቸውን ይፋ አድርገው፤ 132,000 ሕጻናት በምግብ እጦት ስጋት ላይ ወድቀዋል ብለዋል።

ኤሚን ኤርዶዋን "በሺህ በሚቆጠሩ የጋዛ ሕጻናት ላይ የተጻፈው 'የማይታወቀው ሕጻን' የሚለው ሐረግ በህሊናችን ውስጥ የማይሽር ጠባሳ ትቶ ያልፋል" ሲሉ ጽፈዋል።

ደብዳቤው ሜላኒያ ትራምፕ "በጦርነቱ ሕይወታቸውን ላጡ የዩክሬን ልጆች ያሳዩትን ተመሳሳይ ስሜት ለጋዛ ሕጻናትም እንዲያሳዩ" ሲል ጠይቋል።

ኤርዶዋን የአሜሪካዋን ቀዳማይ እመቤት ሜላኒያ ትራምፕን በቀጥታ ለእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ "በጋዛ ያለውን ሰብአዊ ቀውስ እንዲያቆሙ" ጥሪ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋቸዋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ሜላኒያ ትራምፕ ለሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ልጆችን እንዲያስቡ በመማጸን ደብዳቤ የላኩ ሲሆን የትኞቹን ልጆች እንደሆነ ግን በይፋ አልጠቀሱም።

የቱርክ ቀዳማዊት እመቤት አብዛኛውን ጊዜ በፖለቲካ ውስጥ አይሳተፉም።

ከዚያ ይልቅ ከተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ምስጋና ባገኙበት በአካባቢ ጉዳዮች ንቁ ተሳታፊ መሆን ይመርጣሉ።

ነገር ግን ኤርዶዋን በ 2016 በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ያሉ ሶሪያውያንን በመወከል እና በመጋቢት ወር ውስጥ በጋዛ የእስራኤልን ድርጊት በማውገዝ ለዓለም መሪዎች የትዳር አጋሮች ደብዳቤ ጽፈዋል።

ደብዳቤው ይፋ የሆነው በጋዛ ውስጥ ስላለው አስከፊ የሰብዓዊ ሁኔታ ሪፖርት መውጣቱን ተከትሎ ነው።

በዓለም ዙሪያ የረሃብ ደረጃን የሚመድበው በተባበሩት መንግሥታት ድጋፍ ያለው ተቋም በጋዛ ያለውን የምግብ ዋስትና በጣም የከፋ እና ከባድ ሁኔታ ላይ በመድረሱም ከፍተኛው አምስተኛ ደረጃ ላይ መድቦታል።

ተቋሙ በጋዛ ረሃብ መከሰቱን አረጋግጦ ከ640,000 በላይ ሰዎች ከነሐሴ አጋማሽ እና በመስከረም መጨረሻ ድረስ ባሉት ጊዜያት "አሰቃቂ ሁኔታዎች" እንደሚገጥሟቸው አስጠንቅቋል።

የተቀናጀ የምግብ ዋስትና ደረጃ ምደባ (አይፒሲ) ከሆነ በመላው ጋዛ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ፍልስጤማውያን "በረሃብ፣ በቸነፈር እና በሞት" አሰቃቂ ሁኔታዎችን እያለፉ ነው ብሏል።

ተቋሙ አርብ ዕለት ባወጣው ሪፖርት በተለይ በሕጻናት ላይ የተከሰተውን የምግብ እጥረትን ይፋ ያደረገ ሲሆን በጋዛ ውስጥ ከሦስት ሕጻናት አንዱ ከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አለባቸው ብሏል።

እንዲሁም እስከ ሰኔ 2026 ድረስ፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ የ132,000 ሕጻናትን ሕይወት አደጋ ላይ እንደሚጥል ግምቱን አስቀምጧል።

በጋዛ በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በምግብ እጥረት ከሞቱት 281 ሰዎች መካከል 114ቱ ሕጻናት ናቸው።

እስራኤል በጋዛ ረሃብ የለም ስትል የምታስተባብል ሲሆን፤ በተጨማሪም የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሙያዎች አድሏዊ ናቸው፣ ረሃብን የሚገመግሙበትን መስፈርት ቀይረዋል እንዲሁም ከሐማስ የሚመጡ መረጃዎችን ይጠቀማሉ ስትል ትከስሳለች።

የመንግሥታቱ ድርጅት ግን ይህንን ውንጀላ ውድቅ አድርጎታል።

ይህ ሪፖርት የወጣው እስራኤል የጋዛ ከተማን ለመውረር ያለመ አዲስ ወታደራዊ ጥቃት ለመሰንዘር በዝግጅት ላይ ባለችበት ወቅት ነው።

የጋዛ ጤና ሚኒስቴር ከእስራኤል ጥቃት በኋላ ባለፉት 24 ሰዓታት 61 ሰዎች መሞታቸውን ገልጿል።

በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት ሁለት ህጻናትን ጨምሮ የስምንት ሰዎች ሕይወት ማለፉንም አስታውቋል።

የፍልስጤም የዜና ወኪል ዋፋ እንደዘገበው በደቡባዊ ካን ዮኒስ የተፈናቃዮች መጠለያ ላይ በተሰነዘረ ጥቃት 19 ሰዎች ተገድለዋል።

ሐማስ መስከረም 26 2016 ዓ.ም. በደቡባዊ እስራኤል ድንገተኛ ጥቃት ከፍቶ 1,200 ሰዎች ከገደለ እና 251 ሌሎችን ካገተ በኋኃ እስራኤል በገዛ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ከፍታለች።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጋዛ ቢያንስ 62,122 ሰዎች ተገድለዋል ሲል የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

አብዛኛው የጋዛ ሕዝብ በተደጋጋሚ የተፈናቀለ ሲሆን ከ 90 በመቶ በላይ ቤቶች ወድመዋል አልያም ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሎ ይገመታል።

በጋዛ የጤና፣የውሃ፣ የአካባቢ ጽዳትና የግል ንፅህና አጠባበቅ ተቋማት ወድመዋል።