የዩክሬን እና ሩሲያ ግጭት በተካረረበት ወቅት ኪየቭ በጥቁር ባህር ላይ ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን አጠቃች

የዩክሬን የባህር ኃይል ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቁር ባህርን አቋርጠው ይጓዙ የነበሩ ሁለት የነዳጅ ዘይት ጫኝ መርከቦችን መምታቱን የዩክሬን ባለሥልጣናት ገለፁ።

ቢቢሲ ትክክለኛነቱን ያረጋገጠው ተንቀሳቃሽ ምስል በውሃ ላይ የሚቀዝፉ ድሮኖች በውቅያኖሱ ሞገድ መካከል በመጓዝ በፍጥነት ወደ መርከቦቹ ሲገቡ ይታያል።

ሰው አልባ አውሮፕላኖቹ ወደ ነዳጅ ጫኝ መርከቦቹ ከገቡ በኋላ በመፈንዳት በእሳት እንዲያያዝ አድርገዋል።

ዒላማ የተደረገባቸው ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በቱርክ ባለሥልጣናት ካይሮስ እና ቪራት ተብለው የተሰየሙ ሲሆን ሁለቱም ወደ ጋምቢያ የሚሄዱ ነበሩ። ሁለቱም የተመቱት አርብ ዕለት በቱርክ የባህር ጠረፍ ሲሆን ቪራቱ የተሰኘው መርከብ ቅዳሜ ዐዕለት በድጋሚ ተመትቷል ተብሏል።

እስካሁን ድረስ በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት ስለመድረሱ የወጣ መረጃ የለም።

የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃቱ በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል ለሚያካሂደው ጦርነት ለሞስኮ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ወሳኝ የሆነውን የነዳጅ ዘይት ገቢ ለመጉዳት የተወሰደ እርምጃ ይመስላል።

ሁለቱ መርከቦች እአአ በ2022 ሩሲያ ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ ከወረረች በኋላ ምዕራባውያን የጣሉበትን ማዕቀብ ለማለፍ እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ለማሳለፍ የምትጠቀምባቸው "ሻዶው ፍሊት" የሚባሉት አካል መሆናቸው ተነግሯል።

እነዚህ በምስጢር ነዳጅ የሚያመላልሱ መርከቦች በአብዛኛው ያረጁ ነዳጅ መጫኛዎችን ቦቴዎችን የሚይዙ ሲሆን ብዙዎቹ ንብረትነታቸው የማን አንደሆነ እና የመድን ዋስትና የቱ ኩባንያ እንደሰጣቸው ግልጽ አይደለም።

ካይሮስ በጥቁር ባሕር በደቡብ-ምዕራብ ቪራት ደግሞ በማዕከላዊ ምሥራቅ አካባቢ ጥቃቱ እንደደረሰባቸው ተግለጿል።

እንደ ለንደን ስቶክ ኤክስቼንጅ መረጃ መሠረት ሁለቱም ማዕቀብ በተጣለባቸው መርከቦች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ናቸው።

ምንጮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ዩክሬን በጥቃቱ ወቅት ሲ ቤቢ (Sea Baby) ድሮን ጥቅም ላይ አውላለች።

እነዚህ የአገሪቱ የባሕር ኃይል የሚጠቀምባቸው ሰው አልባ አውሮፕላኖች የሚመረቱት በዩክሬን የፀጥታ አካላት ሲሆን ኤስቢዩ (SBU) በመባል ይታወቃሉ።

የቱርክ ባለሥልጣናት ለመርከቦቹ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው ሁለት የቱርክ ጀልባዎች በካይሮስ ላይ የተነሳውን እሳት ለማጥፋት ሲሞክሩ የሚያሳይ ምስል ይፋ አድርገዋል።

ጥቃቱ የሩሲያን ዘይት የጫኑ መርከቦች በጥቁር ባሕር ላይ የሚያደርጉት ጉዞ ከምዕራባውያን ማዕቀብ ብቻ ሳይሆን የኪየቭንም ቀጥተኛ ጥቃት ሊያስተናግዱ እንደሚችሉ ዩክሬን የሰጠችው ማስጠንቀቂያ ተደርጎ ተወስዷል።

በሌላ በኩል፣ ከካስፒያን የመጣ የነዳጅ ዘይት የሚያጓጉዘው ድርጅት በሰው አልባ ጀልባ ጥኣት ከደረሰበት በኋላ በሩሲያ ጥቁር ባሕር ኖቮሮሲይስክ ወደብ ላይ ነዳጅ መጫኑን ማቆሙን ገልጿል።

የካስፒያን ፓይላይን ኮንሰርቲየም ጥቃቱ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ብሏል። ሩሲያ እና ካዛኪስታን የኩባንያው ዋና ባለድርሻዎች ናቸው።

ከእነርሱ በተጨማሪም በከፊል እንደ ኤክሶን ሞቢል፣ ቼቭሮን እና ሼል ያሉ ምዕራባውያን ኩባንያዎችም ከፍተኛ ድርሻ አላቸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ቅዳሜ ዕለት ጦርነቱን ለማቆም በሚደረገው ስምምነት ላይ የተጀመረውን ንግግር ለመቀጠል በከፍተኛ የፀጥታ ባለስልጣን ረስተም ኡሜሮቭ የሚመራ የልዑካን ቡድን ወደ አሜሪካ ጉዞ ጀምሯል።

የቀድሞው ዋነኛ ተደራዳሪ አንድሪይ ይርማክ አርብ ዕለት እየተደረገባቸው ያለውን የሙስና ምርመራ ተከትሎ ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን ተከትሎ ኡሜሮቭ የዩክሬንን ልዑካን ቡድን ይመራሉ።

የዩክሬን ልዑካን እሁድ ዐዕለት በፍሎሪዳ ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚገናኙ ይጠበቃል። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ሞስኮ በማምራት ውይይት ያደርጋሉ።