ለፆታዊ ጥቃት ተጎጂዎች የሥነ ልቦና ድጋፍ ሲያደርግ የነበረው አለኝታ ነፃ የስልክ መስመር በኢትዮ ቴሌኮም ተዘጋ

ለጥቃት ተጎጂዎች ሚስጥራዊነት ተጠብቆ የስነ ልቦና ድጋፍ የሚሰጥበት የአለኝታ 6388 ነፃ የስልክ መስመር
የምስሉ መግለጫ, ለጥቃት ተጎጂዎች ሚስጥራዊነት ተጠብቆ የስነ ልቦና ድጋፍ የሚሰጥበት የአለኝታ 6388 ነፃ የስልክ መስመር

ሴታዊት በተሰኘችው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት የተመሠረተው 'አለኝታ' ነፃ የስልክ መስመር ለፆታዊ ጥቃት ተጎጂዎች ይሰጥ የነበረውን የሥነ ልቦና ምክር እና ድጋፍ አገልግሎት ማቋረጡን አስታወቀ።

ላለፉት ስድስት ዓመታት በ'6388' ነፃ የስልክ መስመር ለተጎጂዎች የሥነ ልቦና ድጋፍን ጨምሮ የሕክምና እና የሕግ ጥቆማ ሲሰጥ የቆየው አለኝታ፤ ካለፈው የካቲት ወር ጀምሮ በኢትዮ ቴሌኮም ውሳኔ መሠረት መቋረጡን የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ስኂን ተፈራ (ዶ/ር) ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በፆታዊ ጥቃት ተጎጂዎች ጥያቄ እና በኢትዮጵያ በቀላሉ ምክር እና ድጋፍ የሚሰጥ ነፃ የስልክ መስመር አለመኖር አለኝታን ለመመሥረት ገፊ ምክንያት እንደነበር የሚያስረዱት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በስምምነት አገልግሎቱ በ2011 ዓ.ም. መጀመሩን ተናግረዋል።

የፆታዊ ጥቃት ተጎጂዎች ድጋፍ መስጫ የሆነው አለኝታ፤ በኢትዮ ቴሌኮም ውሳኔ መሠረት እንደተቋረጠ የሴታዊት ዳይሬክተር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቢቢሲ የኢትዮ ቴሌኮምን የሥራ ኃላፊዎች በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።

ነፃ የስልክ መስመሩን ያለ ክፍያ ከሚያቀርበው ኢትዮ ቴሌኮም ጋር በየዓመቱ ውል እንደሚያድሱ የጠቆሙት ኃላፊዋ፤ የኩባንያው ኃላፊዎች 'በደንብ አላስተዋወቃችሁንም' የሚል ተደጋጋሚ ቅሬታ እንደሚያነሱም ጠቁመዋል።

በዚህም አልፎ አልፎ መቆራረጦች እንደሚከሰቱ የተናገሩት ዳይሬክተሯ፤ በዚህ ዓመት ግን ኩባንያው ከተጎጂ ደዋዮች ገንዘብ መቁረጡን ተከትሎ በማኅበራዊ የትስስር ገፆች የማስተካከያ ጥያቄ ማቅረባቸው ለውሳኔው ምክንያት ሆኖ መቅረቡን ገልፀዋል።

"'በሶሻል ሚዲያ ስማችንን ስላጠፋችሁ ከዚህን ቀን በኋላ ተቋርጧል' ብለው ወዲያው ነው የቆረጡት። ምላሽም ምንም አልጠየቁመንም። ምላሽም ለመስጠት፤ ለማስረዳትም፤ ለማስተካከልም ምንም ዓይነት ክፍተት አልነበረም። ቁጥሩ ተቋረጠ" ሲሉ መስመሩ በዚህ መልኩ መቋረጡን አስረድተዋል።

አልፎ አልፎ ከሚደረጉ የስልክ ምልልሶች ውጭ በአለኝታ ለረጅም ጊዜ የሥነ ልቦና ድጋፍ ያገኙ ተጎጂዎች አንድ ሺህ 200 የሚሆኑ ሰዎች እንደሆኑ የተናገሩት ስኂን (ዶ/ር)፤ የአገልግሎቱን መቋረጥ "ልብ ሰባሪ" ብለውታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ባለፉት ዓመታትም ከተማሪዎች እስከ እናቶች ድረስ የአለኝታ አገልግሎት ተጠቃሚዎች መሆናቸውን ገልፀዋል።

አንድ የስልክ ምልልስ በአማካኝ 45 ደቂቃ እንደሚዘልቅ የሚያነሱት ስኂን (ዶ/ር) ተጎጂዎች ግላዊነታቸው ተጠብቆ በሥነ ልቦና ባለሞያዎች አገልግሎት እንደሚያገኙ ጠቁመዋል።

"ከሥነ ልቦና ድጋፍ የሚያልፍ ከበድ የሚል የአዕምሮ ህመም ከሆነ ሪፈራል እንሰጣለን። . . . ገፋ ሲልም መጠለያ [ማረፊያ] ለማስገባት ሙከራዎች እናደርጋለን" ሲሉ የአለኝታ አገልግሎት ሰፊ መሆኑን ገልፀዋል።

ከሥራ ቦታ ትንኮሳዎች እስከ መድፈር እና የቤት ውስጥ ጥቃቶች ድረስ አንድ ተጎጂዎች እስከ አንድ ዓመት የሚቆይ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርጉም አክለው ተናግረዋል።

በአለኝታ በተለይም ፆታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ብቻ ሳይሆኑ ለወንዶችም ጭምር አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊዋ፤ ከተጠቃሚዎቹ ውስጥ "40 በመቶ ወንዶች ሊሆኑ ይችላል" ብለዋል።

"አንደኛ ወንዶች ላይ ፆታዊ ጥቃት ሲደርስ የሚሄዱበት የትም ቦታ የለም፤ የሚናገሩበት ቦታ የለም። አዲስ አበባ ላይ [የወንዶች] መጠለያ እንኳ አንድ ወይም ሁለት ነው ያለው" ሱሉ ከዚህ ባሻገርም ወንዶች ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችን በሚመለከት ምክር እና ድጋፍ ፈልገው ወደ አለኝታ እንደሚመጡም ገልፀዋል።

"በየዓመቱ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ነው አተረፍን ብለው የሚናገሩት። በሴት የሚመራ የመንግሥት ግዙፍ ተቋም ነው" ሲሉ አለኝታ እንደ ማኅበረሰብ ግልጋሎት መታየት እንደነበረበት ገልፀዋል።

ውሳኔውንም ለተጎጂዎች "የደኅንነት ቦታ" መንጠቅ ነው ብለውታል።

"ጥቃት ሁልጊዜ እየጨመረ ነው። ማኅበራዊ ችግር አለ። ለአንድ ሰዓትም ቢሆን አይዞሽ የምንልበት አገልግሎት ነው የተቋረጠው። ለግፉአን የቆሙ አገልግሎቶች እየጎደሉ በሄዱ ቁጥር አንድ ኪሳራ ነው" ብለዋል።

የአለኝታን አገልግሎት ዳግም ለማስጀመር አማራጮችን እያማተሩ እንደሆነ የሴታዊት ዳይሬክተር ስኂን ተፈራ (ዶ/ር) ተናግረዋል።